
ሸገር ከተማ፦ በሸገር ከተማ በኢንቨስትመንት ላይ የመሰማራት ፍላጎት እየጨመረ መሆኑን የከተማዋ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ፅህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ነብዩ ራጋ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ከተማዋ ከተመሠረተች ገና ሶስት ዓመት ባይሞላትም በኢንቨስትመንት ላይ የመሰማራት ከፍተኛ ፍላጎት እየታየ ነው።
እንደምክትል ሃላፊው ገለጻ፤ እየተጠናቀቀ ባለው በጀት ዓመት ብቻ ከ200 በላይ ሥራ ፈጣሪዎች እና ከ30 በላይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ተመዝግበው ወደ ትግበራ ገብተዋል። በተጨማሪ ከ500 በላይ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮችም የኢንቨስትመንት ዘርፉን ተቀላቅለዋል። እነዚህ ባለሀብቶች ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል አስመዝግበው ኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል።
የኢንቨስትመንት ዋናው ግቡ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን የሥራ እድል መፍጠር መሆኑን የሚገልፁት አቶ ነብዩ ራጋ፤ ከ90 ሺህ በላይ የሥራ እድል በዓመት ውስጥ መፍጠር እንደተቻለ ገልፀዋል።
በተጨማሪ በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ከ200 በላይ ተጨማሪ ሥራ ፈጣሪዎች እና 400 ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ኢንቨስትመንት ለመጀመር የሚፈለገውን መስፈርት በማሟላት ወደ ትግበራ ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ጎን ለጎን የፕሮጀክት ክትትል እና የሴክተር አፈፃፀም ግምገማዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ የገለጹት ምክትል ኃላፊው አቶ ነብዩ፤ 5 ሺህ 97 የኢንቨስትመንት ፕሮጄክቶች በሸገር ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ስር ክትትል እና ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነ አመልክተዋል።
በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚካተቱ ከ2 ሺህ 600 በላይ እንደሆኑና በአገልግሎት ዘርፍ ላይ የሚገኙትም ከ1 ሺህ 900 በላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፤ 430 የሚሆኑት በግብርናው ዘርፍ ውስጥ የሚካተቱ ስለመሆናቸውም ገልጸዋል።
እንደ አቶ ነብዩ ራጋ ገለፃ፤ በከተማ አስተዳደሩ ስር አሁንም ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ የሚገኙ ኢንቨስትመንቶች ያሉ ሲሆን 364 የሚሆኑ ፕሮጀክቶች ግንባታቸውን ማጠናቀቃቸውን፤ 913 የሚሆኑት ደግሞ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገው ወደ ሥራ ለመግባት በሂደት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የከተማዋ አስተዳደር እና ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት መረጃ እንደሚጠቁመው የሸገር ከተማ በባለሀብቶች እምነት እያገኙ ካሉ ከተሞች መካከል ቀዳሚ ነች። የከተማ አስተዳደሩ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ በርካታ ንኡስ ከተሞችን በማቀናጀት ከሁለት ዓመት ከስድስት ወር በፊት የተመሠረተ እንደሆነ ታውቋል::
በ\ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም