
አዲስ አበባ፦ ብሔራዊ የንጹህ ማብሰያ ፍኖተ ካርታው በታሰበው ልክ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ በቀጣይ አሥር ዓመት ከ93 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የንጹህ ማብሰያ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጅነር ሱልጣን ዋሊ (ዶ/ር) ትናንት ፍኖተ ካርታውን ይፋ ሲያደርጉ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ጊዜ እንደሀገር ንጹህ የማብሰያ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች ቁጥር 10 በመቶ አይበልጥም። ይህም ማለት 90 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ማገዶ፣ ኩበትና ከሰልን በመጠቀም የእለት ምግቡን ያዘጋጃል።
በተለይ እናቶችና ህፃናት ምግብ ሲያበስሉ የሚጠቀሙት ማገዶ የሚፈጥረው ጭስ በጤናቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያመጣል ያሉት ኢንጅነር ሱልጣን (ዶ/ር)፤ ይህም ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተገናኘ በሽታ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በዘልማድ ለምግብ ማብሰያነት ጥቅም ላይ የሚውሉ ቁሳቁሶች ከእናቶችና ህፃናት ጤና አንፃር የሚያስከትሉት ጉዳት ሊፈተሽ እንደሚገባም አመልክተዋል።
ለምግብ ማብሰያነት የሚውል ማገዶ፣ ከሰልና ኩበት የአየር ንብረት ለውጥ መንስዔ እንደሚሆን ጠቁመው፤ እንደሀገር ያለውን የደን ሽፋን እንዲቀንስ ያደርጋል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር “ብሔራዊ ንጹህ ማብሰያ” የተሰኘ እና ለአሥር ዓመት ተግባራዊ የሚደረግ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቷል ነው ያሉት።
ፍኖተ ካርታው በታሰበው ልክ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ 93 ሚሊዮን ሕዝብ የንጹህ ማብሰያ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ይሆናል። በፍኖተ ካርታው 36 ሚሊዮን ስቶቭ እንደሚሰራጩ በዚህም 75 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የካርበን ልቀትን መቀነስ እንደሚቻል ጠቁመዋል።
ፍኖተ ካርታው በማኑፋክቸሪንግ፣ በአገልግሎትና በማከፋፈል ዘርፎች ለ335 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጠር የገለጹት ኢንጅነር ሱልጣን (ዶ/ር)፤ ከዚህም ባለፈ ፍኖተ ካርታው ማገዶና ኩበት ለቀማ ላይ የተሰማሩ እናቶችና ህፃናትን ትኩረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
እነዚህ እናቶችና ህፃናት በፍኖተ ካርታው አማካኝነት በዓመት 13 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ሰዓታትን ማትረፍ ይችላሉ። ይህም በትምህርት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች አቅማቸውን ማሳደግ እንዲችሉ እድል ይፈጥራል ብለዋል። የፍኖተ ካርታው ስኬታማነት በመንግሥትና በግል ዘርፉ መካከል ባለው ግንኙነት ልክ የሚወሰን መሆኑንም ተናግረዋል።
በተለይ ለፍኖተ ካርታው ተግባራዊነት የሚያስፈልገውን ሶስት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት የጋራ ትብብር ወሳኝ ነው ያሉት ኢንጅነር ሱልጣን (ዶ/ር)፤ ለዚህም መንግሥት የግል ዘርፉ በኢነርጂው ዘርፍ እንዲሳተፍ የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረጉን ገልጸዋል።
ባለፉት 30 ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የኢነርጂ ፖሊሲ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ከግምት ውስጥ ያስገባ አለመሆኑንም አውስተው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየመነጨ ያለው ኢነርጂ ስድስት ነጥብ አራት ጊጋ ዋት ሲባል በመንግሥት ብቻ ኢንቨስት የተደረገ እንደሆነ መታወቅ አለበት ነው ያሉት።
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውም ከፍተኛ ኢነርጂ የሚጠቀሙ ፋብሪካዎችን ስለሚጋብዝ የኢነርጂ ፍላጎት እንደሚጨምር ተናግረው፤ ለዚህም የመንግሥትና የግል አጋርነት አዋጅ እንዲሁም ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች በማመቻቸት እንደሀገር የሚያስፈልገውን ኢነርጂ ለማሟላት የግሉን ዘርፍ ሚና የማሳደግ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ አመልክተዋል።
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
በሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም