
-ፎረሙ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎችን ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ የሚያሳድግ ነው
ጎንደር፦ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም መቋቋም በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የተቋማቱን ዓለም አቀፍ ተፅፅኖ እንደሚያሳድግ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ። ፎረሙ የምርምር ጉባኤዎች፣ የልምድ ልውውጦች፣ የድኅረ ምረቃ ሥልጠናዎችን እና ሀብት በጋራ መጠቀም የሚያስችሉ የትብብር ማሕቀፎችን ለማጠናከር እንደሚረዳ አመለከቱ።
የኢትዮጵያ 10 የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ትናንት በጎንደር ከተማ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ባቋቋሙበት ወቅት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የፎረሙ ሰብሳቢ አሥራት አፀደወይን (ዶ/ር) እንዳስታወቁት ፤ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የተቋማቱን ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ ከፍ እንዲል ዕድል ይፈጥራል።
የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ተብለው በተልዕኮ የተለዩት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ችግር ፈቺ ምርምሮች በማከናወን፣ የማኅበረሰብ ተኮር አገልግሎት በመስጠትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፎች ቀዳሚ እና ላቅ ያለ ተሳትፎ እንዲደርጉ የሚጠበቅ መሆኑን በማንሳት፤ የምርምር ዩኒቨርስቲዎች ፎረም ይህን ዓላማ እውን ለማድረግ እንደሚያስችል ገልፀዋል።
በእነዚህ የግንኙነት መረቦች ውስጥ የሚካተቱ ተቋማት በተለይ በምርምር፣ በድኅረ ምረቃ ፕሮግራም፣ በትምህርት ልማት እና የፈጠራ ማሕቀፎች ላይ የተሰማሩ እንዲሆኑ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ተራማጅ ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎች በመያዝ የኢትዮጵያን የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም መመሥረት በሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ታሪክ ልዩ አጋጣሚ ተደርጎ የሚወሰድ እንደሆነም አመልክተዋል።
የተቋማቱን ደረጃ ለማሳደግ ሀብት የማፈላለግ፣ የኅትመት እና እውቀት ሥርጭት አቅም ማጎልበት፤ በከፍተኛ ትምህርት፣ ሳይንስ እና ፈጠራ ዘርፎች የሚወጡ ብሔራዊ ፖሊሲዎች ላይ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል የምርምር ግብዓት ማቅረብ ፎረሙ የተቋቋመበት ዓላማ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም፤ የምርምር ጉባኤዎች፣ የልምድ ልውውጥ፣ ድኅረ ምረቃ ሥልጠና እና ሀብት በጋራ መጠቀምን ያማከሉ የትብብር ማሕቀፎችን ማጠናከር ፎረም ከሚያስገኝው ፋይዳዎች መካከል የሚጠቀሱ መሆኑን ገልፀዋል።
ከዚህም ባሻገር ያሉትን የምርምር መሠረተ ልማቶች በተለይም የታወቀ ይዞታ ያላቸውን ላብራቶሪዎችና የዲጂታል ዘዴዎችን በጋራ መጠቀም፣ የእውቀት ሽግግር እና ማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎችን በተመለከተ ተቋማቱ ያላቸውን ዘለግ ያሉ ልምዶችና አዳዲስ አሠራሮች ለመለዋወጥ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
የተቀመጡ ዓላማዎችን ማሳካት የሚቻለው ከዚህ በፊት ከተለመደው አስተዳደራዊ በሆኑ ግንኙነቶች ብቻ በመወሰን ሳይሆን፤ ሁለገብ አንድነትና ትብብር በማድረግ መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል። የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም፣ በእንግሊዝ ሀገር የታወቀው የሩሴል ግሩፕ እንዲሁም፤ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የትብብር ፎረም በማቋቋም ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ለሀገር ችግር ፈቺ እና ፈር ቀዳጅ የከፍተኛ ትምህርት ተቋምና ሁለገብ ተዋናይ የሚያደርገውን ምስጉን ዓላማ የያዘ ፎረም ከፍ ባለ ተሳትፎ ማጠናከር፤ እንዲሁም በተደራጀ መልኩ ለተጠቀሱት ዓላማዎች መሳካት መረባረብ ከእያንዳንዱ የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን አሳስበዋል፡
በፎረሙ ሀዋሳ፤ አዲስ አበባ፤ ጎንደር፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ አዳማ፣ ጂማ፣ ባህርዳር፣ አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች ተካተውበታል።
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም