ዓለማችን ከባድ ጭንቅ ውስጥ ገብታለች። በየደቂቃው የሚሰማው ዜና ሁሉ በጎነት የለውም። ሞት የሚመዘገብባቸው ሀገራት ቁጥር አሁንም ማሻቀቡን ቀጥሏል። መነሻውን ከሀገረ ቻይና አድርጎ መላውን ዓለም ማዳረስ የያዘው የኮሮና ቫይረሰ (ኮቪድ 19) ስርጭት ዛሬም አላንቀላፋም። ሺዎችን ለሞት እየመለመለ ሌሎች ሺዎችን ለከፋ ሕመም መዳረጉን ቀጥሏል።
እነሆ! ዛሬ የዓለም ሕዝቦች በራሳቸው ላይ በር ዘግተው ይቀመጡ ዘንድ ግድ ሆኗል። አዎ! ማንም የማንንም ጩኸት ሰምቶ የሚደርስበት ዘመን አልሆነም። «እዚህም ቤት እሳት አለ» እንዲሉ ሁሉም ስለራሱ እያሰበ በነገዋ ጀንበር በሕይወት አድሮ ለመነሳት በተስፋ መጠበቁን ይዟል። ዛሬም ግን በርካታ ጆሮዎች ይህን ለመስማት የፈቀዱ አይመስልም። ጉዳዩ የጥቂቶች ይመስል መዘናጋትና ግድየለሽነት ከራስ ወዳድነት ጋር ተበራክቷል።
ታክሲ ውስጥ ነኝ። ወደ ፒያሳ የሚያመራውን ሚኒባስ ይዤ ከሾፌሩ ጀርባ ካለው ወንበር ተቀምጫለሁ። እኔን ጨምሮ ሌሎች ተሳፋሪዎች የታክሲውን መነሳት እየጠበቅን ነው። ዞር ብዬ ዙሪያ ገባውን ቃኘሁ። ወንበሮቹ በሙሉ በተሳፋሪዎች ተይዘዋል። ረዳቱ ግን አሁንም መጣራቱን ቀጥሏል። ከነበሩት መሀል አንዳንዶቹ ሾፌሩ እንዲንቀሳቀስ እየወተወቱ ነው።
በታክሲው የተከፈተው ሬዲዮ ስለሰሞንኛው የኮሮና ቫይረስ እያወራ የየሀገራቱን ሞትና ስጋት እየዘረዘረ ነው። ጆሮዎች ሁሉ የሚተላለፈውን መረጃ በአትኩሮት ማዳመጣቸውን ቀጥለዋል። አሁንም የታክሲ ረዳቱ ይጣራል። ወንበሮች ተገቢውን የሰው ቁጥር ቢይዙም አዲስ ለሚገቡ ተሳፋሪዎች ሽግሽግ እየተደረገባቸው ነው። በእያንዳንዳቸው ላይ ሦስት ሰዎች ተጣበን ተቀምጠናል። ረዳቱ አሁንም አልበቃውም «ፒያሳ ፒያሳ» እያለ ይጣራል።
ረዳቱ ተጨማሪ ሦስት ሰዎችን እያዋከበ ወደ ታክሲው አስገባ። የገቡት ሰዎች የታክሲውን ግድግዳ ተጠግቶ በተቀመጠው ቀጭን አግዳሚ ላይ እግራቸውን እያጠፉ ቁጢጥ አሉ። አሁንም የበቃው አይመስልም። ከገቡት ሰዎች ትይዩ ከጋቢናው ጀርባ ያለውን ክፍት ቦታ በእጁ እያመላከተ አንድ ተጨማሪ ሰው አከለ።
የቀትሩ ሙቀት የታክሲውን ሁለመና አግሎ ሁላችንንም ማዳረስ ይዟል። በያንዳንዱ ተሳፋሪ ላይ ስጋት የሚመስል ገጽታ ቢነበብም ሁሉም ዝምታን መርጦ የታክሲውን መንቀሳቀስ ይጠብቃል። ከደቂቃዎች በኋላ ውጭ የነበረው ሾፌር ከመኪናው መሪ ላይ ተደላድሎ ተቀመጠና ሞተሩን አስነሳ። ይህ በሆነ አፍታ ውስጥም ረዳቱ የታክሲውን መጋረጃ ሸፋፈነው። ይህን ማድረጉ ከትራፊክ እይታ ለመከለል መሆኑ ነው።
መኪናው ተንቀሳቅሶ ጉዞ እንደጀመርን ጥቂት ሰዎች የወቅቱን በሽታ መነሻ አድርገው ባለታክሲውን መውቀስ ጀመሩ። ይህኔ ሾፌሩ በ«ጆሮ ዳባ ልበስ» ዓይነት የሬዲዮኑን ወቅታዊ መልዕክት ዘግቶ ሞቅ ያለ ሙዚቃ ከፈተ።
በመኪናው መስኮት ወደውጭ አሻግሬ ቃኘሁ። በመንገዱ ጥቂት ሰዎች አፋቸውን ሸፍነው ይራመዳሉ። በርከት ያሉቱ ወደሚፈልጉት አቅጣጭ ለመጓዝ የታክሲ ሰልፍ ይዘዋል። ሰልፉ ረዥምና ጥቅጥቅ ያለ ነው። ሌሎች መንገደኞች ደግሞ ከዓይኔ ገቡ። በአጭር ርቀት ተጠጋግተው ያወጋሉ። ውስጤ በስጋት ታመሰ። ጎበዝ! ይህ የዓለማችን አጣዳፊና ገዳይ በሽታ እኛ ዘንድ ትርጉም አልባ ሆኗል፤ ሕይወት ያለምንም ጥንቃቄ ጉዞዋን ቀጥላለች።
