
ባሕር ዳር:- በሀገሪቱ ለፍትሕ አገልግሎት ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የዳኝነት ተቋማትን የማዘመን ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምሕረት ገለጹ። በግልጽ ችሎት የመዳኘት፣ ተደራሽ፣ ቀልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ወጥነት እና ጥራት ያለው ውጤታማ የዳኝነት አገልግሎት ማግኘት የዜጎች መብት እንደሆነም ተጠቆመ።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምቹ የሥራ ከባቢ የሚፈጥሩ የሕንፃ እድሳትና የዳኝነት ዲጂታላይዜሽን ፕሮጀክቶችን ትናንት ባስመረቀበት ወቅት አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት እንደገለፁት፤ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ ፍርድ ቤቶች የሕግ እና የሥርዓት መስፈን ማረጋገጫ ሆነው እያገለገሉ ነው።
የነፃነት መከበር፣ የማኅበራዊ ሥርዓት መጠበቅ፣ የኢኮኖሚ እድገት፣ የፍትሕ ሥርዓቱ መስፈን እና የሕግ የበላይነት መረጋገጥ እንዲኖር ነፃ እና ገለልተኛ ፍርድ ቤቶች እንዲኖሩ ግድ ይላል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በኢትዮጵያም ጠንካራ የዳኝነትና የፍትሕ ተቋማት ግንባታ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል ።
ፍርድ ቤቶች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት እንዲወጡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተደረጉ የፍትሕ ዘርፉ ማሻሻያዎች ውጤት እያመጡ መሆኑን አመልክተው፤ ሁሉም ሰዎች በሕግ እንዲገዙ እና ከሕግ በታች እንዲኾኑ፣ በሕግ ፊት እኩል እንዲስተናገዱ፣ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት የሚጠበቅ ነው ብለዋል። ኃላፊነቱን ሊሸከም የሚችል ተቋም እና የሰው ኃይል ግንባታ አስፈላጊ መሆኑንም አመልክተዋል።
ቀሪ ሥራዎችን በዘላቂነት ለመፍታት የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን እቅድ እየተተገበረ መሆኑን አመልክተው፤ ከዚህ አኳያ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በክልሉ የሚታዩ የፍትሕ ችግሮችን የሚፈታና ሀገራዊ ግቦችን የሚያሳካ ለውጥ ማምጣቱን ጠቅሰዋል። ፍርድ ቤቶች የተጣለባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዲችሉ የሁሉንም አካላት ትብብር ወሳኝ ነው ብለዋል።
ፍርድ ቤቶች ያሉባቸውን ጉድለቶች ለመሙላት የማሻሻያ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል፤ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሠራው ሥራ በግልጽ የሚታወቁ ነባር ችግሮችን የሚፈታ ብቻ ሳይሆን ወደሚፈለገው ግብ ለመድረስ ትክክለኛውን መንገድ መያዛችን ማረጋገጫ እንደሆነ አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ የትኛውም ጥግ ለሕዝብ የፍትሕ ጥያቄዎች ሙሉ ለሙሉ ምላሽ ለመስጠት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፤ የተገኙ ውጤቶች ለቀጣይ ሥራ መሠረት ማድረግ ያስፈልጋል። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ለክልሎች የዳኝነት ሥርዓት መሻሻል የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው በበኩላቸው፤ በግልጽ ችሎት የመዳኘት፣ ተደራሽ፣ ቀልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ወጥነት እና ጥራት ያለው ውጤታማ የዳኝነት አገልግሎት ማግኘት የዜጎች መብት ነው። እንዲሁ አይነት ዳኝነት የኅብረተሰቡ የዘወትር መሻት መሆኑን ተናግረዋል።
በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብትን እውን ለማድረግ የችሎት አዳራሾችን ምቹ ማድረግ ይገባል ያሉት አቶ ዓለምአንተ፤ የዳኝነት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የባለጉዳዮችን ርካታ ያረጋገጡ እና በኅብረተሰቡ አመኔታ የተቸራቸው ፍርድ ቤቶችን መገንባት ቀዳሚ ተግባር እንደሆነም አስታውቀዋል።
የመጨረሻ የመብት ማስከበሪያ ለሆነው የዳኝነት አካል ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር ቅንጦት ሳይሆን የዜጎችን በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብት የማክበር እና የማስከበር ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ መሆኑን አስታውሰው፤ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የተከናወኑ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ታችኛው የፍርድ ቤት ድረስ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
የዳኝነት አገልግሎት ሲሰጥባቸው የነበሩ ችሎቶች እና ቢሮዎች ለፍትሕ እና ርትዕ ቀናዒ አመለካከት ላለው ሕዝባችን እና የዳኞችን ክብርን ፈጽመው የማይመጥኑ ነበሩ ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የዳኝነት ሥርዓቱን እና የሕዝብን ክብር የሚመጥን ሥራ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። በአጭር ጊዜ ውስጥ የሕንጻ እድሳት፣ የማስፋፊያ ግንባታ እና የፍርድ ቤቶች ዲጂታላይዝድ የማድረግ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም