በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ግጭቶች እዚህም እዚያም ይቀሰቀሱ አንደነበር ይታወሳል።በሶማሌ ክልል፣ በሲዳማ ዞን፣ በወለጋ እና ጉጂ ዞኖች፣ በአማራ ክልል እና በሌሎችም ተመሳሳይ የሰላም እጦቶች በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት የመከላከያ ሠራዊት መሰማራቱ ይታወቃል። በየአካባቢው በተቋቋሙ ኮማንድ ፓስቶች ውስጥ ከሌሎች የጸጥታና ደህንነት ሀይሎች ጋር ሰርቷል፤ እየሰራም ይገኛል።
በዚህም በሀገሪቱ ተጋርጦ የነበረውን አደጋ ቀልብሷል። በእነዚህ አካባቢዎች ሰላም እንዲመለስ በማድረጉም ነገሮች ወደ ቀድሞው ሁኔታቸው ተመልሰው ልማቱ ቀጥሏል። ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ልዩ ቃለ ምልልስ ያደረጉት የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ብርሀኑ ጁላ እንዳሉትም ሠራዊቱ የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለመመለስ የተሰጠውን ግዳጅ በብቃት ተወጥተዋል። ከጀነራሉ ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ የሰላምና መረጋጋት፤ የመከላከያ ፋወንዴሽን፤ የምእራብ ወለጋ ጸጥታና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ቃለምልልስ ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- በተለያዩ የሀገሪቱ አቅጣጫዎች ተነስቶ የነበረው የሰላም መደፍረስ በአንጻራዊነት ተረጋግቷል።በእዚህ በኩል መከላከያ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።ችግሮቹን እንዴት ነው መፍታት የተቻለው?
ጀነራል ብርሀኑ፡- በአሁኑ ወቅት በንጽጽር ከሁለት አመታት በፊት ከነበረው ጋር ሲታይ በሀገሪቱ ሰላም ሰፍኗል። የለውጡ እንቅስቃሴ ሲመጣ የነበረው የጸጥታ መደፍረስ እየጠራ መጥቷል። ከሞላ ጎደል ሀገራችን አስቸጋሪና ውስብስብበ መስሎ ከሚታየው የጸጥታ ችግር ወጥታለች። አሁን ላለው ሰላምና መረጋጋት መፈጠር ሕዝቡ ከመከላከያና ከክልል የጸጥታ ኃይሎች ጎን በመሰለፍ ከፍተኛ ትብብር አድርጓል።
ለውጡ እንደመጣ ያመጸው የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ነበር። ቤተክርስቲያን እንዲቃጠል፤ ንብረቶች እንዲወድሙ በአካባቢው ደገኛ ተብሎ የሚጠራው ወገን ጅጅጋን እንዲለቅ ሰፊ እንቅስቃሴ ተደርጓል። ከፍተኛ የመንግስትና የዜጎች የግል ሀብት ከመዘረፉም አልፎ እንዲወድም ተደርጓል። ከዚህም በላይ ይህን ድርጊት የፈጸመው አካል መገንጠልን ለማወጅ ተዘጋጅቶ የክልሉን ልዩ ኃይል አሰማርቶ ከፌዴራል መንግስት ጋር ለመዋጋት ጥረት አድርጎም ነበር።
ደም ሳይፈስ፤ እልቂት ሳይከተል ተጽእኖ በመፍጠር ዜጎች እንዳይጎዱ መንግስት ከፍተኛ ትዕግሰት አድርጎ በዲፕሎማሲና በጥበብ በሰላማዊ መንገድ ፕሬዚዳንቱ እጁን እንዲሰጥ ተደርጎ ችግሩ ተፈቷል።
ኃይል አስገብተን አማራጭ በመከልከል፤ ሕዝቡ ውስጥ የእርስ በእርስ ግጭት ሳይከሰት፤ ከልዩ ኃይሉም ሆነ ሄጎ ከሚባለው የቀድሞው የክልሉ ፕሬዚዳንት ካደራጀው የወጣት ታጣቂ ኃይል ጋር ግጭት ሳይፈጠር አስፈላጊውን ወታደራዊና ቁልፍ መሬቶችን ተቆጣጥረን በመያዝ ሙሉ የኃይል የበላይነታችንን አረጋግጠናል። ፕሬዚዳንቱ ተስፋ በመቁረጡ መጥቶ እጅ እንዲሰጥና በአውሮፕላን ከክልሉ እንዲወጣ ተደረገ። በዚህ መልኩ ሶማሌ ክልል ወደ ሰላም እንዲመለስ ተደርጓል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከአሁን የሶማሌ ክልል ፍጹም ሰላማዊ ነው። በሰላም እየተመራ ይገኛል።
ቀጥሎ ያጋጠመን የደቡብ ክልል የሲዳማ ዞን ችግር ነው። በዚህም ውስጥ ለጥፋት የተዘጋጁ ኃይሎች ስለነበሩ አጀማመሩ ከፍተኛ እልቂት ሊፈጠርበት የሚችል ነበር።የሀዋሳውን፣ በወላይታና ሲዳማ የተደረገውን ግጭት ስናይ የሲዳማና የወላይታ ሕዝቦች እንዲተላለቁ አላማ የነበራቸው ኃይሎች ሆን ብለው አቅደው ከፍተኛ አሻጥር (ሳቦታጅ) የፈጠሩበት ነው።የክልሉ የጸጥታ ኃይል ወደ ሲዳማና ወላይታ የተከፋፈለና ደካማ ነበረ። ችግሩን መከላከያ ሠራዊታችን ገብቶ ፈቶቷል።
ሌላው አደገኛ ችግር በአማራ ክልል የተከሰተው ነው። እሱንም መከላከያ ገብቶ በዘዴና በእርጋታ ፈቶታል።የክልሉ የጸጥታ ኃይል በተለይ ነባሩ ለሰራዊቱ ከፍተኛ እገዛ አድርጓል። እኛ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ እንዳይወጣ በማድረግና ተቋማትን በመቆጣጠር ላይ ሰርተናል።
በከሚሴም ግጭት መከሰቱ ይታወቃል ግጭቱ የሕዝብ ለሕዝብ አይደለም። ሕዝቡና የክልል ጸጥታ ኃይሎች የፈጠሩት ግጭት ነበር።ግለሰቦች የፈጠሩት ችግር ነው። መከላከያ በሕዝቡና ጸጥታ ኃይሉ መካከል በመግባት ሕዝቡን በማረጋጋት የጸጥታ ኃይሉን ገለል በማድረግ ችግሩ ተፈቷል።እንደዚያ ባናደርግ መተላላቁ በጣም ይከብድ ነበር።
በአዲስ አበባም ከኦነግ መምጣት ጋር ተያይዞ ረብሻ፤ መገዳደል፤ የጎራ መደበላለቅ ከቡራዩም ጋር ተያይዞ ከባድ ሁኔታዎች ተከስተዋል።ይህን ለመፍታት የመከላከያ ሠራዊት ዋጋ ከፍሏል። በዚህ መልኩ በመላው ሀገሪቱ ችግሮች በተከሰቱበት ቦታ ሁሉ ፈጥነን እየደረስን ችግሮቹን በመፍታት ፋታ በማይሰጡ የጸጥታ ስራዎች ውስጥ ተጠምደን ቆይተናል።
በኋላ ላይ ኦነግ በሁለት ተከፈለ፤ የሸኔ ኦነግ እንቅስቃሴ ቀጠለ። ግማሹ በሰላም እታገላለሁ ብሎ አዲስ አበባ ከፊሉ እጄን አልሰጥም የትጥቅ ትግል አደርጋለሁ ብሎ ገጠር ገባ። ኦነግ ይከፈላል የሚል ግምት አልነበረም። ውሎ አድሮ በሰላም ይገባሉ እየተባለ ከኦነግ መሪዎች ጋር ለአራት ወራት ንግግር ተደረገ።እነሱ ግን በእነዚህ ወራት በከፍተኛ ደረጃ ራሳቸውን አጠናከሩ። መንግስትን በሶስት ወር ውስጥ እንገለብጣለን አሉ።
በእንቅስቃሴያቸውም በተለይ የወለጋና የጉጂ ዞኖች እንቅስቃሴ ቆመ። የመንግስትን መዋቅር አፈራረሱት። ሕዝቡን በኃይል እያስገደዱ ነጠቁት፤ ደበደቡት፤ ገደሉት። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ መንግስት ለምን ዝም ይላል የሚል ጥያቄ አነሳ። መንግስት የሕግ የበላይነት መከበር አለበት ብሎ ወሰነ፤ ወደ ስራ ገባን።
ሰላም ይበጃል የሚል ተጽእኖ እየፈጠርን በጦርነት ከመጣችሁ አደጋው ይከፋል በሚል ትምህርት ለማስተማር ሞከርን፤ እነሱ ግን በፍጹም እምቢ አሉ። በተደጋጋሚ ለሰላም የተደረገው ጥረት መከነ።
ሌላ የሚጠበቅ አልነበረም። መከላከያ የማያዳግም እርምጃ ወሰደ። በአሁኑ ወቅት ወለጋም ጉጂም ሰላም ናቸው። በትጥቅ ትግሉ በሽብር ስራ ውስጥ የነበሩ እርምጃ ከተወሰደ በኋላ ተበትነው በጥብቅ እየተፈለጉ ያሉ አሉ። የተንጠባጠቡትን አባሎ ቻቸውን አሳዶ ለመያዝ በሰፊው እየተሰራ ነው። ለእዚህም ሕዝቡ ራሱ ከጸጥታ አካሎች ጋር ተቀናጅቶ እየተከታተለ መረጃና ጥቆማ ሰጥቷል።
በአሁኑ ወቅት በሕገወጥነት የተደራጀ አቅም ያለው፤ መዋ ቅር የሚያፈርስ፤ መን ገድና ትምህርት ቤት የሚዘጋ፤ ሕዝብን በመሳሪያና በጉልበት እያስገደደ ግብርና ታክስ የሚያስከፍል፤ ዜጎችን በግፍ የሚገድል የሚደፍር ኃይል የለም። መከላከያ ሕዝብን ከስጋት ከጭንቀት ከመዘረፍ ለማዳን ባከናወነው ተግባር በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ሰፍኗል።
በአማራም ሆነ በኦሮሚያ ክልል የተከሰቱ የሰላም ችግሮችን ለመፍታት በኃላም በሸኔ ኦነግ ላይ በተወሰደው እርምጃ ወቅት የየክልሉ የጸጥታ ኃይሎች በከፍተኛ ደረጃ ተሳትፈዋል። መከላከያ በተጓዳኝ የክልሉን የጸጥታ ኃይሎች የማጠናከር ስራ ሰርቷል።
አዲስ ዘመን፡- መከላከያ በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር የሰራ ቢሆንም፣ በሰብአዊ መብት ጥሰት የሚከሱት አሉ።እርስዎ ምን ይላሉ ?
ጀነራል ብርሀኑ ጁላ፡- በሕዝቡ ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰትና ረገጣ ሲፈጽሙ፣ ሲገሉት፣ ሲዘርፉት፣ ሲያስሩት፣ ሲያቃዩት በሕዝቡ ስም እየነገዱ ሲጫወቱበት የነበሩትን አስወግዶ የሕዝቡ ሰብአዊ መብትና ሰላም እንዲከበር ያደረገው መከላከያ ሠራዊታችን ነው። ይሄንን እውነት ሕዝቡ ይመሰክራል። ይሄንን ተራ ውንጀላና ክስ በመከላከያ ላይ የሚያሰሙት ያንን ወንጀል በሕዝብ ላይ የፈጸሙ ግብረአበሮች ናቸው።
ሕግና ስርአትን ስናስከብር፤ ሕዝብን የሚዘርፉ፣ ንጹሀንን የሚገድሉ፤ የሚደፍሩ፣ ሰላም አንፈልግም ብለው በሕዝብና በሠራዊታችን ላይ ተኩስ የከፈቱ ጸረ ሕዝቦችን ተከታትለን አሳደን እንዲመክኑ ስናደርግ የሰብአዊ መብት ተጥሷል የሚሉት የአሻባሪዎቹ ደጋፊዎች ብቻ ናቸው።
የእነሱ ቡድን ሽኔ በሕዝቡና በልጆቹ ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት በከፍተኛ ደረጃ ሲያካሂድ እንደ በጎና መልካም ነገር ቆጥረውት ትንፍሽ ብለው አያውቁም። ዛሬ ደርሰው የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ሁኖ ለመታየት ሲሞክሩ ያሳፋራል።
መከላከያ አኩሪ ተግባር አከናውኗል። ሕዝብና ልጆቹን ከአደጋ ታድጓል። የሕዝብ ወገንተኝነቱን በተግባር ደጋግሞ አረጋግጧል። አሁንም ይህንኑ ይቀጥላል።የመከላከያ ሠራዊትን ስም በማጥፋት ክብርና ዝናውን ለማጉደፍ የሚሞክሩ ክፍሎች ከነውረኛ ድርጊታው ሊታቀቡ ይገባል።ሠራዊቱ ሰላም ባስከበረ ሀገር ባረጋጋ ሊዘመትበት አይገባም።
ሠራዊቱ እንኳን ቢሳሳት አይ ይሄን ይሄን አታድርጉ ስህተት ነው ብሎ በተቆርቋሪነት ሀሳብ የሚሰጥ ጋዜጠኛ፤ ምሁር፤ የሀገር ሽማግሌ፤ የኃይማኖት አባት የሆነ እውነተኛ ዜጋ ነው የሚያስፈልገው። ሚዲያ በእጄ አለ ወይንም ለሚዲያ ቅርብ ነኝ በሚል ሠራዊቱ ያላደረገውን አድርጓል እያለ ሲወነጅል የሚውል የሕግ ጥሰት ፈጻሚዎቹ አካል ደጋፊና ተባባሪ እንዲሁም የተለየ አላማ ያለው አካል ነው። የእኛ ሠራዊት የሰብአዊ መብት ጥሰት አይፈጽምም።
አዲስ ዘመን፡- በቋሚነት ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋቱን ጠብቆ ለመሄድ ምን መደረግ አለበት ይላሉ ?
