አዲስ አበባ፡- የኮሮና ወረርሽኝ በሚያደርሰው ጫና የሚፈጠረውን የገበያ አለመረጋጋት ተጽዕኖ ለመቋቋም የህብረት ስራ ማህበራት በግንባር ቀደምትነት እንደሚሰሩ የፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአገራችን የሚስፋፋ ከሆነ በገበያ ላይ የሚከሰተውን እጥረት እና የዋጋ ንረት ለመቋቋም እንዲቻል የህብረት ስራ ማህበራት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወኑ ናቸው።
‹‹የህብረት ስራ ማህበራቱ ገበያን የማረጋጋት አቅም ያላቸውና ከገጠር እስከ ከተማ የተደራጁ ናቸው›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በሰው ኃይል፣ በሎጂስቲክስና በፋይናንስ ቀላል የማይባል አቅም ስላላቸው ችግሩን በግንባር ቀደምትነት ለመቅርፍ እንደሚረባረቡ ገልጸዋል። ጤናማ ያልሆነውን የአገራችንን ገበያ ወደ ጤናው እንዲመለስም ያደርጋሉ።
የኮሮና ቫይረስ ወደ አገራችን መግባቱን ተከትሎ የተፈጠረውን የገበያ ውዥንብር ለማረጋጋት የህብረት ስራ ማህበራቱ የግብርና ምርቶችንና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ለህዝቡ በማቅረብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። የተዛባውን ገበያም ለማስተካከል የከተማና የገጠር ህብረት ስራ ማህበራት የፈጠሩትን ትስስር በመጠቀም ችግሩን ለመፍታት ቀጣይነት ባለው መልኩ እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በሀገሪቱ የሚታየውን የዋጋ ንረት ለማስተካከል ማህበራቱ የነበራቸውንና አሁንም እያስገቡት ያለውን ምርት ቀደም ሲል በነበረው ዋጋ እያቀረቡ ነው። የህብረት ስራ ማህበራት የተቋቋሙት በህዝብ የሚሰሩትም ለህዝብ መሆኑን ያነሱት አቶ ኡስማን አሁንም በህዝብ ላይ በገበያ አለመረጋጋት ጉዳት እንዳይደርስ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት እየሰሩ ነው።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት የኮሮና ቫይረስ ዓለም አቀፍ ችግርና የሁሉንም ትብብር የሚጠይቅ በመሆኑ ህብረተሰቡም ከተቋማቱ ጋር መተባበር አለበት። የህብረት ስራ ማህበራት ዋና ዓላማ የሰው ልጆች በጋራ የራሳቸውንና የአካባቢያቸውን ችግር መፍታት ነው። በመሆኑም የኮሮና ቫይረስ ሁሉንም የሚያጠቃ መሆኑን በመረዳት እጅ በእጅ በመያያዝ በጋራ ችግሩን መቋቋም አለብን ብለዋል።
ኤጀንሲው ቀደም ሲል ማህበራቱ ገበያ እንዲያገኙ፣ እሴት ጨምረው ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ፣ የስራ ዕድል እንዲፈጥሩና ቁጠባን በማሰባሰብ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ማድረጉን አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 ቀን 2012 ዓ.ም
አጎናፍር ገዛኸኝ