ግብጽ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌትና አተገባበርን አስታካ የውሃ ክፍፍልን በውል በማሰር ቁማር መጫወት እንደምትፈልግ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ቡድን አባላት ይገልጻሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ቡድን አባል ዶክተር ይልማ ስለሺ፤ ግብጾች በህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትና አተገባበር ላይ የጎላ ጉዳት እንደማይደርስባቸው ጠንቅቀው እንደሚያውቁ ይናገራሉ። ነገር ግን የህዳሴ ግድቡን አስታከው ታሪካዊ የውሃ ተጠቃሚነታቸውን በውል በማሰር ቁማር ለመጫወት እየጣሩ ናቸው።
ዶክተር ይልማ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ግድቡን በሦስት ዓመት መሙላት ትችላለች። ሆኖም ግን በታችኞቹ አገራት ላይ የጎላ ተጽዕኖ እንዳይደርስ በማሰብ ከአራት እስከ ስድስት ዓመታት ለመሙላት ትብብሯን አሳይታለች። ግድቡ ሲሞላም በዓመት ከሚፈሰው 50 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ 13 በመቶ ብቻ ለመያዝ ሃሳብ አቅርባለች። ይህ በሌሎች አገራት ከሚፈሰው ውሃ እስከ 50 በመቶ ከሚይዙ አገራት ጋር ሲነጻጸር እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው። ግብጾች ግን የኢትዮጵያን ተባባሪነትና ቅንነት ወደ ጎን በመተው የግድቡን ውሃ ሙሌትና አተገባበር በማስታከክ የአባይን የውሃ ክፍፍል ስምምነት በማድረግ ታሪካዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማስቀጠል ሴራ እየሰሩ ነው።
‹‹ግብጾች ኢትዮጵያ ቋሚ የውሃ አለቃቀቅ ስምምነት ውል እንድትፈርም ይፈልጋሉ። ኢትዮጵያ ቋሚ የውሃ አለቃቀቅ ከተስማማች የውሃ ክፍፍል አደረገች ማለት ነው›› ብለው ስለ ስምምነቱ ምንነት በዝርዝር የሚናገሩት ምሁሩ፤ ይህ ማለት ወደ ግብጽ የሚሄደው ውሃ ከጎደለ ኢትዮጵያን ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ያጠራቀመችውን ውሃ እንድትለቅ የሚያስገድድ ነው። ከግድቡ በኋላም ሌሎች የልማት ስራዎች እንዳትሰራ የሚያግድ መሆኑን ይገልፃሉ።
በአሜሪካኖች የተዘጋጀውን ሰነድ ግብጽ ተቀብላ ፈርማለች፤ ኢትዮጵያም እንድትፈርም ጫና እየተደረገባት ነው የሚሉት ዶክተር ይልማ፤ ሰነዱን እነሱ ፍትሃዊ ነው ቢሉም በግልፅ በድረ ገጽ ይፋ አድርገው የዓለም ህዝብ እንዲፈርድ ማድረግ እንዳልቻሉ ይገልፃሉ። ይህ ቢደረግ ኢ ፍትሃዊ ስምምነት መሆኑን የዓለም ህዝብ ይፈርድ ነበር በማለትም እውነታውን ለማሳየት ይሞክራሉ። የግብጾች ሴራ በማምታታት የውሃ ክፍፍል ማድረግ ነው። ይህ ሁሉም የተፋሰሱ አገራት ባልተሳተፉበት ያለድርድር እንደማይሆን ተነግሯቸዋል። አዋጪው መንገድ በፍትሃዊ መንገድ መጓዝ እንደሆነም አመላክተዋል።
ሌላኛው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የኢትዮጵያ የሳይንቲፊክ ቡድን መሪና ተደራዳሪ ዶክተር በለጠ ብርሃኑ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ግድቡን ስትሞላ ለታችኞቹ አገራት ከ35 እስከ 37 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ በዓመት ለመልቀቅ ሃሳብ አቅርባለች። ይህም ግድቡ እስኪሞላ በዓመት የምትይዘው የውሃ መጠን 10 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ነው። ኢትዮጵያ ያቀረበችው ሃሳብ ምክንያታዊ እና ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች በታችኞቹ አገራት ጉዳት እንደማያደርስም ያረጋገጡት መሆኑን ያመለክታሉ።
‹‹ግብጾች ለማሳካት የሚጥሩት የቅኝ ግዛት ዘመን ታሪካዊ የውሃ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ነው። ህልማቸውን ለማሳካት ኢትዮጵያ በዓመት 40 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ እንድትለቅ ነው›› የሚሉት የሳይንቲፊክ ቡድን መሪው፤ የአስዋን ግድብ ከ 165 ሜትር በታች እንዳይቀንስ፤ ከቀነሰም ከተጠራቀመው የህዳሴ ግድብ እንድትለቅ ስምምነት እንዲደረግ እንደሚፈልጉ ይናገራሉ። የህዳሴ ግድብም ከ15 እስከ 20 ዓመታት እንዲሞላ እንደሚጠይቁ ይገልፃሉ። ኢትዮጵያ በዚህ ላይ ከተስማማች በቀጣይ በምታካሂዳቸው ልማቶች ላይ ተጽዕኖ የሚያደርግ መሆኑንም ይናገራሉ።
ዶክተር በለጠ እንደሚሉት፤ በግድቡ አሞላል ላይ በተለያየ ጊዜ ስምምነት ቢደረግም ግብጽ ታሪካዊ የውሃ ተጠቃሚነቷን ስላላሳካች አፋርሳለች። ግድቡን ሰበብ አድርጋ የቅኝ ግዛት የውሃ ክፍፍልን የማስረገጥ አላማ ነው ያላት። ኢትዮጵያ ይህን አይነት ስምምነት እንደማታደርግም ይገልፃሉ። ዛሬም ሆነ ነገ ይሄ አላማቸው እንደማይሳካ ተገንዘበው ወደ ፍትሃዊ የተጠቃሚነት ድርድር መምጣት እንዳለባቸው ይመክራሉ።
እንደ ቡድን መሪው ገለፃ፤ በሦስቱ አገራት መካከል ድርድር መካሄድ ያለበት የግድቡ አሞላል ላይ ብቻ ነው። የውሃ ክፍፍልን በተመለከተ የሚደረገው ድርድር በናይል የትብብር ማዕቀፍ ከሁሉም የተፋሰሱ አገራት ጋር ነው። ግብጽ አሜሪካ ሄዳ ፍላጎቷን ለማሳካት ብትጥርም አይሳካላትም። ኢትዮጵያ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ግድቧን ከመሙላት የሚያቆማትም ሃይል የለም።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ዓለም አቀፍ የውሃ ሀብት ምህንድስና አማካሪው ዶክተር አድማሱ ገበየሁ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ፍላጎት ግድቧን ለመሙላት ከሚፈሰው ውሃ በአማካይ አንድ አስረኛውን መውሰድ ነው።
ይህም በታችኞቹ አገራት ላይ የሚያደርሰውም ተጽዕኖ የለም። የግብጽ ፖለቲካዊ ሸፍጥ ግን ድርድሩ በምክንያታዊነትና በፍትሃዊነት ተካሂዶ ፍፃሜ እንዳያገኝ ማድረግ ነው።
‹‹ኢትዮጵያ ከአባይ ወንዝ ጥቅም አላገኘችም›› የሚሉት ምሁሩ አሁን ላይ የአገሪቱ ችግር እየፈጠጠ በመምጣቱ የመልማት ፍላጎቷ ማደጉን ይገልፃሉ። በወንዙ ተጠቃሚነታችንን ለማረጋገጥም ተቋማዊ አሰራር በመዘርጋት ምርምሮችንና ጥናቶችን በማካሄድ በመገናኛ ብዙሃን በኩልም አጀንዳ በመቅረጽ የግብጽን አድሏዊ አካሄድ ለመመከት መሰራት አለበት ብለዋል። ግድቡ የተወሰነ ውሃ እስኪይዝ ግብጽ ጫጫታ መፍጠሯ እንደማይቀር አንስተውም ኢትዮጵያ ግድቡን አጠናቃ ቶሎ ወደ ልማት ማስገባት አለባት ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከዛሬ ዘጠኝ ዓመት በፊት ሲጀመር የታችኞቹ የተፋሰሱ አገራት ግብፅና ሱዳን ግድቡ ተፅዕኖ እንደሚያሳድርባቸው ቅሬታ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው። ሆኖም የኢትዮጵያ መንግስት ግድቡ የጎላ ተፅዕኖ እንደማያሳድር ሲያስረዳ ቆይቷል። ዓለም አቀፍ ተቋማትና ከሦስቱ አገራት በተውጣጡ ባለሙያዎች የተቋቋመው የቴክኒክ ኮሚቴም ጥናት አድርጓል። በውጤቱም ጉልህ ተፅዕኖ እንደማያደርስ ማረጋገጡም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ሱዳን በኢትዮጵያ መንግስት ማብራሪያና በጋራ የቴክኒክ ቡድኑ የቀረበውን የጥናት ውጤት ብትቀበልም ግብፅ የተለያዩ ምክንያቶች በመደርደር ከስምምነት ላለመድረስ ስታንገራግር ቆይታለች።
ምሁራኑ በቀጣይም በውሃ የተሳሰሩ አገራት ተለያይተው እንደማይለያዩ አንስተዋል። ኢትዮጵያም በተፋሰሱ አገራት መካከል ፍትሃዊ የውሃ ክፍፍል እንዲኖር በትብብር መስራቷን መቀጠል እንዳለባትም ገልፀዋል። የታላቁ የህዳሴ ግድብ አሞላልም ከተንኮል በጸዳ እንዲሁም ምክንያታዊ በሆነ አጠቃቀም መቀጠል እንዳለበትም መክረዋል። ግብጽም አማራጭ ስታጣ ከተንኮል ወጥታ ወደ ፍትሃዊ ድርድር መምጣቷ እንደማይቀር ተንብየዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 ቀን 2012 ዓ.ም
አጎናፍር ገዛኽኝ