ጀነራል ብርሀኑ፡- አሁን የተገኘው ሰላምና መረጋጋት ዝም ብሎ አልመጣም። መከላከያ ብዙ መስዋእትነት ከፍሎበታል። በእርግጥ ሌሎችም የጸጥታና የደህንነት ተቋማት ተቀናጅተው ስለሚሰሩ የየቡኩላቸውን ድርሻ ተወጥተዋል።
ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋቱን በዘለቄታዊነት ጠብቆ ለመሄድ የሚቻለው ትልቁ የሕግ የበላይነት ሲከበር ብቻ ነው። መንግስት የዲሞክራሲ ምሕዳር ማስፋቱ፤ ሰው እንዲደራጅ እንዲናገር እንዲጽፍ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ፣ እስረኞች መፈታታቸው ስደተኞች መመለሳቸውም ጥሩ ነው። በሀገራችን ያልተለመደ ሀገርን ወደ ዲሞክራሲ ለማሸጋገር የሚረዳ መልካም ጅምር ነው።
የቀድሞ መንግስታት ጉልበተኞች ስለነበሩ ሁሉንም በኃይል ለማስተካከል ሞክረዋል። ይሄ ችግር ነበር። ሕዝቡ ዲሞክራሲን መለማመድ መቻል አለበት። አፈናና የጉልበት አካሄድ መቆም ይገባዋል ተብሎ እድል መሰጠቱ ጥሩ ነው።
ለውጡን ተከትሎ በሀገራችን ቀድሞ ያልታዩ ብዙ ችግሮችም ተከስተዋል። ቤተክርስቲያንና መስጊድ ማቃጠል፤ ልቅነት፣ ስድነት፤ ስርአተ አልበኝነት፤ ንጹሀን ዜጎችን መግደል፤ ሰው መስቀል ዘረፋዎች ብዙ አሳዛኝና
አሳፋሪ ነገሮች ታይተዋል።ሀገሪቱ መንግስት ሕግና ስርአት እንደሌላት አድርገው በመቁጠር ህገወጦች ብዙ ሞክረዋል።
ጉዳዩ በየአካባቢው ካሉ ጸጥታ አስከባሪዎች አቅም ያለፈ በመሆኑ መንግስት መከላከያው የግድ የሀገርን ሰላምና ጸጥታ ማስከበር ስላለበት እንዲገባ አድርጓል። በዚህም ከፍተኛ ውጤት ተገኝቷል። ህገወጦቹ ከልኩ የሚያልፍ ልቅነት እንደሌለ እያዩ ሲመጡ እየሰከኑ መጥተዋል። ዛሬ ሁኔታው በእጅጉ ተቀይሯል። የሕዝቡ ስጋት ቀንሷል። የሕግ የበላይነትን የማስከበሩ ስራ በማያቋርጥ መልኩ ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን፡- መከላከያ ከክልል የጸጥታ ኃይሎች ጋራ ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል ?
ጀነራል ብርሀኑ፡- ሁለቱም ተባብረው፣ ተቀናጅተውና ተናበው እየሰሩ ናቸው። ሰራዊቱ ኮማንድ ፖስት (ማዘዣ ጣቢያ) በተቋቋመባቸው አካባቢዎች ሁሉንም ኃይሎች በስሩ አስገብቶ ይሰራል። በዚህም ውጤታማ ተሆኗል።
አዲስ ዘመን፡- ሠራዊቱ ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርገው መዋጮና ድጋፍ እንዴት ይገለጻል? ግድቡን የመጠበቅ ከፍተኛው ኃላፊነትም የመከላከያ መሆኑ ይታወቃል። አሁን ስላለው የሰራዊቱ ድጋፍ እና ተልእኮ ቢያስረዱን ?
ጀነራል ብርሀኑ፡- የሀገር መከላከያ ሠራዊት የታላቁ ሕዳሴ ግደብ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ መዋጮውን አላቋረጠም። ለግድቡ ከፍተኛ ገንዘብ ካዋጡ ተቋማት ግንባር ቀደሙ ነው። ሕይወቱን ለሀገር ሰጥቶ ገንዘቡን የሚሰስት ኃይል አይደለም። በየአመቱ የአንድ ወር ደመወዙን ይከፍላል።ግድቡ ለሠራዊቱ የሀገር ሉአላዊነት ጉዳይ እና ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ግድቡን መስራት እየፈለገ ሳይሳካለት ኖሯል። ግድቡን አቅም አግኝተን እንዳንገነባ፣ ብድር ሲያስከለክሉ ተጽእኖ ሲያደርጉ የኖሩ ሀይሎች እንዳሉ ይታወቃል። ግድቡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ራሴን ላልማ ከድህነት ልውጣ ብሎ ከኪሱ ገንዘቡን አዋጥቶ የጀመረው የሕዝብ ፕሮጀክት ነው። ከእናቶች መቀነት ጭምር ገንዘብ ተዋጥቶ እየተገነባ ነው።
የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል በታላቁ ሕዳሴ ግደብ ዙሪያ የሚመጣ ማናቸውም አይነት ተቃርኖ በኢትዮጵያ ሕልውና ላይ የተቃጣ አደጋ አድርጎ ይወስደዋል። በግድቡ ጥበቃ ላይ ያሉትን የመከላከያ አባላት ሄደህ ብትጠይቃቸው ግድቡ የኢትዮጵያ ሕልውና ፕሮጀክት ነው ይሉሃል። በቅርቡ በጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹሙ የተመራው ቡድን ታላቁ ሕዳሴ ግድብን ሄዶ ጎብኝቷል። አላማው ግድባችን በደማችን ይጠበቃል፤ በግድባችን ላይ ምንም አይነት ድርድር የለም የሚለውን መልእክት ማስተላለፍ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ግብጽ ከታላቁ ሕዳሴ ግደብ ጋር በተያያዘ ሠራዊቷን በተጠንቀቅ እንዲቆም አዛለች ይባላል። ዛቻና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻቸው በእኛ በኩል እንዴት ይታያል ?
ጀነራል ብርሀኑ፡- እኛ በሰከነና ስርአት ባለው መንገድ እንራመዳለን። በስሜታዊነትና በጀብደኝነት ከሚያብዱ ጋር አናብድም። በሀብታችን የመጠቀም ሙሉ መብት አለን። የአባይ ውሀ ምንጭ 85 በመቶ ኢትዮጵያ ናት። ይህም ሆኖ ተፈጥሮ በጋራ እንድንጠቀምበት የሰጠንን ጸጋ በሰላም አብረን መጠቀም እንችላለን ብለናል።
የግብጽ ወንድሞቻችን በስክነ መንፈስ ማሰብ ይገባቸዋል። ውሀው ለሁላችንም ይበቃል። የአባይን ውሀ ያለገደብ በሞኖፖል ይዤ እኔ ብቻ ልጠቀምበት የሚል አስተሳሰብ ጤነኛ አይደለም። የኢትዮጵያ ጥያቄ የመልማት የማደግ ከድህነት የመውጣት የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም ነው፤ ግብጽን የመጉዳት ፍላጎትም ሆነ አላማ የላትም። ሁለቱን ሀገራት ወደ ጦርነት ውስጥ ሊያስገባ የሚችል ምንም አይነት መሰረታዊ ምክንያት የለም።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ጦርነት ሊያስገባ የሚችል ምክንያት በሌለበት የጦርነት ፉከራው ምን ይፈይዳል ?
