አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢኮኖሚው፣ በድርጅቶች ቀጣይነትና ህልውና እንዲሁም በሰራተኞች ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ ይረዳል የተባለ የስራ ቦታ ምላሽ የሶስትዮሽ ፕሮቶኮል ይፋ ተደረገ።
የስራ ቦታ ምላሽ የሶስትዮሽ ፕሮቶኮሉን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን በጋራ ይፋ አድርገውታል።
በወቅቱ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደገለጹት፤ ፕሮቶኮሉ ህጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ እንዲቻል ከወረርሽኙ ጉዳት አኳያ ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ በመንግስት፣ በአሰሪ እና ሰራተኛው እየታዩ የሚወሰዱ አቅጣጫዎችን ይዟል። ወረርሽኙን በአስተማማኝ መልኩ ለመከላከል እና በድርጅቶችና በሰራተኛው ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን ለመቀነስ ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው።
እንደ ዶክተር ኤርጎጌ ገለጻ፤ ቀውስን የመቋቋም ችሎታ እና ምላሽ አቅም ከድርጅት ድርጅት እንዲሁም ከዘርፍ ዘርፍ የሚለያይ በመሆኑ መፍትሄዎች ከየድርጅቶች እንዲመነጩ በማድረግ በፕሮቶኮሉ የቀረቡ ምክረሃሳቦችን አሰሪውና ሰራተኛው የጋራ እንዲያደርጉት ይጠበቃል። በዚህም ደረጃ በደረጃ ሊወሰዱ ከሚገባቸው ህጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች መካከል ያልተቋጩ አዲስ የህብረት ስምምነት ድርድሮች ለሚቀጥሉት 12 ወራት እንዲቋረጡ የሚል ተካቷል። ተግባራዊ ያልተደረገ የደመወዝ ጭማሪ ለሚቀጥሉት 12 ወራት ተግባራዊ እንዳይደረግ የሚል አቅጣጫ በፕሮቶኮሉ ተቀምጧል።
እንደ ሚኒስትሯ ከሆነ፤ በተጨማሪ ሰራተኞች ያልተጠቀሙበት የዓመት ዕረፍታቸውን እንዲጠቀሙ ማድረግ እና እረፍታቸውን ተጠቅመው የጨረሱ ካሉ ከቀጣይ ዓመታት የእረፍት ጊዜ ቢያንስ ግማሹን እየተጠቀሙ በክፍያ እንዲቆዩ የሚለው ተካቷል። እንደየተቋማቱ የኪሳራ ሁኔታ የሚለያይ ሆኖ እና የችግሩ መጠን እየታየ ተግባራዊ ሲደረጉ የነበሩ የተለያዩ አበሎች፣ ጉርሻ እና ኮሚሽን እንዲሁም እንደደመወዝ የማይቆጠሩ ክፍያዎች ችግሩ ሙሉ በሙሉ እስኪቀረፍ እንዳይፈጸሙ ቢደረግ የሚል ሃሳብም ፕሮቶኮሉ አካቷል። እጅግ አስፈላጊ ባልሆኑ የድርጅት ስራዎች ላይ የተሰማሩ ሰራተኞች ለጊዜው የተወሰነ ብድር በመስጠት ሁኔታዎች ሲሻሻሉ ወደስራ እንዲመለሱ የጽሁፍ ማረጋገጫ መስጠት እንደሚገባ በፕሮቶኮሉ ሰፍሯል።
ፕሮቶኮሉ በአሰሪዎች ሊወሰዱ የሚገቡ ጥንቃቄዎችን መያዙን የገለጹት ዶክተር ኤርጎጌ፤ የአፍና የአፍንጫ ማስክ ማቅረብ እና ስለአጠቃቀሙ ግንዛቤ ማስያዝ፣ በድርጅቱ ሃላፊ የሚመራና ሰራተኞች አባል የሚሆንበት የኮና ቫይረስ ቁጥጥርን የሚመራና የሚከታተል ኮሚቴ ማቋቋም እንዲሁም የሰራተኞችን የጥግግት ሁኔታ ማስቀረት እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል። ሰራተኞች በበኩላቸው ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው በማስታወስ፣ የሴፍቲ ኦፊሰሮች በስራ ቦታዎች እየተንቀሳቀሱ ለኮሮና ቫይረስ የሚያጋልጡ ሁኔታዎችን እየተከታተሉ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባቸው በፕሮቶኮሉ መካተቱን አስረድተዋል። በፕሮቶኮሉ የቀረቡ ሃሳቦች በእያንዳንዱ ድርጅት እንደየሁኔታው የሚወሰን መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሯ፣ ፕሮቶኮሉ ከአንድ ሰው በላይ ለቀጠሩ ድርጅቶች በሙሉ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አሰሪዎች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው፣ ከጥንቃቄ እርምጃዎች ባሻገር አብዛኛዎቹ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች ተብለው የሰፈሩትን ጉዳዮች ኪሳራ ባጋጠማቸው ድርጅቶች ላይ እንጂ ትርፋማ የሆኑትን እንደማያካትት ገልጸዋል። በቀጣይም እንደየችግሩ መጠን እና ሁኔታ ደረጃ በደረጃ መንግስት፣ ሰራተኛ እና አሰሪዎችን ባካተተ መልኩ የፕሮቶኮሉ ይዘት ሊስተካከል እንደሚችልም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ታደለ ይመር በበኩላቸው ከችግሩ ለመውጣት አሰሪውም ሆነ ሰራተኛውም ሳይጎዳ ለመጓዝ ፕሮቶኮሉ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። በሌላ በኩል ግን ያላስፈላጊ ጥቅም ለማጋበስ የሚሰሩ ነጋዴዎችም ሱቃቸውን መዝጋት ብቻ ሳይሆን በአደባባይ ተጋልጠው ለፍርድ ሊቀርቡ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ዓለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት የቀውስ ጊዜ አስተዳደርን ምላሽ በተመለከተ ባሰፈረው መመሪያ መሰረት በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሳቢያ የስራ ሁኔታ ጉዳት ሲደርስበት በቀውስ ለተጎዱ ሰራተኞች መሰረታዊ ገቢያቸው እንዳይቋረጥ ማገዝ ይገባል።
አዲስ ዘመን መጋቢት19/2012
ጌትነት ተስፋማርያም