የቀድሞው የፖርቹጋል ጠቅላይ ሚኒስትር የዛሬው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሰሞኑን የጦርነቶች ሁሉ ጦርነት የሆነውን የኖቭል ኮሮናቫይረስ (ኮቪድ19) በተባበረ፣ በፈረጠመ ክንድ መከላከል ይቻል ዘንድ ዓለምአቀፍ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ለመላው ዓለም ጥሪ አድርገዋል። ተኩስ አቁሙ ያስፈለገው እውነተኛውንና የሰው ልጆች ሁሉ ጠላት የሆነውንና ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዝነውን ትንቅንቅና የጨበጣ ፍልሚያ በድል ለመወጣት ነው። ሌሎች ጦርነቶች በገዥዎች ግትር አቋም፣ ስውር ጥቅም እና ፍላጎት በሀገርና በሕዝብ ስም የሚካሄዱ የውክልና (ፕሮክሲ) ጦርነቶች እንጂ እውነተኛ ጦርነቶች አለመሆናቸውን ዋና ጸሐፊው በሾርኔ ነግረውናል። እውነተኛው ጦርነት በማንም ስህተት የማይቀሰቀስ እናት ተፈጥሮ የምታውጅብን እንደ መሬት መንቀጥቀጥ፣ ሱናሚ፣ ኃይለኛ ውሽንፍር (ሀሪኬን) ፣ እሳተ ገሞራ፣ ከባድ አውሎ ንፋስ (ቶርኔዶ) እና ወረርሽኝ ነው። ተኩስ አቁም ከጠብ መንጃም ሆነ ከማንኛውም የጦር መሣሪያ አፈሙዝ የሚወጣ አረርን ጥይትን ብቻ የሚመለከት አይደለም ።
ከመደበኛውም ሆነ ከማህበራዊ ሚዲያው የሚተኮሰውን የፍርሀት፣ የጥላቻን፣ የልዩነት፣ የቂም፣ የደባ ፣ የሴራ ፣ የውዥንብር፣ የአሉባልታ፣ የሀሰት፣ የመረጃ ወረርሽኝ (ኢንፎዴሚክ) እሩምታ ጭምር እንጂ ። ወረርሽኙን ፖለቲካዊ ግዳይ መጣያ፣ ነጥብ ማስቆጠሪያ፣ መራጭ ማማለያ ለማድረግ የሚከወን ስውር ወይም ይፋ ትንቅንቅና ግብግብንም ያካትታል ። ጉቴሬዝ እኒህን ሰው ሰራሽ ከፍ ሲልም ጊዜአዊና ሀሰተኛ ጦርነቶችን በተኩስ አቁም አቆይተን ዋናውን በሰው ልጅ ህልውና ላይ የተደቀነውን ጦርነት በአንድነት እንፋለመው ሲሉ ነው ጥሪ ያስተላለፉት። ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከ70 ዓመታት በላይ ዓለምን ዋልታና ማገር ሆነው ያቆሟትን፣ ገድግደው የያዟትን ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን)፣ እንደ የተባበሩት መንግሥታት ፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)፣ የቡድን 20፣ የቡድን 7፣ የአስያን፣ ብሪክስ ፣ ወዘተ ተቋማት በሕዝበኝነት (ፖፑሊዝም)፣ በተነጣይነት፣ በአክራሪ ብሔርተኝነት፣ አሜሪካ በታሪክ አጋጣሚ በተፈጠረ ኢኮኖሚያዊ የበላይነትና የጦር ልዕለ ኃያልነት የተጎናጸፈችውን ዓለምአቀፍ የመሪነት እርካብ በቀኝ አክራሪውና አወዛጋቢው ዶናልድ ትራምፕ «አሜሪካ ትቅደም ! » ስሁት ወለፈንዲ መርህ ከሦስት ዓመታት ወዲህ በፈቃዷ ስለለቀቀች በዓለማችን የመሪነት ክፍተት ተፈጥሯል። ክፍተቱን በአየር ንብረትና በአካባቢ ጥበቃ፣ በኒውክሌር የጦር መሣሪያ፣ በዓለምአቀፍ ሽብርተኝነት እና በዓለምአቀፍ ነፃ የንግድ ሥርዓት ስምምነቶች መክሸፍ ተመልክተናል። ዛሬ ደግሞ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚደረገውን ዓለምአቀፍ ጥረት አስተባብሮ አቀናጅቶ የሚመራ ኃይል ባለመኖሩ የተፈጠረው ክፍተት ዓለማችንን ውድ ዋጋ እያስከፈላት ነው። በባራክ ኦባማ ዘመን ሳርስ፣ ኢቦላንና ሌሎች ወረርሽኞችን ለመከላከል አሜሪካ ዓለምአቀፉ ማህበረሰብን፣ ምዕራባውያንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን አስተባብራ በመምራቷ በአጭር ጊዜ ውጤታማ መሆን ችላ ነበር። ዛሬ ዕድሜ ለትራምፕ አሜሪካ ወረርሽኙን ለመከላከል ዓለምአቀፍ ጥረቱን ማስተባበር አይደለም የየግዛቶቿን ጥረት በቅጡ ማቀናጀት ተሰኗት ማጣፊያው አጥሯታል።
ይህን መጣጥፍ እየጫጫርሁ በአሜሪካ ወደ 70ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ወደ 1ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ሕይወታቸው አልፏል። የወረርሽኙ ዋና መናኸሪያ ነጥብ (ኤፒሴንተር) በሆነችው ኒውዮርክ በየሦስት ቀኑ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ ያሻቅባል። ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያግዙ ቁሳቁሶችና መድኃኒቶች እጥረት በሁሉም ግዛቶች እየተስተዋለ ነው። በዓለማችን ወደ 500ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ የሞቱት ደግሞ ከ22ሺህ በላይ ደርሷል። በአንድ ሳምንት ብቻ ከ3ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ አሜሪካውያን ወረርሽኙን ተከትሎ የሥራ ፈላጊ ሆነዋል።
ሁሉን ነገር ፖለቲካዊ መሣሪያ፣ የምርጫ መቀስቀሻ ማድረግ የሚቀናው ትራምፕ ወረርሽኙን ለመከላከል ያደረገው ጥረት ደካማ መሆኑ ሲተች ዴሞክራቶች የሩሲያ ምርመራ እና ሥልጣንን አላግባብ የመጠቀም ክስ አልሳካ ቢላቸው አሁን ደግሞ በ2020 ምርጫ እንዳላሸንፍ በኮሮናቫይረስ ስም እየቀሰቀሱብኝ እንጂ ወረርሽኙስ እንዲህ የሚያሳስብ አይደለም በማለት ቢያቃልለውም ዛሬ ዙሪያው ገደል ሆኖበታል። ቀኝ ዘመም ሚዲያዎችም በፎክስ ኒውስ ፊታውራሪነት ከእሱ ጋር ወረርሽኙን ሲያናንቁት እንዳል ኖሩ ዛሬ ተመልሰው ስለወረርሽኙ ዋና ለፋፊ ሆነዋል።
በዓለማችን አሜሪካ በትራምፕ ስሁት አይዶሎጂ የተነሳ የመሪነት ሚናዋን መወጣት ባለመቻሏ። ቻይናም ከወረርሽኙ የዞረ ድምር (ሀንጎቨር) በቅጡ ባለማገገሟ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችል ዓለምአቀፍ ጥረት እያስተዋልን አይደለም። ወረርሽኙን ለመከላከል የተመሰረተው ፋና ወጊና አንድ ለእናቱ ትብብር በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አነሳሽነትና በአሊባባው የቻይና ቁጥር አንድ ቢሊየነር ጃክ ማ ድጋፍ የተቋቋመው ግብረ ሰናይ ድርጅት ይጠቀሳል። በዚህ አርዓያነት ባለው ትብብር 100 ቶን የአፍንጫ ተአፍ መሸፈኛና መከላከያ አልባሳት በኢትዮጵያ አጋፋሪነት ለ53 የአፍሪካ ሀገራት እየተከፋፈለ ይገኛል። ለዚህ ነው የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርን «በአህጉሩ ወረርሽኙን ለመከላከል እየሰጠኸው ያለውን በሳል አመራር እና ያሳየኸውን ተነሳሽነት አደንቃለሁ። የዐቢይ- ጃክ ማ ድርጅት (ፋውንዴሽን ) ኮቪድ 19 ለመከላከል የሚያግዙ የምርመራ መሣሪያዎችን ፣ የአፍንጫ ተአፍ መሸፈኛዎችን እና የመከላከያ አልባሳትን ስለለገሰ አመሰግናለሁ ።» ሲሉ የምስጋና ደብዳቤ በመጻፍ እውቅና የሰጡት። በዚህ ፈታኝ ወቅት ወረርሽኙን ለመከላከል ከሚያስፈልገው ሀብት በላይ የተዋጣለት አመራር ይጠይቃል። ለዚህ ነው በአሜሪካ፣ በጣሊያንና ስፔን ወረርሽኙ እያስከተለ ያለው የከፋ ጉዳት አንዱ መንስኤ የመሪ እንደ ንስር አርቆ አለማየት፣ አቅላይነት ፣ አቀናጅቶ የመምራት ልምሻ፣ ዳተኝነት፣ ዉልዉል ፣ ወዘተ ተደርጎ የተወሰደው ።
ኮቪድ 19 እያጠቃ፣ እያሸበረ፣ ኑሮአችንን እያመሰቃቀለ፣ ነፃነታችን፣ ተስፋችንን፣ ራእያችን እየሸራረፈ፣ ማህበራዊ መስተጋብራችንን በአዲስ እየበየነ ያለው፣ ያለ ልዩነት በሰው ልጅነታችን ነው። ልናስቆመው፣ ልንገታው የምንችለው እንደ ሰው በአንድነት ቆመን ስንመክተው ነው። ወረርሽኙ ቀኝ አክራሪ፣ ሦስተኛ አማራጭ ፣ ግራ ዘመም ፣ ለዘብተኛ ፣ ሕዝበኛ ፣ ሶሻሊስት፣ ካፒታሊስት አይለይም። አይመርጥም ። ሊበራል ፣ ኒዎ ሊበራል ፣ ዴሞክራት ፣ ሶሻል ዲሞክራት ፣ ሪፐብሊካን እያለ በአይዶሎጂ አይከፋፍልም ። ቀራጭ ፣ ፀሐፍት ፣ አይሁድ ፣ ግሪክ ግብፅ ፣ እስራኤል ፣ ሙሴ ፣ ፈርኦን እያለ አያሰልፍም። ጥቁር ፣ ነጭ ፣ ቢጫ ፣ እስፓኒክ ፣ ነባር ፣ መጤ በሚል መርጦ ለይቶ አያጠቃም ። ከቆዳህ ቀለም ጉዳይ የለውም። ክርስቲያን ፣ እስላም ፣ ሽያ ፣ ሱኒ ፣ ሒንዱ፣ ቡድሀ ፣ ሽንዙ ፣ ኮንፊሺየስ በማለት ከሃይማኖትህ ጋር ጠብ የለውም። ምዕራባውያን ፣ አሜሪካ ፣ ዓለምአቀፉ ኅብረተሰብ ፣ ቅብርጥሴ ፣ ምንአምን የሚል ዝርዝርም የለውም ።
የኖቨል ኮሮናቫይረስ አማራ፣ ትግሬ ፣ ኦሮሞ ፣ አፋር፣ ሶማሌ ፣ ጋምቤላ ፣ ጉምዝ ፣ ወላይታ ፣ ጌዲዎ ፣ ሀድያ፣ ወዘተ የሚል ፋይል የለውም። ኮቪድ19 ብልፅግና፣ ኢዜማ፣ አብን ፣ እነግ ፣ ኦብነግ ፣ አረና፣ ትህነግ ፣ ፌደራሊስት ፣ አህዳዊስት ፣ ጎጠኛ፣ ትምክተኛ ፣ ገንጣይ ፣ አስገንጣይ ፣ ቁሞ ቀር ፣ ተቸካይ ፣ አጎንባሽ ፣ ጨለምተኛ ወዘተ የሚል ጥቁር መዝገብ የለውም። ሴት፣ ወንድ ፣ ብላቴና ፣ ጎልማሳ ፣ መበልት ፣ ሽማግሌ ፣ አሮጌ ፣ ወዘተ የሚል መደብም የለውም ። ኮቪድ19 የሞት ፈረሱን ሽምጥ እየጋለበ፣ ጦሩን እየሰበቀ፣ ዘገሩን እየነቀነቀ ከቻይናዋ ዉሃን ታኅሣሥ መጨረሻ ላይ ተነስቶ ከአንታርቲካ ውጪ ሁሉን አህጉራት ያዳረሰው ሕዝበ አዳምን ያለልዩነት በማርገፍ ነው። የመጣው በሁላችን በሰው ልጆች ላይ ነው። የጦር ዕቃችንን ጥሩራችን ለብሰን፣ የራስ ቁራችንን ደፍተን የምንጋፈጠው ሰው በመሆን ነው። ከሰውነት ልዕልና ባለመጉደል። ውሃ ልካችንን በመጠበቅ። ትራምፕ የ «ቻይና ቫይረስ» ያለው ጊዜ ስቷል። ከሰውነት ሙላት ጎድሏል። በዚህ ፈታኝ ፣ ክፉ ቀን በጎሳ ፣ በሃይማኖት፣ በጎጥ፣ በቀዬ፣ ከተከፋፈልን ከኢትዮጵያዊነት ጽዋ ጎድለናል። ለኮቪድ19 እጅ ሰጥተናል። ይሄን ክፉ ቀን ተጋግዞ ፣ እጅ ለእጅ ተያይዞ ፣ አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ተባብሎ ማለፍ ሲገባን የሀብት ማካበቻ ካደረግነው ከሰውነት ተራ ወጥተናል። 20 ብር ይሸጥ የነበረን አፍንጫ ተአፍ መከለያ በ20 እጥፍ 400 ብር ሲሸጥ፣ 100 ብር ይሸጥ የነበረ ነጭ ሽንኩርትን 250 ብር ሲልህ፣ ገና ክፉ ቀን መጥቷል ብሎ ትናንት ምሽት ያየኸውን ሸቀጣሸቀጥ ዛሬ ማለዳ መደርደሪያውን ባዶ አድርጎ ስታገኘው ሰውነቱን፣ ኢትዮጵያዊነቱን ብትጠራጠር አይፈረድብህም ። ይፈረድበታል እንጂ። ከወዲህ እንደ ጋዜጠኛ ቤተልሔም ጥጋቡ ያሉ የሰውነት ልኬቶች በትርፍ ጊዜአቸው ጭምብል ሰፍተው በነፃ ውሰድ ሲሉህ፣ በዚህ በኩል ቤታቸውን ለቀው ለለይቶ ማቆያ ይዋል ብለው ሲሰጡ፣ ኦል ማርት ዋጋ ሳይጨምር ከማገልገል አልፎ 100ሺህ ብር ሲለግስ በወገንህ እንዳላፈርህ ፣ እንዳልተሸማቀቅህ መልሰህ ትፅናናለህ። አንተ ዓይንህን ለአፈር ተባብለህ መሽገህ ገድበህ እየተጠባበቅህ እያለ ጃክ ማ ውቅያኖስ ተሻግሮ ሲደርስልህ በራስህ ከማፈር ውጪ ምን አማራጭ አለህ ። ተጸጽተህ በማንነቱ ያገለልኸውን ወገንህን ለመደገፍ ብትነሳ ግን ትድናለህ ።
የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ተማፅኖ በአንድም በሌላ በኩል የሰውን ልጅ ወደ ሙላቱ ወደ ከፍታው የመመለስ የንኡድ ጥሪ አካል ነው ። «የቫይረሱ አስከፊነት የጦርነትን ከንቱነት ያሳያል። ለዚህ ነው በመላው ዓለም የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ የማደርገው። አፈ ሙዝን በመዘቅዘቅ ፣ የባሩድ ሽታን በማስወገድ በአንድነት ወረርሽኙን መከላከል ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ።» የተኩስ አቁሙ በሶሪያ ፣ በአፍጋኒስታን፣ በሊቢያ፣ በፍልስጤም፣ በዩክሬን፣ በየመን፣ በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን ፣ ” በዴሞክራሲያዊ ” ኮንጎ ፣ በካሜሩን፣ በናይጀሪያያ፣ ወዘተ ረጂ ድርጅቶች ያለስጋት ለሆስፒታሎች ለዜጎች ድጋፍ በማድረግ የሰዎችን ሕይወት ለመታደግ ያስችላቸዋል ።
ጉቴሬዝ ለሰው ልጆች ሁሉ በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በማንዳሪን፣ በአረበኛ፣ በስፓኒሽ ፣ በስዋሂሊ፣ ወዘተ ባስተላለፉት ጥሪ «ዓለም ኮቪድ19 የተሰኘ የጋራ ጠላት ተነስቶበታል። ቫይረሱ ዜግነት፣ ጎሳ፣ ሃይማኖት ሳይለይ ሁሉን ያጠቃል። ይሁንና ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞች፣ ተፈናቃዮች ፣ አረጋውያን፣ የተገለሉ ሰዎች ላይ ይበረታል። ጦርነት ባወደማቸው ሀገራት ደግሞ የጤና ተቋማት ስለፈራረሱ የሕክምና ባለሙያዎች በበቂ ሁኔታ ስለሌሉ የወረርሽኙ ጉዳት የከፋ ይሆናል።»
ዋና ጸሐፊው በማስከተልም «ተዋጊ ኃይሎች ጠባጫሪነትን አቁመው፣ አለመተማመንንና ለግጭት መፈላለግን ትተው፣ ተኩስን እና የአየር ጥቃትን በማስቀረት ሕይወትን ለማዳን የሚያግዝ እርዳታ ለማድረስ መተላለፊያ መንገድ (ኮሪደር) ሊከፍቱ ይገባል። እግረመንገድም ተቀራርቦ ለመነጋገር ለመወያየት መልካም አጋጣሚ መፍጠር ይቻላል። በግጭት ቀጣናዎች ለሚኖሩ ዜጎችም ተስፋን የሚያለመልሙ እና ቫይረሱን ለመከላከል የሚያግዙ ድጋፎች ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ተጻራሪ ኃይሎች ለትብብርና ለንግግር ዕድል ፈንታ በመስጠት በመሀላቸው ያለውን ልዩነት በማጥበብ ወረርሽኙን ለመከላከል ተጨማሪ አቅም መሆን ይጠበቅባቸዋል። አሁኑኑ በየትኛውም የዓለማችን ማዕዘን የሚገኙ ግጭቶች ጦርነቶች ቆመው ። ፊታችንን የሰው ልጅ የጋራ ጠላት ወደሆነው ኮቪድ19 ማዞር አለብን ። »
እንደ መውጫ
በ1911 ዓ.ም በሀገራችን በተከሰተው ስፓኒሽ ፍሉ (የኅዳር በሽታ) 40ሺህ ወገኖቻችን አልቀዋል። ከዚህ ከፍ ያሉ በጸና ታመው ድነዋል። እንደ የኔታ ወልደጊዮርጊስ ያሉ የቁርጥ ቀን ሰዎች መኖር የወረርሽኙን ጉዳት በእጅጉ ቀንሶታል። የኔታ ለሕይወታቸው ሳይሰስቱ ጎሳ ሃይማኖት ሳይለዩ በሰፈራቸው በጉለሌ በየቤቱ እየዞሩ ለበሽተኞችና ለገመምተኞች እንጀራና ውሃ በማደል የብዙዎችን ሕይወት መታደጋቸውን ፤ ሙሴ ሴደርኩይስት የተባሉ ስዊድናዊ ሚስዮናዊ አስተማሪ በየሰፈሩ እየዞሩ ለበሽተኞች እህልና ውሃ መድኃኒት በመስጠት ትሩፋት መስራታቸውን ከጥቂት ቀናት በኋላ በዚሁ በሽታ ታመሙና ሞተው ጉለሌ መቀበራቸውን ፤ «የሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ » ደራሲ መርስኤ ኀዘን ወ/ቂርቆስ ሰንደው አቆይተውናል።
ዛሬም በሀገራችን የኮቪድ19ን ወረርሽኝ ለመከላከል በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ ቅን እና ደጋግ ሰዎች ለሕይወታቸው ሳይሰጉ ፣ ለሀብት ገንዘባቸው ሳይሰስቱ አርዓያነት ያለው ተግባር በማከናወን ባለፉት ሦስት ዓመታት ካሳለፍነው የጥላቻ፣ የልዩነት፣ የቁርሾ ሀንጎቨር እንድናገግም ማስታገሻ ሆነውናል። በዜጋችን በሀገራችን መልሰን ተስፋ እንድንሰንቅ ከወረርሽኙ አድማስ ፣ ከአሜን ባሻገር እንድንመለከት ዓይናችንን ከፍተውልናል። ውለታቸውንም ትውልድ ሲዘክረው ይኖራል።
ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ ! አሜን ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 / 2012
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com