ጀነራል ብርሀኑ፡- ኢትዮጵያ በአባይ ውሀ ላይ ግድብ ከሰራች ግብጽ ጦርነት ትከፍታለች የሚለውን በንጉሱም በደርግም ዘመን ብለውታል። ግድቡ በኢትዮጵያዊ የገንዘብ መዋጮ እየተሰራ ነው፤ የማንንም እርዳታ ሳይፈልግ ይጠናቀቃል።
በመጀመሪያ ደረጃ ጦርነት ምንድነው? ለምን ይነሳል? ገፊ ምክንያቶቹ ምንድንናቸው? የሚያስከትለው ተጽእኖና ውጤት ምን ይመስላል? ጦርነትን የሚሸከመው ብሔራዊ ኢኮኖሚስ? የሚሉትን አበይት የጦርነት መሰረታዊ መርሆዎች ትንተና መሰረት አድርጎ ማየት ተገቢ ይመስለኛል።
ታሪካችን ሁሉ የጦርነት ታሪክ ስለሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ስለጦርነት ማውራት ዋጋ የለውም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለብዙ ዘመናት በጦርነት ውስጥ የኖረ፤ ጦርነትን በተግባር የሚያውቅ ብዙ አይነት ጦርነቶችን ተጋፍጦ ያለፈ ነው፤ የሀገሩን ክብርና ሉአላዊነት ከየትኛውም አይነት ወራሪ በታላቅ መስዋእትነት የጠበቀ እና በሀገሩ ጉዳይ ድርድር የማያውቅ ነው።
እኛ የጦርነት ጉጉት፣ ናፍቆትና አራራ የለብንም። ግብጽ ከእኛ ጋር ጦርነት የምትከፍተው የትኛው ብሔራዊ ጥቅሟ ተነክቶ ነው የሚለው ግልጽ መሆን አለበት።ግብጽ ጦርነት እገጥማለሁ እያለች እየፎከረች ነው ለተባለው ሲፎክሩ እንሰማለን።
ጦርነት ለማስነሳት የሚያስችላቸው መሰረታዊ ምክንያት የላቸውም። የተፈጥሮ ሀብታችን የሆነውን የአባይ ውሀ ተጠቅመን ግድብ እንስራ፤ ኤሌክትሪክ እናምርት፤ እራሳችንን እናልማ ብለን ተነስተናል። የግድቡ ውሀ ኤሌክትሪክ አምርቶ እንደበፊቱ ፍሰቱን ይቀጥላል። ለምንድነው? ምን ለማግኘት? ምንስ ለማምጣት ነው? እንዋጋለን የሚሉት ነው መሰረታዊው ጥያቄ።
ግብጽ ወደ ጦርነት የምትገባበት ምክንያት አይታየኝም። እኔ እንደ አንድ ወታደርና መሪ ሳየው በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል የሠራዊት ግጭት የሚያመጣ ነገር በፍጹም የለም። ፖለቲከኞቹ በስሜታዊነት ተነስተው ማበድ ስለሚወዱ ማበድ ይችላሉ።
በዚህ ምክንያት የግብጽ ሠራዊት ከኢትዮጵያ ሠራዊት፤ የግብጽ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ጦርነት ይገጥማል የሚል ግምትም እምነትም የለንም። የግብጽ ሕዝብ ወንድማችን ነው። አንዳንድ ጊዜ የአበደ የገዢ መደብ ይኖርና አላማና ግብ የሌለው ጦርነት ሊከፍት ይነሳል። እንዲህ አይነቱ ነገር በምናልባታዊነት ሁልጊዜም ታሳቢ ተደርጎ ስለሚወሰድ ብዙም አያሳስብም። ዝግጁ ሕዝብና ሀገር አለን።
ግብጽ ሰፊ የከርሰ ምድር የውሀ ሀብት ክምችት እንዳላት እናውቃለን። ሕዝቡ ከእኛ የሚሄደውን ውሀ ሳያጣው እንደሚያጣው አስመስለው ሕዝብን አነሳስተው ጦርነት ውስጥ ከገቡ በእርግጠኝነት ይሸነፋሉ።
