አዲስ አበባ፡- በግለሰብ ቸልተኝነት ማህበረሰብን እና አገርን ለአደጋ የሚጥል አካሄድ እንዳይፈጸም ህግ የማስከበር ስርዓቱ ጠንከር ባለ መልኩ እንዲፈጸም
ትእዛዝ መተላለፉን በሚኒስትሮች ምክር ቤት የኮሮና ቫይረስን (ኮቪድ 19) ለመከላከል የተቋቋመው ንዑስ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ኮሚቴው እስካሁን በተወሰኑ ውሳኔዎችና አጠቃላይ
ሁኔታ ዝርዝር የአፈጻጸም ግምገማዎችን ማካሄዱን፣ በግምገማው መሰረት ለወደፊቱ መደረግ ስለሚገባቸው ጉዳዮች አቅጣጫ ማስቀመጡን አስመልክተው፤ህግና ስርዓትን የማስከበሩ ሥራ ከማስተማር ጎን ለጎን ተጠናክሮ
እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህብረተሰቡ የህግ አስከባሪ አካላት ባልተመቹ ሁኔታዎች እየሰሩት ያለውን ሥራ መደገፍና መተባበር እንደሚገባ ጠቅሰው፤ አንዳንድ ለአደጋ የሚያጋልጡ ምልክቶች ስላሉ የሁሉንም አካላት ርብርብና የተቀናጀ ሥራ እንደሚያስፈልግ ኮሚቴው መመልከቱን አስረድተዋል፡፡
በንግድ ስርዓቱ የታዩ አንዳንድ መጥፎ ምልክቶችን ለማስተካከል የአሰራር ስርዓት መዘርጋቱን የጠቆሙት አቶ ደመቀ፤ ችግሩን ለመሻገር የህሊና እርቅ መፍጠር ይገባል እንጂ የተለየ ትርፍ ለማግኘት መሻትና መጓዝ ከዜግነትና ሰዋዊ ሚዛን ያወርዳል ብለዋል፡፡
በዓለም ደረጃ ያለው አስከፊና አሳሳቢ ደረጃ በርቀት የሚታይ ሳይሆን በአገራችን በደጃችን ደርሷል ያሉት አቶ ደመቀ፤ ‹‹በሞት ደረጃ ተጋላጭ ባንሆንም ዜጎች ተጠቂ ሆነዋል፤ያለምንም መዘናጋት ለከፋው ችግር መዘጋጀት ያስፈልጋልም ››ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ መረበሽና መጨነቅ አያስፈልግም፡፡ አሻግረን እየተመለከትን እንደማይደርስብን እያሰብን ከተዘናጋን የከፋ አደጋ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ሁሉም ዘማች ሆኖ ኃላፊነቱን ለመወጣት መረባረብ
ይገባዋል ፡፡ የዓለም የጤና ድርጅት ያስቀመጣቸውን ህግጋቶች በመፈጸም አደጋውን መከላከል ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም ኃላፊነቱን ከተወጣ አገርን ነጻ ማድረግ ይቻላል፡፡ በሌሎች አገሮች የታየው አደጋ እንዳይደርስ አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
የመገበያያ ስፍራዎች አካላዊ ርቀትን ጠብቆ የመተግበሩ ሂደት መሻሻሎች ቢታይበትም አሁንም ከፍተኛ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል ፡፡ የሃይማኖት ተቋማት የእምነቱን ስርዓት ተከትሎና ርቀትን ጠብቆ እንዲከናወን ከሃይማኖት አባቶች ጋር ምክክር በመደረጉ ዜጎችን መታደግ እንዲቻል ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ኮሚቴው ወስኗል፡፡
በፌዴራል መንግሥትና በክልሎች መካከል የሚወሰዱ የመከላከል ስርዓቶች ግንኙነታቸውን ማጠናከር፣ ወጥና ተመጋጋቢ የሆነ የመከላከል ስርዓት እንዲዘረጋ ኮሚቴው መወሰኑን አቶ ደመቀ አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን 87 የበረራ ግንኙነቶችን ዘግቷል ያሉት አቶ ደመቀ፤ በእዚህ ላይ በመመስረት ከፍተኛ የጥንቃቄ ሥራዎች እንደሚከናወኑና ከተለያዩ አገሮች የሚገቡ ዜጎች ለቆይታ ወደ ተመደቡ ሆቴሎች የመውሰዱ ሥራ የበለጠ ሊጠናከር እንደሚገባው ኮሚቴው ውሳኔ ላይ መድረሱንም ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ደመቀ ገለጻ ፤ወረርሽኙ የጤና ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና አጠቃላይ የአገር ህልውና እየሆነ መጥቷል፡፡ ከህብረተሰቡ የአኗኗር ሁኔታና ድህነት በመነሳት አስቀድሞ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ የኢኮኖሚ ጉዳትን ለመቀነስና አቅም ለመገንባት፣ በህብረተሰቡ በኩል ለመደጋገፍና ለመተጋገዝ ያለውን ፍላጎት በተቀናጀና ወጥ በሆነ ስርዓት እንዲመራ ኮሚቴው ወስኗል፡፡ የገቢ ማሰባሰብና የምግብ ክምችት ሥርዓትም ተዘርግቷል፡፡
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ያሉ ዜጎች ካላቸው በማካፈል ያለውን ችግር ለመሻገር ያሳዩት ቁርጠኝነት የሚያበረታታ ነው፡፡ የሃብት አሰባሰብና አጠቃቀሙ በኃላፊነትና በጥንቃቄ ለቁርጥና ለባሰ ጊዜ እንዲውል ሥርዓቱን የበለጠ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ያቋቋመው የገቢ አካል እንጂ ሌሎች ጎን ለጎን የሚካሄዱ የገቢ ማሰባሰብ ሥራዎች ጠቀሜታቸው ያን ያህል ስለሆነ ወጥ በሆነው ሥርዓት ተመጋግቦ እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡
በአገር ውስጥም ንብረታቸውን፣ የንግድ ድርጅታቸውን፣ መኖሪያ ቤታቸውን ሆቴላቸውንና ልዩ ልዩ አፓርትመንቶችን ለእዚህ ዘመቻ እንዲውሉ ለተወሰነ ጊዜ ያመቻቹ ዜጎች አሻራቸው በታሪክ የሚቀመጥ ነው፡፡ ሌሎችም ይህንን ተግባር ተከትለው አቅማቸው በፈቀደ
መጠን ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ብዙ ዜጎች የዕለት ማደሪያ የሌላቸው መኖራቸውን በግምት ውስጥ ያስገባው ኮሚቴ፤ ለድርቅና ለተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች የተዘረጋውን የምግብ ክምችትን የማሳደግ ተግባር ኮሚቴው ተጠናክሮ እንዲተገበር ወስኗል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የገበያ ስርዓቱን በማሳለጥ የምግብ ክምችት አስተማማኝ ሆኖ መጥፎ ጊዜን ለመሻገር የሚያስችል አቅምን መገንባት ትኩረት እንደሚደረግበትም ጠቁመዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የጸጥታ አካላት በጠረፍ ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚያገናኙ መውጫና መግቢያ በሮችን እየለዩ አካባቢውን የመቆጣጠርና የመከላከል ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ባልታሰበና ባልታቀደ ሁኔታ ከውጭ የሚገቡ ዜጎች መኖራቸውንና በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሥርዓትም ወደ ባሰ ችግር ለመጓዝ የሚሞክሩ እንዳሉ አስረድተዋል፡፡
በድንበር አካባቢ አመቺ የመቆያ ሥፍራዎች የማዘጋጀት፣ አስፈላጊ የኳራንቲንና የምርመራ ሥራዎች በመስራት ወደፊት ከህብረተሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ የማድረግ ሥራዎች እንዲተገበሩ መወሰኑንም አክለው ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2012
ዘላለም ግዛው