ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ወረርሽኝ ሲል የፈረጀው የኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገራችን ከገባ ሁለት ሳምንታትን አስቆጥሯል። በዚህ ጊዜ ውስጥም 16 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። እነዚህ ሰዎች ከውጪ ወደ ሀገር ቤት የገቡ ብቻ ሳይሆን ከሀገር ያልወጡ ሰዎች ጭምር መሆናቸው ተረጋግጧል። ይሄ የሚያሳየው ቫይረሱ በሀገር ውስጥም እየተሰራጨ መሆኑን ነው።
መንግስት የወረርሽኙን አስከፊነት በመገንዘብ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል እና በዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ለማድረግ አስቀድሞ ህዝብን የማስጠንቀቅ፣ የማስተማር እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች አስፈላጊ የሆኑ የዝግጅት ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። ከእነዚህም አንዱ እና ወሳኙ ተግባር ህዝቡ ከመንግስት፣ ከጤና ባለሙያዎች እና ከሀይማኖት አባቶች የሚሰጠውን የጥንቃቄ ትምህርት እና ማሳሰቢያ እንዲተገብር ማድረግ ነው። ሰዎች እጃቸውን በውሃና በሳሙና በተደጋጋሚ ጊዜ በመታጠብ ንጽህናቸውን መጠበቅ፣ የመጨባበጥ የእጅ ሰላምታ ማቆም፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ፣ በአንድ ቦታ ላይ በብዛት እንዳይገኙ ማድረግ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። በትራንስፖርት ላይ የሚኖርን ጭንቅንቅ ለመቀነስም የመንግስት ሰራተኞች በቤታቸው ሆነው ስራቸውን ማከናወን እንዲችሉ መመሪያ ሰጥቷል። ሰዎች የሚሰባሰቡባቸው የመጠጥ፣ የጫት ቤቶች እና ሌሎችም እንዲዘጉ አድርጓል። ይሄ ቅድሚያ የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ነው። ችግሩ ሰፍቶ ከመጣ መቆጣጠር እንደማይቻል ጭምር ከሌሎች የውጪ ሀገራት ከታየው ልምድ በመነሳት ችግሩ ሳይስፋፋ ለመቆጣጠር እንዲቻል የተወሰደ እርምጃ ነው።
ይሁን እንጂ አሁንም በአንዳንድ ቦታዎች በተለይ በገበያ ስፍራ፣ በእምነት ተቋማት፣ የንጽህና መጠበቂያ ይገኝባቸዋል በሚባሉ ማከፋፈያዎች እና በሌሎችም ስፍራዎች የሚታየው የህዝብ ቁጥር ዛሬም ህዝቡ ከመንግስትም ሆነ ከሌላ ቦታዎች የሚወጣውን መመሪያና ማስጠንቀቂያ እያደመጠና እየተገበረ እንዳልሆነ ያሳያል።
ዓለም አቀፍ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ጣሊያን ዛሬ ለደረሰችበት ከፍተኛ የህዝብ እልቂት የተዳረገችው እዚህ ደረጃ ይደርሳል ብላ አስቀድማ የመከላከሉንና ህዝቧን የማስጠንቀቁን ስራ ባለመስሯቷ ነው። ከእነሱ እኩል ችግሩ መኖሩን የተረዱት እንደ ደቡብ ኮሪያ ያሉት ሀገራት ደግሞ ለጉዳዩ ከፍተኛ ክብደት በመስጠታቸው ህዝባቸውም ስለተቀበላቸውና ትዕዛዝና መመሪያዎችን እየተገበሩ በመሆናቸው የከፋ ጉዳት አላስተናገዱም። እኛም የእነዚህን ሀገሮች ተሞክሮ በማየት መማር የሚገባንን መማርና ራሳችንን መጠበቅ ይኖርብናል።
የኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ ከ175 በላይ ሀገራትን አዳርሷል። ከግማሽ ሚሊየን በላይ ህዝብ አጥቅቷል። ከ 26 ሺህ በላይ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት ዳርጓል። ዛሬም የበሽታው ስርጭት እየተስፋፋ እና ዓለምን እያዳረሰ እንጂ እየተገታ አይደለም። ዛሬም የሰዎች ህይወት እያለፈ ነው። ስለዚህ ሁላችንም ልንጠነቀቅና ከመንግስትም ሆነ ጉዳዩ ከሚመለከተው አካል የሚሰጡ መመሪያዎችን ልንተገብር ይገባል። ዛሬም ነገም የራሳችንን ንጽህና፣ ማህበራዊ ርቀታችንን በመጠበቅ ከኮሮና ቫይረስ ራሳችንን መከላከል ይኖርብናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ እግሮቻችንን በመሰብሰብና በጣም አስፈላጊ ላልሆኑ ጉዳዮች ከቤት ባለመውጣት የራሳችንና የማህበረሰቡን ደህንነት መጠበቅ አለብን።
አሁንም የኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ ክትባትም ሆነ መከላከያ መድሐኒት ያልተገኘለት ወረርሽኝ መሆኑን በመገንዘብ አስፈላጊ የሆነውን ጥንቃቄ ሁሉ ማድረግ ከሁላችንም ይጠበቃል። ዛሬም የቫይረሱን ስርጭት መከላከያው ብቸኛውና ብቸኛው መንገድ ከመንግስት እና ከጤና ሚኒስቴር የሚወጡ ትዕዛዛትን ያለማወላወልና ያለመሸራረፍ ማክበር ነው።
በተለያዩ ወገኖች የሚሰነዘሩ የማዘናጊያ ቃላትን ወደ ጎን በማድረግ ለህይወታችን ዋጋ መስጠት አለብን። ይሄ ቀን ዛሬ ነው። አሁን በቸልተኝነት እንደዋዛ የምናልፈው ነገ ዋጋ ያስከፍላል። ስለዚህ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎችን መተግበር የሁላችንም ሀላፊነትና ግዴታ ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 ቀን 2012 ዓ.ም