ሀቀኛ አላማ ሳትይዝ ጦርነት ውስጥ ከገባህ ትሸነፋለህ። ግብጽ ጦርነት ልታነሳ የምትችልበት ምንም አይነት ሀቀኛ አላማ የላትም። ግድቡ ተሰርቶ ያልቃል፤ የውሀ ሙሌቱ ስራ ይቀጥላል። ኤሌክትሪክ ያመነጫል። የትኛውም ኃይል ሊያስቆመው አይችልም። በዚህ ምክንያት ተነስቶ ዘራፍ የሚል ካለ የኢትዮጵያን ሕዝብ አያውቁትም ማለት ነው።
ጦርነት ሲኖር የኢትዮጵያ ሕዝብና መላው ኢኮኖሚዋ ወደ ጦርነት ይገባል። የኋላ ታሪካችንም ይሄንኑ ያሳያል። ታንክ አሰልፈህ ወታደር ደርድረህ ምሽግ ሰብረህ አትመልሰውም። ጦርነትን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ጦርነት እገጥማለሁ አይልም።
ጦርነት የሀገር ሀብትና የሰው ኃይል ይበላል፤ ያወድማል፤ ድህነትን ያራዝማል። የግብጽ መሪዎች፤ ፖለቲከኞች፤ ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ላይ ከሚሰነዝሩት የተሳሳተ የጥላቻ ቅስቀሳና ከተዛባ ፕሮፖጋንዳቸው መውጣት አለባቸው። ወንድማማች ሕዝብ ነን። ለሁላችንም የሚበጀው መነጋገርና መደራደር ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለሠራዊቱ አባላት በመከላከያ ፋውንዴሽን በኩል የመኖሪያ ቤት እየሰራችሁ መስጠት ጀምራችኋል ይባላል። እስቲ ስለፋወንዴሽኑ ቢነግሩኝ ?
ጀነራል ብርሀኑ ጁላ፡- የመከላከያ ፋወንዴሽን ቤቶች እየሰራ ነው። የተወሰኑ ቤቶች ሰርቶ እጣ አውጥቶ ለተጠቃሚዎች አስተላልፏል፤ ብዙ አይደሉም። አሁን ወደ 6000 ቤቶች ገደማ ግንባታ እየተካሄደ ነው። ግንባታቸው ሲጠናቀቅ በእጣ ይሰጣሉ። ይሄ የመጀመሪያው ነው። ከዚህ በመለስ ደግሞ መከላከያ እንደ ፊቱ ወታደራዊ ካምፖች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየገነባ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- በድሮው ምድር ጦር ግቢ ውስጥ የተጀመረው አዲሱ የመከላከያ ዋና ቢሮ ግንባታ ከምን ደረሰ ? የድሮው መከላከያ ቢሮ ምን ይሆናል?
ጀነራል ብርሀኑ፡- እየተገነባ ያለው አዲሱ የመከላከያ ሕንጻ እጅግ ዘመናዊ ነው። ሁሉንም ነገር ያሟላና እያደገ ለመጣው የሀገሪቱ መከላከያ ኃይል በሚመጥን መልኩ እየተካሄደ ያለው ግንባታ እየተጠናቀቀ ይገኛል። ለቀጣዩ ትውልድ በሚበጅና በሚያኮራ መልኩ የተሰራ የሀገር ሀብት ነው። የድሮው መከላከያ በቢሮነቱ ይቀጥላል፤ ቤት አልተረፈንም።
ኢትዮጵያ የምትገኝበት ጂኦ ፖለቲካዊ አቀማመጥ እጅግ ዘመናዊና ብርቱ የመከላከያ ኃይል እንዲኖራት ግድ ይላል። ዘመኑ የቴክኖሎጂ ጦርነት አፍጥጦ የመጣበት ነው። መከላከያ ይህን በሚመጥን መልኩ እየተደራጀ ቢሮዎቹም እየሰፉ ነው። የቢሮ ችግራችን ተፈቶ አልቋል ማለት አይደለም። መከላከያ እያደገና እየሰፋ ያለ ሀገራዊ የሕልውና ተቋም ነው። አሁን ያለንበት የመከላከያ ቢሮ የአንዱ ዘርፍ ቢሮ ሆኖ ይቀጥላል። ብዙ ይሰራበታል።
አዲስ ዘመን፡- የመከላከያ አንዱስትሪዎችስ በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?
