– የኮሪዶር ልማቱ ከተማዋን ተጨማሪ ውበት እያጎናጸፋት መሆኑም ተገልጿል
ጎንደር፦ የጎንደር ከተማን የመጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት እየተሠራ ነው ሲል የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ። በከተማዋ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ለከተማው ተጨማሪ ውበት ከመስጠት ባለፈ፤ የከተማዋን ፕላን ለማስተካከል እና ከተሜነትን ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና መጫወቱን ገለጸ ።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው የከተማዋን ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንዳስታወቁት፤ በጎንደር ከተማ ከፍተኛ የሆነውን የመጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።
የጎንደር ከተማ የውሃ ችግር ሳይፈታ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ቻላቸው፤ በየጊዜው ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሰው የሕዝብ ቁጥር መጨመር ችግሩን ያባባሰው መሆኑን አመልክተዋል።
ከፀጥታ ስጋት ጋር ተያይዞ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በአፋጣኝ ሠርቶ ወደ ሥራ ማስገባት እንዳልተቻለ ያመለከቱት ከንቲባው፤ ከዚህ የተነሳም የከተማዋ ነዋሪ በሦስት ሳምንት ወይም በወር አንዴ ውሃ የሚገኝበት ሁኔታ መፈጠሩን ገልፀዋል።
የአንገረብ የመጠጥ ውሃ ግድብ የአገልግሎት ጊዜው ተጠናቆ በደለል በመሞላቱ በበቂ ሁኔታ ግልጋሎት እየሰጠ አይደለም ያሉት ከንቲባው፤ በመገጭ ግድብ በየዓመቱ ማኅበረሰቡ ተስፋ ቢያደርግም፤ በጎርፍ እየተወሰደ የሕዝቡ ተስፉ ሲጨልም ቆይቷል ብለዋል።
የመገጭ ግድብን በሚቀጥለው ዓመት አጠናቆ ለማስመረቅ 24 ሰዓት በፀጥታ ኃይሎች በማስጠበቅ ሥራው እየተሠራ የሚገኝ መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባው፤ አሁን ላይ ግድቡ እስከ 40 ሜትር ውሃ መያዙን አስታውቀዋል።
እንደ አቶ ቻላቸው መግለጫ፤ የመገጭ ግድብ 82 ሚሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ የሚይዝ ሲሆን፤ ከዛ ውስጥ ለጎንደር ከተማ አስተዳደር እና ለአካባቢው ለመጠጥ አገልግሎት የሚውለው 32 ሚሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ ነው።
የከተማዋን የውሃ ችግር ከመፍታት አኳያ የሳራባ ግድብ ፕሮጀክት ጥልቅ ተስፋ የተጣለበት መሆኑን አመልክተው። ግድቡን ለመገንባት ፕሮጀክት ተቀርጾ ለገንዘብ ሚኒስቴር መላኩን፤ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ምላሽ እየተጠበቀ እንደሚገኝም አመልክተዋል
የጎንደር ከተማ ጥንታዊ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የከተማውን ፕላን ለማስተካከል ችግር እንደነበር አመልክተው፤ የኮሪዶር ልማቱ ለከተማው ውበት ከመስጠት ባለፈ፤ የከተማዋን ፕላን ለማስተካከል እና ከተሜነትን ለማረጋገጥ ትልቂ ሚና መጫወቱን አስታውቀዋል። የሥራ ባህልን እየቀየረ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በኮሪዶር ልማቱ የከተማው ሕዝብ አካባቢውን በማስዋብ፤ ቀለም በማስቀባት እና በሌሎች ሥራዎች አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልፀው፤ በልማቱ የመጀመሪያው ዙር አንድ ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር መንገድ መገንባቱን ጠቁመዋል። አሁን ላይ ሁለተናው ዙር የ15 ኪሎ ሜትር የኮሪዶር ልማት ሥራ መጀመሩን፤ መስከረም ወር 2018 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።
የኮሪዶር ልማት የሥራ ባህልን የቀየረ፤ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠረ ነው ያሉት ከንቲባው፤ በዚህም በዘንድሮው ዓመት በከተማው ከተፈጠረው 46ሺህ የሥራ ዕድል ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የኮሪዶር ልማቱ እንደሆነም ገልፀዋል።
በከተማው በኮሪዶር ልማቱ ለተነሱ ሱቆች በ311 ሚሊዮን ብር አዘዞ ከተማ አካባቢ ሱቅ እየተገነባ ነው፤ የግንባታ ሥራውም 80 በመቶ መድረሱን አስታውቀዋል ።
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም