ባህርዳር፣ በአማራ ክልል የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ባህር ዳርና እንጂባራን ጨምሮ በአራት ከተሞች የተሽከርካሪም ሆነ የሰዎች እንቅስቃሴ መታገዱን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ይርሳው ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት የእንቅስቃሴ ገደቡ የተጣለው በባህር ዳር፣ እንጅባራ፣ ቲሊሊና አዲስ ቅዳም ከተሞች ነው።
በእነዚህ ከተሞች ከዛሬ መጋቢት 23 ቀን 2012 ዓ/ም ከቀኑ 6 ሰዓት ጀምሮ ለ14 ተከታታይ ቀናት ማንኛውም እንቅስቃሴ እንደማይደረግ በኮሮና መከላከል ኮማንድ ፖስት መወሰኑን ገልፀዋል።
በከተሞቹ እንቅስቃሴ እንዲገደብ ውሳኔ ላይ የተደረሰው በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው ምርመራ ከተደረገላቸው 27 ሰዎች መካከል በሁለቱ ከተሞች ላይ ቫይረሱ መገኘቱ በመረጋገጡ እንደሆነ አመልክተዋል።
ቫይረሱ ከተገኘባቸው ግለሰቦች መካከልም አንዷ ከዱባይ የመጣች የባህርዳር ነዋሪ ስትሆን 2ኛው ደግሞ ከአሜሪካን ሀገር ወደ እንጅባራ ከተማ የመጣ መሆኑን ገልፀዋል።
ግለሰቦቹ በቆይታቸው ከሰዎች ጋር በነበራቸው ቆይታ ለቫይረሱ አጋላጭ የሆኑ ግንኙነቶች ይኖራቸዋል ተብሎ በመገመቱ እንቅስቃሴው እንዲገደብ ውሳኔ ላይ መደረሱን አቶ ጌትነት አብራርተዋል።
ከግለሰቦቹ ጋር ግንኙነት የነበራቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች የመለየት ስራም እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በከተሞቹ የበጎ አድራጎት ስራ የሚሰሩ ወጣቶች፣ሰብዓዊ አገልግሎት ከሚሰጡ ደረቅና ፍሳሽ ከሚጭኑ ተሽከርካሪዎችና ከተፈቀደላቸው ሰዎች በስተቀር ማንኛውም ሰው እንቅስቃሴ እንዳያደርግ እገዳ መጣሉን አውቆ ህብረተሰቡ ለተላለፈው ውሳኔ ተገዥ እንዲሆን አሳስበዋል።
የእንቅስቃሴ እገዳ የተጣለባቸው ከተሞችን የሚያቋርጡ ተሽከርካሪዎችም በእነዚህ ከተሞች ማራገፍም ሆነ መጫን እንደማይችሉ መወሰኑን ገልፀዋል።
የክልሉ የፀጥታ ኃይልም ህጉን ተላልፎ የሚገኝ ካለ ህግ የማስከበር እርምጃ እንዲወስድ ትዕዛዝ መሰጠቱንም አስታውቀዋል። በሽታው እንዳይሰራጭ ሲባል ወደ ለይቶ ማቆያ ለሚገቡ ግለሰቦች የሚሆን የምግብና ሌሎች ቁሳቁሶች ህብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ዋና ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2012