ጀነራል ብርሀኑ፡- የወታደራዊ (ሚሊተሪ) ኢንዱስትሪዎች መኖርና መስፋፋት ከሀገር ሕልውናና ሉአላዊነት ጋር ይያያዛል፤ አሁን በመከላከያ ይዞታ ስር 6 የሚሆኑ ኢንዱስትሪዎች አሉን። ወደፊትም እንዳስፈላጊነቱ እየታየ እንጨምራለን።
የመከላከያ ኢንዱስትሪዎቹ ከጥገኝነትና ከውጭ ጠባቂነት ሊያላቅቁ የሚችሉ እራስን በሁሉም መስክ የመቻል ክቡር አላማን ያነገቡ ናቸው። ሲፈልጉ ሲሰጡን ሳይፈልጉ ሲከለክሉን የውጭ እጅ ጠባቂ ሁኖ ከመኖር ይልቅ በራሳችን ፋብሪካዎች በራሳችን ሳይንቲስቶች የራሳችንን ሁሉን አይነት ዘመናዊ ወታደራዊ ምርቶች ማምረት ለራሳችን መብቃትን ከውጭ ጠባቂነት መላቀቅን ግባቸው ያደረጉ ናቸው። በሂደት እያደጉና እየሰፉ ይሄዳሉ።
በአሁኑ ሰዓት ለመከላከያ የሚሆኑ ምርቶችን ያመርታሉ። በተለያየ መስክ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ኢንጅነሮች፤ ሳይንቲስቶች፤ እንዲሁም ሲቪል ሠራተኞችን ያቀፉ ዘመናዊ ኢንዱስትሪዎች ናቸው። የምርምርና የፈጠራ ስራዎች ይካሄዱባቸዋል። ሀገሪቱ የተከበረችና የታፈረች ኢትዮጵያ ሁና እንድትቀጥል ታላላቅ ስራዎች እየሰራን ነው። ብዙዎቹ ጉዳዮች ሀገራዊ ምስጢር ስለሆኑ አይገለጹም።
አዲስ ዘመን፡- የጀነራል ሰአረ መኮንን ጉዳይ በፍርድ ቤት እየታየ ነው። መከላከያ ጉዳዩን እንደሚከታተለው ይታወቃል። ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው ?
ጀነራል ብርሀኑ፡- መከላከያ የራሱ ጉዳይ ስለሆነ እያንዳንዱን ሂደት እየተከታተለ ነው። በፍርድ ቤት የተያዘ ነው። ከሳሽ አቃቤ ሕግ ሲሆን የፍርድ ሂደቱን የሚያየው ዳኛ ነው። በእኛ በኩል በየጊዜው እንከታተላለን። የፍርድ ውሳኔውን አብረን የምናየው ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሠራዊቱ ወስጥ ምን እየተሰራ ነው?፤ ሰራዊቱ ከካምፑ ውጭ እንዳይንቀሳቀስ እየተደረገ ነው ይባላልና ለእነ አልሸባብ እድል አይሰጥም ወይ ?
ጀነራል ብርሀኑ፡- የቀነስነው እንቅስቃሴ ነው። ወታደራዊ ካምፕ ባለባቸው ቦታዎች ሠራዊቱ በካምፕ እንዲቆይ አድርገናል። ሠራዊት ለመዝናናት ይወጣል፤ ዘመድ ቤተሰብ ጥየቃ ፈቃድ ወስዶ ይሄዳል። እነዚህ እንቅስቃሴዎች እንዲወሰኑ፤ ከቦታ ቦታ የኃይል ንቅናቄ እንዲቋረጥ፤ ጽዳትና ንጽህና በየካምፑ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ እንዲሰራ፤ አመራሩም ሆነ ሠራዊቱ ኮሮና ቫይረስን እንደ አንድ ትልቅ ሀገራዊ አደጋና ጠላት አይቶ ለዛ የሚጋብዙ ሁኔታዎችን ተከታትሎ እንዲቆጣጠርና እንዲያስፈጽም ተደርጓል። እቅድ ወጥቷል። በመከላከያና በእዞች በተለያዩ የጦር ክፍሎች ደረጃ ኮሚቴዎች ከላይ እስከ መጨረሻው አደረጃጀት ድረስ ተቋቁመዋል።
መከላከያ በተለያየ ደረጃ ያሉ ሆስፒታሎችና በየክፍሉም ያሉ የጤና ባለሙያዎች የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት በልዩ ትኩረት እየሰሩ ይገኛሉ። ግዙፍ ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚያስከትል አለም አቀፍ ወረርሽኝ ስለሆነ ለመከላከል ሰፊ ስራ እየሰራን እንገኛለን። የሰላም አስከባሪ ዝውውሩን (ፒስ ኪፒንግ ሮቴሽን) ለጊዜው አቁመናል።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ሰፊ ቃለምልልስ እናመሰግናለን።
ጀነራል ብርሀኑ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/./.2012