ዓባይ ለግብጽ የኃይል ምንጭ ሲሆን ለኢትዮጵያ ደግሞ የጥበብ ምንጭ ነው። ዓባይ ‹‹ከኢትዮጵያና ከግብጽ ማንን ታውቃለህ?›› ተብሎ ቢጠየቅ ‹‹ኢትዮጵያን›› ማለቱ አይቀርም። ምሁራን አንድ የሚሉት ነገር አለ። ይሄውም፤ ግብጽ ውስጥ ከህፃን እስከ አዋቂ፣ ከአርሶ አደር እስከ ወታደር ያውቁታል የሚል ነው። እንዲያውቁት ደግሞ ስለዓባይ በሰፊው ይሰበካሉ። በሥርዓተ ትምህርታቸው ውስጥ ይካተታል፤ መገናኛ ብዙኃኖቻቸው ይደጋግሙታል፤ አለፍ ሲልም ለፖለቲካ ፍጆታ ይጠቀሙታል። ይህን የሚሉ ምሁራን በተቃራኒው ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ትኩረት እንዳልተሰጠው ይናገራሉ። አዎ! እውነት ነው ትኩረት አልተሰጠውም።
ግን፤ እውነት ዓባይ ከግብጽ በላይ ኢትዮጵያ ውስጥ አልተዘመረለትም? አዎ! ዓባይ ከግብጽ በላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ተዘምሮለታል፤ ተነግሮለታል፤ ተዘፍኖለታል። ልዩነቱ ብዙም ምርምር አይጠይቅም፤ ግብጽ ውስጥ በስብከት ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በተፈጥሮ ነው። ዓባይ ለግብጽ ህልውና የሆነው በፖለቲከኞች ስብከት ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ከህዝቡ ጋር በተፈጠረ ባህልና ማንነት ነው። ዓባይ ለኢትዮጵያ ማንነት ነው።
ዓባይ የኢትዮጵያ ማንነትና ምንነት ለመሆኑ ደግሞ ምስክሮቻችን ስነ ቃሎች ናቸው። የባህል ጥናትና የስነ ጽሑፍ ባለሙያዎች እንደሚሉት ደግሞ ስነ ቃል የአንድ ማህበረሰብ ምንነት ነው። ምክንያቱም ስነ ቃል በመንግስት ትዕዛዝ ወይም በአንድ ወገን ጫና የሚፈጠር ሳይሆን ማህበረሰባዊ ስነ ልቦና የሚገለጽበት ነው። ህዝብ ብሶቱንና ደስታውን የሚገልጽበት ነው። እነዚህ የስሜት መግለጫ የሆኑ የስነ ቃል ሀብቶች ደግሞ የሚፈጠሩት ከሚታየው ነባራዊ ሁኔታ ነው። ለዚህም ነው የአንድ ማህበረሰብ ታሪክ ሲጠና ትውፊቱ መነሻ የሚሆነው።
እንግዲህ ዓባይ የኢትዮጵያውያን ማንነትና ምንነት ባይሆን ኖሮ ስነ ቃሎቻችን እንዲህ በዓባይ አይጥለቀለቁም ነበር ማለት ነው። በተረትና ምሳሌዎቻችን ውስጥ ዓባይ አለ፤ የደስታና የኀዘን እንጉርጉሮዎቻችን ውስጥ ዓባይ አለ፣ በባህል ዘፈኖቻችን ውስጥ ዓባይ አለ፣ በስም አወጣጣችን ውስጥ ዓባይ አለ… ዓባይ በብዙ ነገሮቻችን ውስጥ አለ።
ተረትና ምሳሌዎቻችን፣ እንጉርጉሮዎቻችን ሁሉ የሚያሳዩት የዓባይን ግዙፍነት ነው። በሌላ በኩል የዓባይን አስቸጋሪነትና አደገኛነትም የሚያመለክቱ ናቸው። ከግብጽ ጋር ያለን ልዩነትም እዚህ ላይ ይመስላል። ግብጾች የሚዘምሩለት በጠቃሚነቱና በህይወትነቱ ብቻ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በአስቸጋሪነቱም ተዘምሮለታል። ይሄውም በክረምት ወራት የዓባይ ወዲያ ማዶና የዓባይ ወዲህ ማዶ ሰዎችን ስለማያገናኝ ነው። ያኔ በዘመኑ ድልድይ የሚባል ነገር ስለማይታወቅ በዋና እና በእግር በመሻገር ብቻ ስለነበር ስለአስቸጋሪነቱ ተዘፍኖለታል። አብዛኞቹ ተረትና ምሳሌዎች፣ እንጉርጉሮዎች ግን ስለግዙፍነቱ ነው።
ከተረትና ምሳሌዎቻችን ውስጥ፤ ዓባይን ያላየ ምንጭ ያመሰግናል፣ ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል፣ ዓባይ ቢሞላ ተሻገር በሌላ፣ ዓባይ አንተ አየኸኝ ከደረት እኔም አየሁህ ከጉልበት፣ ዓባይና ስንቅ እያደር ይቀላል፣ ዓባይን በጭልፋ፣ የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው፣ የሰው ቤት ዓባዩ… የሚመሳሰሉት ይጠቀሳሉ። አብዛኞቹ ግዙፍነቱን የሚገልጹ ሲሆኑ አንዳንዶቹም ተጓዥነቱንና አስቸጋሪነቱን የሚገልጹ ናቸው። ዓባይን ያላየ ምንጭ ያመሰግናል የሚባለው አንድ ሰው ትንሽ ነገር ሲያደንቅ ነው፤ ከዚህም የበለጠ አለ ለማለት ነው። ለምሳሌ የአንዲት የወረዳ ከተማን ህዝብ ብዛት ለሚያደንቅ ሰው እነ አዲስ አበባን ለመግለጽ ‹‹ዓባይን ያላየ ምንጭ ያመሰግናል›› ሊባል ይችላል። የዓባይ ግዙፍነት ሌሎች ነገሮችን ለመግለጽ እንደ ማንፀሪያ ያገለግላል ማለት ነው። ዋና ዓላማችን ተረትና ምሳሌዎቹን ማብራራት ስላልሆነ እንደየ ዓውዳቸው እንጠቀማቸዋለን።
አሁን ከተረትና ምሳሌዎች (ምሳሌያዊ ንግግሮች) ወደ ቃል ግጥሞች እንሂድ። የቃል ግጥሞች በጣም ብዙ ናቸው። በተለይም በባህል ዘፈኖች ውስጥ ይደጋገማሉ። የባህል ዘፈኖች ሲባል በካሴት የወጡትን ሳይሆን እረኞችና ገበሬዎች የሚዘፍኑትን ለማለት ነው። ዓባይ ኢትዮጵያ ውስጥም ከእረኛ ጀምሮ እንደሚታወቅ የምናውቀውም በእነዚህ የስነ ቃል ዘፈኖቹ ነው። ለምሳሌ የፍቅር ዘፈኖችን እንይ።
በድሮው ጊዜ ዓባይን መሻገር የሚቻለው በበጋ ወቅት ውሃው በመጠኑም ቢሆን ሲቀንስ ብቻ ነበር። እንደ ዛሬው ድልድይ የለም፣ መኪና የለም። አንድ ከዓባይ ወዲህ ማዶ ያለ ኮበሌ ከዓባይ ወዲያ ማዶ ያለች ጉብል ካፈቀረ መገናኘቱ ከባድ ነበር። የሚገናኙት የበጋ ወቅት ጠብቀው ነው። የፍቅረኛው ናፍቆት ሲጠናበት በማሽላ ይመስላታል። እንዲህም ሲል ያንጉራጉራል።
ዓባይ ወዲያ ማዶ ማሽላ ዘርቼ
ወፎች ጠረጠሩት መሻገሪያ አጥቼ
‹‹ወፎች‹‹ ተብለው የተገለጹት ፍቅረኛውን የሚነኩበትን ሌሎች ወንዶች ነው። በዚህ ቅኔ ለበስ ግጥም ውስጥ ብሶቱን ይገልጻል። ከዓባይ ወዲያ ማዶ አፍቅሬ ማግኘት አልቻልኩም ማለቱ ነው። ባስ ሲልበት ደግሞ እንዲህ በማለት ፈጣሪን ይማጸናል።
አንቺ ወዲያ ማዶ እኔ ወዲህ ማዶ
አንገናኝም ወይ ተራራው ተንዶ?
