. 8100A አጭር የፅሁፍ መልዕክት 380 ሺ ሰው እንደላከም ተጠቁሟል
አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ የኮሮና ቫይረስ ስጋት እያለም ህብረተሰቡ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ተገለፀ። በ8100A አጭር የፅሁፍ መልዕክት 380 ሺ ሰው እንደላከም ተጠቁሟል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሀይሉ አብርሃም በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ በህዳሴ ግድቡ ግንባታ ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ቢያሳርፍም ፣ህብረተሰቡ በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። ባለፈው ሳምንት
በ8100A አጭር የፅሁፍ መልዕክት 380 ሺ ሰው ልኳል።
እንደ አቶ ሀይሉ ገለፃ፤ ለህዳሴ ግድቡ ቦንድ ሽያጭ በሰባት ወራት ጊዜ ውስጥ 400 ሚሊዮን ብር ማግኘት ተችሏል። አጠቃላይ ግድቡ ከተጀመረ በቦንድ ሽያጭ 13 ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር ተገኝቷል። በቅርቡም የተጀመረው የቦንድ ሳምንት እየተካሄደ ሲሆን፣ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ብዙ ህዝብ እየተሳተፈበት አይደለም፤የተለያዩ ማስታወቂያዎች ግን እየተሰሩ ይገኛሉ።
ህብተረሰቡ ለግድቡ ግንባታ አስተዋፅኦ ለማድረግ የአጭር የፅሁፍ መልዕክት በመጠቀም እና የስጦታና የቦንድ ግዥ የሚከናወንባቸው የባንክ ቁጥሮች እንዲዘጋጁ መደረጉን አስረድተዋል። ህብረተሰቡም
እቤቱ ሆኖ በቦንድ ግዥና በስጦታ እንዲሳተፍ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ተናግረዋል። ህብረተሰቡ ስጦታ ለሚከናወን የባንክ ቁጥር 1000291929609 እንዲሁም ለቦንድ ግዥ ደግሞ 1000291927738 የባንክ ቁጥር መጠቀም እንደሚችል አብራርተዋል።
የዳያስፖራና የባለሀብቱ እንቅስቃሴ ከግድቡ ድርድር በኋላ እየጨመረ መምጣቱን የጠቀሱት አቶ ሀይሉ” በአጠቃላይ እስካሁን ከዳያስፖራው አንድ ቢሊዮን ብር ማግኘት መቻሉን ጠቅሰዋል። ዳያስፖራው ባለበት ቦታ ሆኖ የቦንድ ግዥ በማከናወን ገቢው መገኘቱን ጠቅሰዋል። የኮሮና ቫይረስ ስጋት ቢኖርም ህብረተሰቡ በቻለው አቅም ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2012
መርድ ክፍሉ