አዲስ አበባ፡- እንደ አገር አደጋ ደቅኖ ያለውን ዓለምአቀፍ የኮሮና ወረርሽኝን በልኩ ተመልክቶ በተገቢው የመከላከል ስራ ካልተሰራ እንደሀገር የከፋ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል የተለያዩ ምሁራን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስኩል ኦፍ ሳይኮሎጂ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ትዕግስት ውሂብ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ወረርሽኙን ተከትሎ ሁለት ማህበራዊ ገጽታዎች ይኖራሉ፡፡ አንደኛው የመረበሽ ስሜት ሲሆን፤ ሁለተኛው ነገሮችን አቅልሎ የማየት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከስነ ልቡና ዝግጁነት ጋር የሚያያዝ እንደመሆኑ ችግሩን በልኩ ተመልክቶ ተገቢው የጥንቃቄና የመከላከል እርምጃ እንዲወሰድ ከማድረግ አኳያ የግንዛቤ ማስጨበጥና መረጃን ተደራሽ የማድረግ ተግባራት ሊከናወኑ ይገባል፡፡
እንደ ዶክተር ትዕግስት ገለጻ፤ በሽታው አዲስ ከመሆኑ አንጻር በርካታ ነገሮች ሊባሉ፤ የተለያዩ መረጃዎችም ሊሰራጩ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ህብረተሰቡ ተገቢው መረጃ ከሌለውና ግንዛቤ ተፈጥሮለት የስነ ልቡና ዝግጅትም ካላደረገ በተለያዩ አገሮች ከሆነውና እየሆነ ካለው ጋር በማያያዝ የመረበሽ ስሜት ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡
በአንጻሩ በሌሎች አገራት ያለውን ሁነት በኢትዮጵያ ካለው ጋር በማነጻጸር የተከሰተውን ነገር አቅልሎ የማየትና ችግሩ በኢትዮጵያ ላይ ጉዳት እንደማያደርስ አድርጎ የመመልከት አዝማሚያ ውስጥ መግባት በከፍተኛ ሁኔታ ለቫይረሱ ተጋላጭ ያደርጋል፡፡
ዶክተር ትግስት እንደሚሉት የኮሮና ቫይረስን ከልክ በላይ አግዝፎም ሆነ አቅልሎ መመልከት በሀገራችን በስፋት ይታያል፡፡ ችግሩን ከሚገባው በላይ አግዝፎ የማየትና በጣሙን በመረበሽ ሂደት ውስጥ በስራ አከባቢም ሆነ በሌሎች ማህበራዊ መስተጋብሮች ውስጥ የሚገለጽ ትልቅ የፍራቻ ስሜት ተፈጥሯል፡፡ መጠንቀቁ ተገቢ ቢሆንም የበዛ ጸጥታና ነገሮችን ሁሉ ከኮሮና ጋር አያይዞ ማየቱ ትልቅ የስነ ልቡና ጫና ፈጥሯል፡፡
በአንጻሩ ችግሩን አቅልሎ ከማየትና እኛጋ ወይም እኔጋ አይከሰትም ብሎ ከማሰብ የሚመነጭ የበዛ የግዴለሽነት መገለጫ ተግባራት ይስተዋላሉ፡፡ ይሄም በማቅለል ውስጥ ችግሩን የማባባስና ራስንም ሆነ ሌሎችን ለበሽታው ተጋላጭ የማድረግ አካሄድ መሆኑ መታወቅ ይገባዋል፡፡ እነዚህ ሁለት ገጽታዎችም አውሮፓን ጨምሮ በሌሎች አገራት ለችግሩ መባባስ ምክንያት ሆነው ተስተውለዋል፡፡
በመሆኑም ችግሩን አቅልሎ የመናቅም ሆነ አግዝፎ የመረበሽ አካሄዶች በሽታውን በወጉ ተገንዝቦ ወረርሽኙን በመከላከል ሂደት ላይ አሉታዊ አስተዋጽዖ እንዳላቸው በመገንዘብ፤ ህብረተሰቡ ሳይረበሽም ግዴለሽ ሳይሆንም ተገቢውን ግንዛቤ ፈጥሮ ችግሩን የመከላከል አካል በመሆን ራሱንም ህብረሰቡንም እንዲጠብቅ ማስቻል ያስፈልጋል፡፡
እጅን አዘውትሮ ከመታጠብ ጀምሮ አካላዊ ርቀትን ምጣኔና መሰል የቅድመ መከላከል ስራዎችን መተግበርና እንደ አማኝም በጸሎት እንዲተጋ በማስገንዘብ የወረርሽኙ አባባሽ ሳይሆን ተከላካይ ደጀን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ህብረተሰቡም የሚሰጠውን መረጃና የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በአትኩሮት ወስዶ ሊተገብረው ይገባል፡፡
ዶክተር ትዕግስት እንደሚሉት፤ ስለ ቫይረሱ ስርጭትና የመከላከል ሂደት ከሚሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጥና ህብረተሰቡን እንዲከላከል ከማብቃት በተጓዳኝ ሥርዓት የማስከበር እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ህብረተሰቡ አሁን ላይ ከኮሮና ቫይረስ ባልተናነሰ መልኩ የኑሮ ውድነትና የፍጆታ ምርቶች ጉዳይ እያሳሰበው ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ አንድም ካልተገባ የዋጋ ጭማሪና የምርቶች እጥረት ጋር የሚያያዝ ሲሆን፤ አሁን ላይ አቅም ያለው እየሸመተ ቢሆንም በሂደት ግን በእለት ስራ ላይ ተሰማርቶ የእለት ጉርሱን በሚሸፍን ሰፊው የህብረተሰብ ክፍል ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ የማይቀር ነው፡፡
በመሆኑም ችግሩ ሳይባባስ መንግስት አሁን በጀመረው መልኩ እርምጃዎችን አጠናክሮ ሊቀጥልና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዳይፈጥር አቅርቦቱንም ማሳደግ ያለበት ሲሆን፤ ችግሩ የአጭር ጊዜ መሆኑንና ህብረተሰቡ በግንዛቤ ላይ ተመስርቶ ወረርሽኙን የመከላከል ስራ ላይ ከተረባረበ ሁሉም የሚፈታ መሆኑን ማሳወቅም ያስፈልጋል፡፡ በተመሳሳይ አሁን ላይ የተጀመሩ እጅን የማስታጠብና መሰል የበጎ ፈቃድ ተግባራትም ተጠናክረው ሊቀጥሉና ልምድ ሆነው ሊወሰዱ፤ የሳሙናና ሌሎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችም በአግባቡ ሊቀርቡ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት19/2012
ወንድወሰን ሽመልስ