እንግዲህ ተራራ ተብሎ የተገለጸው የዓባይ ውሃ ነው። የያኔው አፍቃሬ ፀሎት ሰምሮ እነሆ ዛሬ ተራራው ተንዷል። ከዓባይ ወዲህ ማዶ ያለ አፍቃሪ ከዓባይ ወዲያ ማዶ ያለች ፍቅረኛው እንዲህ ህልም አትሆንበትም። ያ የከለከለው ተራራ በዓባይ ድልድይ ተንዷል። በፈለገው ቀን ሄዶ ፍቅረኛውን ማግኘት ይችላል።
የዓባይ ውሃ ክረምቱን ሙሉ እንዲህ ሰውን ያቆራርጥ ነበር። መገናኘት የሚቻለው በበጋ ወቅት ነው። ፍቅሩ ብሶበት የበጋ ወቅት የሚጠባበቀው አፍቃሪ እንዲህ ሲል ተስፋ በቆረጠ አንጀት ይዘፍናል።
ዓባይ ጉደል ብለው አለኝ በታህሣሥ
የማን ሆድ ይችላል እስከዚያ ድረስ?
ታህሳስ የበጋ ወቅት የመጀመሪያው ወር ነው። ይሄን የበጋ ወቅት መጠበቅ ያልቻለ ያለው አማራጭ በዋና መሻገር ነው። በእርግጥ ይህ የሚሆነው ደግሞ ዋና ለሚችል ሰው ነው። ዋና የሚችለው ደግሞ እንዲህ ሲል ይዘፍናል።
እስኪ ልሻገረው ዓባይን በዋና
የጎጃም ልጅ ወዶ ምን እንቅልፍ አለና!
ዓባይ ውሃው ብቻ ሳይሆን ከእርሱ ጋር የተያያዙ ነገሮችም እንዲሁ አስቸጋሪዎች መሆናቸውን በስነቃሎቻችን ተገልጸው እናገኛቸዋለን። ወደ ወንዙ የሚያስገቡ መንገዶች ሁሉ ዳገትና ገደል ናቸው። በዋና እንኳን ለመሻገር ብዙ አስቸጋሪ መንገዶችን ሄዶ ነው። የወንዝ ዳር መንገዶች እንደሌላው ምቹ አይደሉም። ወደ ወንዙ ሲወርድ ቁልቁለት አለ፤ ከተሻገረ በኋላ ደግሞ አቀበት (ዳገት) አለ። ቁልቁል ሲወርድ እሷን ለማግኘት ነውና ይጨንቀዋል (በዚያ ላይ የውሃው ስጋት አለ) ከተሻገረ በኋላ ደግሞ በችኮላ አቀበቱን ይወጣዋል። ይህኔ እንዲህ እያለ ይዘፍናል።
ዓባይ ቁልቁለቱን እምባዬ እያነቀኝ
ዓባይ አቀበቱን ላብ እያጠመቀኝ
መቅረትስ አልቀርም እስከዚያው ጨነቀኝ።
የዓባይ ውሃ መሙላት አንዳንዴ ደግሞ ጥሩ አጋጣሚም ይፈጥራል። ይህ የሚሆነው ከዓባይ ወዲያ ማዶ ያለችዋ ተፈቃሪ አፍቃሪዋ ጋ ወዲህ ማዶ እንደመጣች ውሃው ከሞላ ነው። ምክንያቱም ተመልሳ አትሄድምና። ይህን አጋጣሚ ሲያገኝ
ዓባይ ሞላ አሉ ሞላ አሉ
እንደ ዕድሌ ሁሉ
እያለ ይዘፍናል። አንዳንዱ ደግሞ እንዲህ በማለት ቀጭን ትዕዛዝ ይሰጣል።
ዓባይ ቢሞላ ቢሞላ
ዞረሽ ነይ በሌላ!
