- የንግዱ ማህበረሰብ ከህዝብና ከመንግሥት ጎን ሊቆም እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ:- ጊፍት ሪል እስቴት በመንግሥት እየተደረገ የሚገኘውን የጸረ ኮቪድ- 19 እንቅስቃሴን በማጠናከር የቫይረሱን ስርጭት በአገሪቱ ለመግታት ለሚደረገው እርብርብ የሚውል የአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ። የንግዱ ማህበረሰብ የተፈጠረውን የጤና ቀውስ ተጠቅሞ ያልተገባ ትርፍ ለማግበስበስ ከላይ ከታች የሚልበት ሳይሆን ከመቼውም ጊዜ በላይ ከህዝብና ከመንግሥት ጎን ሊቆም የሚገባበት ወቅት መሆኑ ተገልጿል።
ድርጅቱ የጸረ ኮቪድ 19 ወረርሽኝን እንቅስቃሴን አስመልክቶ ትናንት በሰጠው መግለጫ የጊፍት ቢዝነስ ግሩፕና የጊፍት ሪል እስቴት መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ገብረየሱስ ኢጋታ እንደገለጹት፤ ኮቪድ- 19 የተባለው ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በአገሪቱ መግባቱ በምርመራ ከተረጋገጠበት ጀምሮ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሚደረገው እርብርብ ድርጅቱ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በተጨማሪም ድርጅቱ በመንግሥት እየተደረገ የሚገኘውን የጸረ ኮቪድ- 19 እንቅስቃሴን በማጠናከር የቫይረሱን ስርጭት በአገሪቱ ለመግታት ለሚደረገው እርብርብ የሚውል የአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።
ኮቪድ 19 ያደገ ኢኮኖሚና ደረጃውን የጠበቀ የጤና መሰረተ ልማት ባላቸው አገራት ጭምር ቫይረሱን ለመቆጣጠር አዳጋች ሆኖ ባቸው እንደ ሰደድ እሳት እየለበለባቸውና እንደ አውሎ ንፋስ ዓለምን እያደረሰ ሲሆን፤ በኢትዮጵያም ቫይረሱ መገኘቱ ይፋ ከተደረገ ወዲህ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እያሻቀበ እንደሚገኝ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ድርጅቱ የኮቪድ 19 ቫይረስ ስርጭትን በአገሪቱ ለመግታት ከመንግሥት የተላለፈውን ጥሪ መሰረት በማድረግና የሚጠበቅበትን ማህበራዊ ኃላፊነት ከመወጣት አንጻር የተለያዩ ተግባራትን እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
እርሳቸውም ለአብነት የበሽታውን አምጭ ቫይረስ ለመከላከል በዋነኝነት የግል ንጽህናን መጠበቅ ግንባር ቀደሙ የመከላከያ መንገድ በመሆኑ፤ ድርጅቱ በመዲናዋ በርካታ ሰው በሚንቀሳቀስባቸውና የእጅ መታጠቢያ
ውሃ እጥረት ባለባቸው ሰባት አካባቢዎች ላይ ባለ አንድ ሺ ሊትር ውሃ የሚይዝ በርሜል፣ ሳሙናና ሌሎች የጸረ ጀርም ግብዓቶችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ህብረተሰቡ ንጽህናውን እንዲጠብቅ የማድረግ ሥራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የድርጅቱ ሰራተኞችና በጎ ፍቃደኞችን በማስተባበር በሽታውን መከላከል በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ የተለያዩ የግንዛቤ መስጨበጫ ሥራዎችን የማከናወን ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ድርጅቱ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች እየተረዱ ለሚኖሩ አረጋውያን በሽታውን ለመከላከል የሚረዱ ግብዓቶችን እያቀረበ የሚገኝ ሲሆን፤ ለመቄዶኒያ አረጋውያን መርጃ ማዕከል ለሚገኙ አረጋውያን የንጽህና መጠበቂያ የሚውል ጠጣርና ፈሳሽ ሳሙናዎችን፣ አንድ ሺ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስኮችን እንዲሁም አንድ ሺ ሊትር ውሃ የሚይዝ በርሜል ወጥነት ካለው የውሃ አቅርቦት ጋር መቅረቡን ተናግረዋል።
ከላይ የተዘረዘሩት ድጋፎች የበሽታው ስርጭት በአገሪቱ እስከሚገታ ድረስ ተጠናክሮና ተስፋፍቶ እንደሚቀጥል በድርጅቱ ስም አቶ ገብረየሱስ አረጋግጠው፤ ድርጅቱ በግል እያከናወናቸው ካሉ ተግባራት በተጨማሪ ወረርሽኙ በሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ጫና ምክንያት የምግብ እጥረት ለሚያጋጥማቸው ዜጎች የምግብ አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ፤ ከሌሎች በጎ ፈቃደኛ የቢዝነስ ድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር በመሆን ከየካ ክፍለ ከተማ የምግብ መጋዘን ተረክቦ የተለያዩ ለምግብነት የሚውሉ ግብዓቶችን የማሰባሰብ ሥራ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የንግዱ ማህበረሰብ የተፈጠረውን የጤና ቀውስ ተጠቅሞ ያልተገባ ትርፍ ለማግበስበስ ከላይ ከታች የሚልበት ሳይሆን ከመቼውም ጊዜ በላይ ከህዝብና ከመንግሥት ጎን ሊቆም የሚገባበት ወቅት መሆኑን አሳስበው፤ የንግዱ ማህበረሰብ ሰርቶ ማግኘት የሚቻለው ህዝብና መንግሥት ሲኖር መሆኑን አውቆ፤ የተፈጠረውን ችግር እንደ ምክንያት በመውሰድ ለህብረተሰቡ የሚያቀርበውን ግብዓት በመደበቅ ሰው ሰራሽ የዋጋ ውድነት በመፍጠር ዋጋ ጨምሮ ሳይሸጥ ያለውን አካፍሎና ተጋግዞ ይሄን የፈተና ወቅት ማለፍ እንደሚገባ አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2012
ሶሎሞን በየነ