ከተሳፋሪዎች መሀል ጥቂቶቹ ፒያሳ ሳይደርሱ ከመንገድ ላይ ወረዱ። ይህኔ ረዳቱ በተጓደሉት ምትክ ሌሎች ተሳፋሪዎችን ለማስገባት በሩን ከፈተ። ጉዞው ተጠናቆ ካሰብነው ስንደርሰ አብረውኝ ከነበሩ አንድ ጎልማሳ ጋር ጨዋታ ጀመርኩ። እሳቸው ይህ በሽታ መገኘቱ በሀገራችን ከታወጀበት ማግስት ጀምሮ በርካታ ራስ ወዳድ ባለታክሲዎች አጋጥመዋቸዋል። አብዛኞቹ ስለወገን የማያስቡና ለገንዘብ ትርፍ ብቻ የቆሙ ናቸው።
ባለታክሲዎቹ ጨለማን ተገን አድርገውና ከትራፊኮች እይታ ተከልለው ትርፍ ለመጫን የሚያደርጉት ሩጫ የራሳቸውን ወገን አጣድፎ ከመግደል የተለየ አይደለም። በርካቶቹ ዓለም ክፉኛ የተጨነቀበት አሳሳቢ ችግር ግድ አይላቸውም። እነሱ አብሮን መኖር የጀመረውን ወረርሽኝ «ቤት ለእንግዳ» ያሉና ሞትና ጉዳትን ለማባባስ የታጠቁ የክፉ ቀን ክፉዎች ሆነው አግኝቻቸዋለሁ።
የአንዳንዶቹ ባለታክሲዎች ድርጊት ደግሞ ከበርካቶቹ ልማድ ለመለየት የታሰበበት ይመስላል። እነዚህኞቹ ወንበሮቻቸውን በትርፍ ተሳፋሪዎች አጨናንቀው ትኩረት አይስቡም። ጉዟቸውም ቢሆን በመጋረጃዎች የተሸፋፈነ አይደለም። ሁሌም በወንበሮች ልክ ጭነው ያለ ችግር ይጓዛሉ። ከጥቂት መንገድ በኋላ ግን የብር ከሃምሳውን በሦስት ብር፣ የሦስት ብሩን በስድስት ብር፣ የስድስቱን… እያሉ በትርፍ ያገኙት የነበረውን ጥቅም መልሰው ያካክሳሉ።
ከሰሞኑ ከምሥራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ ጽሕፈት ቤት የተሰማው ዜና ደግሞ ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ነው። በዞኑ የተለያዩ ስፍራዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ከሚሰጡ ሀይሩፍ ሚኒባሶች አንዱ «በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ረዳቱን መልስ መጠየቅ አይቻልም» ሲል ከመኪናው ጀርባ ላይ ማስታወቂያ ለጠፈ። ድርጊቱ ከማስገረም አልፎ የክፉ ተሞክሮው ድርጊት ያናደዳቸው ሁኔታውን ለሕግ አሳወቁ። ፖሊስም በቁጥጥር አውሎ እነሆ! ተማሩበት ሲል ለሕዝብ ይፋ አደረገ።
ይህ ሁሉ ዓይን ያወጣ ድርጊት በሕግ አግባብ ይታሰር ዘንድ የራሱ ማዕቀፍ ሊወጣለት ግድ ብሏል። እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት የሚፈጽሙ ስግብግብ ባለታክሲዎችም ስለሚፈጽሙት ሕገወጥነት ሲባል የአንድ ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲጣልባቸው ተወስኗል።
ሰሞኑን ከወገን መኖር ይልቅ የገንዘብን ጥቅም ያስቀደሙ በርካቶች ከበሽታው መከሰት ጋር ተያይዞ በራስ ወዳድነት ከትዝብት የሚጥል ድርጊት መፈጸማቸውን ሰምተናል። በምግብ ፍጆታዎች ላይ የተጋነነ ዋጋ በመጨመር፣ ሸቀጦችን አከማችቶ በመደበቅና ገበያውን በማስወደድ፣ እንደማር ባሉ ምግቦች ላይ ጎጂ የሚባሉ ኬሚካሎችን በመደባለቅና ለሽያጭ በማቅረብ ራሳቸውን ጠቅመው ሌሎችን ለመጉዳት ሲሽቀዳደሙ ታይተዋል።
መንግሥት የጤና ሕጉ በአግባቡ እንዲተገበር ከመስራት ባሻገር ይህን አይረሴ ድርጊት በወገኖቻቸው ላይ የሚፈጽሙ የክፉ ቀን ክፉዎች በሕግ ይዳኙ ዘንድ አስተማሪ እርምጃ እንዲወስድ ይጠበቃል። ሁላችንም የበኩላችንን እንድንወጣም በዓለማችን ላይ እየሆነ ያለው እውነት ሊያስተምረን ይገባል። ይህ ፈታኝ ጊዜ አልፎ ዓለም ወደ ጤናዋ አስክትመለስም የክፉ ቀን ክፉዎችን በመለየት ለሕግ አሳልፈን ልንሰጥ ይገባል። ጉዳዩ «አንተ ቤት ሲንኳኳ ይሰማል እኔ ቤት» ነውና።
አዲስ ዘመን መጋቢት19/2012
መልካምሰራ አፈወርቅ