አዲስ አበባ፡- ከውጪ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ ተጓዦች ለአስራ አራት ቀናት መቆያ ቀድመው ከነበሩት ሁለት ሆቴሎች በተጨማሪ በ10 ሆቴሎች መዘጋጀታቸውን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ልማት ዘርፍ ሚስትር ደኤታ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት ቀደም ሲል ከውጪ ለሚገቡ እንግዶች ዝግጁ ከነበሩት ስካይ ላይትና ጊዮን ሆቴል በተጨማሪ ሂልተን ሆቴልን ጨምሮ ከደረጃ አንድ እስከ አምስት አስር ሆቴሎች ተዘጋጅተዋል። በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኩልም በየሆቴሉ ያሉ ሰራተኞችን ደህንነት የማስጠበቅ ባለሙያና ክትትል የሚያደርግ የጸጥታ ሀይልም የተመደበ ሲሆን ይህንንም ወደ ክልሎች ለማውረድ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። እንደ ውጪ ዜጎች ሁሉ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት ሲመጡ አስራ አራት ቀናት በራሳቸው ወጪ የሚቆዩ በመሆኑ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲስተናገዱ ትብብር እንዲደረግም ሚንስትር ደኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም ቫይረሱ የሰዎችን እንቅስቃሴ የሚገድብ በመሆኑ ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጥሯል። በዚህም ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ከየካቲት እስከ ሀምሌ ቀጠሮ የነበራቸውና የተወሰኑትም ክፍያ ፈጽመው የነበሩ ጉዟቸውን ለመሰረዝ ስለተገደዱ የዘርፉ እንቅስቃሴ መቀዛቀዙ ተገልጽዋል። ይህም ቢሆን ግን ባለሆቴሎችና ቱር ኦፕሬተሮች የተቻላቸውን አማራጭ በመጠቀም ሰራተኞችን ሳይቀንሱ እንዲቆዩ የተጠየቀ ሲሆን በዚህ ጉዳይ ከመንግስት ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ህብረተሰቡ በያለበት ሆኖ በህክምና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን በአግባቡ በመጠቀም ራሱን ቤተሰቡን ብሎም ማህበረሰቡን ከጥፋት እንዲታደግ የጠየቁት ሚኒስቴር ደኤታዋ ሰራተኞች ስራ በማይገቡበት ወቅት በማንበብና ራሳቸውን በማብቃት እንዲያሳልፉም ጠይቀዋል።
የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማህበር ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ቱሪዝም ቦርድ አባል አቶ ቢንያም አስራት በበኩላቸው ወረርሽኙ በአለም አቀፍ ደረጃ መከሰቱ ከተሰማበት ቀን ጀምሮ ከህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን በከተማዋ ባሉት 130 ሆቴሎች ውስጥ የሚገኙ 15 ሺ 255 ሰራተኞች ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅትም ሰራተኞች ከቫይረሱ ራሳቸውን እንዲከላከሉም የጽዳት እቃዎችን ለተመረጡት ሆቴሎች ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን እየቀረበላቸው ሲሆን ለሌሎቹ ሆቴሎች ከአከፋፋይ እንዲወስዱ ዝርዝር ተላልፎላቸዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ለጉብኝት ብቻ ሳይሆን በኮንስትራክሽን፤ በግብርናና በማኑፋክቸሪንግ እንዲሁም በተለያዩ የልማት ስራዎችና በዪኒቨርሲቲዎች ለማስተማር የመጡ የውጪ ዜጎች መኖራቸውን በማስታወስ፤ በአንዳንድ ወገኖች ከኢትዮጵያዊነት ባህልና ስነ ምግባር ባፈነገጠ መልኩ የውጪ ዜጎች ላይ እየተደረገ ያለው ማግለል መቆም እንዳለበትም አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት19/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