በእርግጥ እሷን ብቻ ሳይሆን ለራሱም እንዲህ ብሏል።
ዓባይ ሞላ ብየ ሞላ ብየ
አልቀርም ሸግየ
አንዳንዱ ደግሞ ትንቢት ይገለጥለታል። የዓባይ መሙላት እንዲህ አስቸጋሪ ሆኖ አይቀርም ያለ አፍቃሪ እንዲህ ብሎ ነበር።
ዓባይም ቢሞላ ቢሞላ
አለው አሉ መላ
የዚህ ትንቢት ፈጣሪ መላው ምን እንደሆነ አልነገረንም፤ ‹‹አለው አሉ መላ›› ብሏል። እነሆ መላው ተገኝቶ ዛሬ የዓባይ መሙላት ፍቅረኞችን መለያየት አልቻለም። ሰውየው የተናገረው ነገር ምናልባትም ድልድይ ሊሰራ እንደሚችል ተገልጦለት ነበር ማለት ነው።
የስነ ቃል ዘፈኖችና ምሳሌያዊ አነጋገሮቻችን ብዙ ጥልቅ ሃሳብ ያላቸው ናቸው። ዓባይ ከኢትዮጵያውያን ጋር ያለውን ባህላዊና ታሪካዊ ትውፊት የሚያሳዩ ናቸው። የዓባይንና የኢትዮጵያን ህዝብ ስነ ልቦናዊ ትስስር ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ ናቸው።
ዓባይ የጥንት ኢትዮጵያውያን መኩሪያ ብቻ አይደለም። ዓባይ ለዚህ ትውልድም ገናና ማንነት ነው። ይሄ ትውልድም ገናና አሻራውን ያሳረፈበት ነው። ይሄ ትውልድም የተጠበበበት ነው። ስለዓባይ ያልዘፈነ የለም፤ ያልተቀኘ የለም፣ ያልገጠመ የለም፣ ያልሳለ የለም፣ ያልተወነ የለም! ዓባይ ለብዙ ከያኒያን የጥበብ ምንጭ ሆኗል። ለዛሬው ዘፋኞችን ብቻ እናያለን። የሁለት ዘፋኞችን ስንኞች መልዕክት እንያቸው።
በ2003 ዓ.ም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ሲጣል ከዜናው እኩል ተሰምቷል። ስለህዳሴው ግድብ የሚሰሩ ፕሮግራሞች ሁሉ ማጀቢያ ነበር። የድምጻዊት ገነት ማስረሻ ‹‹ዓባይ ጭስ አልባው ነዳጅ›› የተሰኘው ዘፈን አሁን ድረስ የሬዲዮና የቴሌቪዥን የፕሮግራሞች ማጀቢያ ነው። ከዚያ ወዲህ ስለህዳሴው ግድብ ብዙዎች ቢዘፍኑም ቀዳሚ በመሆኑ ይመስላል ይደጋገማል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ስንኞቹ ጥልቅ መልዕክት አላቸው። እስኪ ጥቂቶችን እንያቸው።
አደባልቆት ሲሄድ ጥቁር እና ነጩን
ግዮን አበሻ ነው ማን ይነካል ምንጩን!
