አዲስ አበባ፡- በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት የየተቋማቱ ኃላፊዎችና መምህራን ሥራቸውን በአግባቡ እየተወጡ አለመሆኑ ተገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና እንዳሉት፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ ለውጥ ለማምጣት ህዝቡ ተቃውሞዎች ሲያደርግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ ለውጡ ከመጣ በኋላም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ መንግሥትና የየተቋማቱ ኃላፊዎችና መምህራን ሥራቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ሁከቶቹ ተበራክተዋል፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚታዩትን የሰላም መደፍረስ ምክንያት የሚያጠና ቡድን ማዋቀሩን በመጥቀስ፤ በቀጣይ ለሚሠራቸው ሥራዎች አንድ ሚሊዮን ብር መመደቡን ገልጸዋል፡፡ ሰላም ከሌለ ልማትና የመኖር ነፃነት ስለማይኖር በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ በመድረኩ ጥናት ያቀረቡት ዶክተር ዮሐንስ አላዩ፤ እንደ አገር ለመቀጠል ቅድሚያ ሰላም እንደሚያስፈልግና ሰላም ለማምጣት አብሮ የመኖር እሴቶች ተግባራዊ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አካባቢም ይሁን በሌሎች ቦታዎች የሰላም መደፍረሶች የሞራል ልዕልና ማጣት ዋነኛ ተጠቃሽ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የወጣቶች ተምረው ሥራ ማጣት፣ አክራሪነትና ፅንፈኝነት፣ የህግ የበላይነት አለመኖር ይበልጥ የሰላም መደፍረስ እንዲባባስ ማድረጋቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ የኔ ነገር ከሁሉም ይበልጣል በሚል ግጭቶች እንደሚበዙ ጠቁመዋል፡፡ ለዚህ ችግር መባባስም መንግሥት፣ የየተቋማቱ ኃላፊዎችና መምህራን ሥራቸውን በአግባቡ አለመወጣታቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ችግሮችን ለመፍታት የመጣውን ለውጥ መቀበል፤ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አካባቢ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን ማስቆም፣ በትምህርት ቤቶች ባህላዊ እሴቶችን የሚያንጸባርቁ ትምህርት መስጠት እንዲሁም ችግር የሚፈጥሩ ኃላፊም ሆነ አመራር ተጠያቂ የሚሆኑበት መንገድ መፈጠር እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሰላም መደፍረስ ለምን እንደሚከሰት ማብራሪያ የሰጡት ፕሮፌሰር ካሳሁን ጉረማ፤ በአሁን ወቅት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሰላም መደፍረስ እየተባባሰ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ ደግሞ ንብረት መውደምና የሰው ህይወት መጥፋቱን ጠቁመዋል፡፡ በንጉሡ ዘመን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ብጥብጥ ሲነሳ ‹‹መሬት ለኢትዮጵያ ገበሬ›› በሚል መንፈስ እንደነበር ያስታወሱት ፕሮፌሰር ካሳሁን፤ በአሁን ወቅት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ብጥብጥ ሲነሳ ጎሳና ብሄር ላይ ያተኮሩ ልዩነቶች ላይ በመሆኑ ከፍተኛ ችግር የሚያስከትል እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ኃላፊዎችና መምህራን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የብጥብጥ አራጋቢ በመሆናቸው ተማሪዎች ወደማይቆም ብጥብጥ እንዲገቡ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡ በተቋማቱ አካባቢ የሚታየው የፓርቲዎች አባል ያለገደብ መመልመል ዋነኛ የግጭት ምንጭ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 6/2011
በመርድ ክፍሉ