ዓባይ አንተ እያለህ ታላቁ ወንዛችን
መሳለቂያ አንሆንም በድህነታችን።
አዎ! ዓባይን የሚያህል ግዙፍ ሀብት ይዘን መሳለቂያ ሆነናል። ለመዝገበ ቃላት የድህነት ትርጉም መፍቻ ሆነናል። ይሄ ሁሉ ሲሆን ከኢትዮጵያ ተነስቶ የኢትዮጵያን ጋራና ሸንተረር አቆራርጦ፣ የኢትዮጵያን አፈር እያደባለቀ የሚሄድ ነው።
ዘመን ቢያስታርቀን ከዓባይ ብንስማማ
ይዘን ተጠጋነው አካፋና ዶማ
ዓባይ ለዘመናት ለቀረርቶና ለፉከራ የግጥም ምንጭ ብቻ ሆኖ ኖሯል። እነሆ 2003 ዓ.ም ላይ ግን ታሪክ ተቀየረ። አካፋና ዶማ ይዘን ተጠጋነው።
ማደሪያ ሳይኖረው ግንድ ይዞ ይዞራል
የሚባለው ተረት ከእንግዲህ ይቀራል
እንዲህ እንደ ዛሬው መልካም ቀን ሲመጣ
ግንድም ይዘህ አትዞር ማደሪያም አታጣ።
አዎ! ተረት እውን ሆነ። ‹‹ዓባይ ማደሪያ የለውም ግንድ ይዞ ይዞራል›› የሚለው ተረትና ምሳሌ ራሱ ተረት ሆነ። ዓባይ ማደሪያ አገኘ፤ ሥራው ግንድ ይዞ መዞር ሳይሆን ኃይል ማመንጨት ሊሆን ነው።
ዓባይ እኔና አንተ ሳይሉን ቸር ሆነን
ፎከሩብን እንጂ ማን አመሰገነን!
በራሳችን ውሃ በራሳችን አፈር
ተዘባበቱብን ተመጠጠ ከንፈር!
ዓባይ ለዘመናት ለኢትዮጵያ ምንም ሳይጠቅማት ግብጽንና ቅኝ ገዥ አገራትን ሲያወዳጅ ኖሯል። ግብጽን አበልጽጓል። ኢትዮጵያ ግን አልተመሰገነችም፤ እንዲያውም መሳለቂያና መዘባበቻ አደረጓት። በራሷ ውሃና አፈር መሳለቂያ ሆነች፤ በሌለችበት እንደፈለጋቸው ይፈራረሙበታል፤ ይወዳጁበታል። አቅም የላትም፣ አትገነባውም የሚል ንቀት መሆኑ ነው።
ስንት ዘመን ቁጭት ስንት ዘመን ግጭት
ስንት ዓመት በጣሳ ስንት ዓመት በወጪት!
ፍሰስበትና በሀገርህ ሜዳ
የሚቆጣም ካለ ያበጠው ይፈንዳ!
አሁን ተረቱም ፉከራውም ይበቃል፤ ‹‹ዓባይን በጭልፋ፣ ዓባይን በወጪት…›› የሚሉ ተረትና ምሳሌዎች ወደ እውን ይቀየሩ። እነሆ ዓባይ ይገደብ እንደማለት ነው፤ ‹‹አትገድቡም›› የሚል ካለም ኢትዮጵያውያን ያውቁበታል ለማለት ነው።
መቼም የዓባይ ነገር ከተነሳ ከወንዙ እኩል ስመ ገናና የሆነችው ድምጻዊት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) በሁላችንም ልብ ውስጥ ናት። አንድ ለሙዚቃ ምንም ቅርበት የሌለው ሰው ‹‹እስኪ የአንድ ዘፋኝ ስም ተናገር›› ቢባል ‹‹ጂጂ›› ማለቱ አይቀርም። ጂጂ ከዓድዋ እና ከዓባይ እኩል ስሟ ይነሳል፤ ምክንያቱም ዓድዋንም ዓባይንም በብዙዎች ልብ ውስጥ እንዲሰርጹ አድርጋለች። መዝፈን ቢሉ ዝም ብሎ መዝፈን ሳይሆን ልብን ሰርስረው በሚገቡ ጥልቅ ስንኞች በመቀኘት ነው።
ጂጂ ለዓባይ የዘፈነችው ሊገደብ ነው ሲባል አይደለም፤ ማንም ባላሰበበት ወቅት ነው። እውነተኛ ጥበብም እንዲህ ነው፤ ቀድሞ ይተነብያል፤ የሌሎችን አይንና ልብ ይከፍታል። ጂጂ ዓባይን እንዲህ ስትለው ኖራለች።
የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና
የማይደርቅ የማይነጥፍ ከዘመን የፀና
ከጥንት ከፅንስ አዳም ገና በፍጥረት
የፈሰሰ ውሃ ቀድሞ ከገነት
ጂጂ የዓባይን ታሪካዊና ጥንታዊነት ነው የነገረችን። ዓባይ የማያረጅ ውበት መሆኑ ደግሞ ቀደም ሲል ያየናቸው የማህበረሰቡን ስነ ልቦና የሚገልጹ ስነ ቃሎችም ይነግሩናል። ከሰው ልጅ ፍጥረት ጋር ያለውን ቁርኝትና የሥልጣኔ አስጀማሪነቱን ትነግረናለች። ‹‹ግርማ ሞገስ የአገር ፀጋ የአገር ልብስ›› እያለች የዓባይና የኢትዮጵያን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ አንድነት ትነግረናለች።
ዓባይ
የበረሃ ሲሳይ
ብነካው ተነኩ! አንቀጠቀጣቸው
መሆንህን ሳላውቅ ስጋና ደማቸው!
ይሄ እንግዲህ የአሁኑን ወቅታዊ ሁኔታ እንኳን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ዓባይ ለግብጻውያን ስጋና ደማቸው ነው፤ ሲነካ ያንቀጠቅጣቸዋል። ለዚህም ነው በመገናኛ ብዙኃኖቻቸው የውሸት ዜና ሳይቀር የሚያሰራጩት። ግብጽ ከኢትዮጵያ በላይ በወቅታዊው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተጠቅታለች፤ ዳሩ ግን ከዓባይ ፕሮፖጋንዳ ዝንፍ አላሉም። እንዲህ አይነቱን እውነታ ነው የጂጂ ስንኞች የሚነግሩን።
የሚበሉት ውሃ የሚጠጡት ውሃ
ዓባይ ለጋሲ ነው በዚያ በበረሃ
ልብ በሉ እነዚህን ስንኞች! የሚበሉት ውሃ፤ የሚጠጡት ውሃ። አዎ! እንዲህ ላወቁበት ውሃ የሚጠጣ ብቻ ሳይሆን የሚበላም ነው። ውሃን የምናውቀው እንደሚጠጣ ነው፤ በልማድ ውሃ ይበላል አንልም፤ በሳይንሳዊ ጥበብ ግን ውሃ ይበላል። ልክ እንደ ግብጽ ላወቀበት ልማት ነው፤ ምግብ ነው። ‹‹ውሃ እንዴት ይበላል?›› ሳይንሳዊ ማብራሪያ የሚያስፈልገው አይመስለኝም!
ዓባይ ዓባይ
ዓባይ ወንዛወንዙ
ብዙ ነው መዘዙ!
አዎ! የዓባይ ጉዳይ የባለቤቶች ብቻ አልሆነም። ከአውሮፓ እስከ እስያ፣ ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ እጃቸውን አስገብተውበታል። አገራት ተጣልተውበታል፤ ተወዳጅተውበታል። በዓለም አደባባይ ስሙ የተነሳባቸው አጋጣሚዎች ብቻ ናቸው። ዓባይ ጓዙም መዘዙም ብዙ ነው።
ዓባይ የወንዝ ውሃ አትሆን እንደሰው!
ተራብን ተጠማን ተቸገርን ብለው
አንተ ወራጅ ውሃ ቢጠሩህ አትሰማ
ምን አስቀምጠሃል ከግብፆች ከተማ?
ዓባይ ሰው አይደለም፤ እንዳደረጉት ይሆናል። ከገደቡት ይገደባል። በዚህ የጂጂ ስንኝ ውስጥ እንደ ሰው ታናግረዋለች። መልዕክቱ የሚነግረን ግን እኛም እንደ ግብጾች ማድረግ እንዳለብን ነው።
እጅጋየሁ ሽባባውም ሆነች ሌሎች ከያኒያን ዓባይን በጥበባቸው ገልጸዋል። ከእነዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የእረኞችና የገበሬዎች እንጉርጉሮዎች ቀድመው ዓባይን ተረድተውታል። ከዚህ የምንረዳው ዓባይ ግብጽ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥም ሕይወት እንደነበር ነው። ከዚህ በኋላ ዓባይ የጥበብ ብቻ ሳይሆን የኃይልም ምንጭ ይሆናል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 / 2012
ዋለልኝ አየለ