አዲስ አበባ:- ሩቅ ምስራቅ እና አውሮፓን ጨምሮ ወደ ተለያዩ ሀገራት እቃዎችን እያመላለሱ በሚገኙ 11 የኢትዮጵያ መርከቦች ላይ የኮሮና ቫይረስን በመከላከል ረገድ ለካፒቴኖች አስፈላጊው መመሪያ እየተላለፈና ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ።
በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ አገልግሎት ድርጅት የኮሙዩኒኬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አሸብር ኖታ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ በሚገኙ 11ዱ የኢትዮጵያ መርከቦች ለሀገር የሚያስፈልጉ እቃዎችን እያመላለሱ ይገኛሉ። በባህር ላይም ሆነ ወደየብስ በሚጠጉበት ወቅት አስፈላጊው የኮሮና ቫይረስ ጥንቃቄ እንዲደረግ አስቀድሞ ለካፒቴኖች መመሪያ በመተላለፉ ተገቢው ጥንቃቄ በመርከቦቹ ላይ እየተደረገ ይገኛል።
እንደ አቶ አሸብር ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መርከቦች ከጥቁር ባህር አካባቢ እና ከሩቅ ምስራቅ ሀገራት እቃዎችን እያመላለሱ ይገኛሉ። መርከቦች ወደ ሩቅ ምስራቅ ሲጓዙ ለአንድ ወር ያክል፤ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ሲጓዙ ደግሞ ለ15 ቀናት ባህር ላይ ሊቆዩ ይችላሉ። እያንዳንዱ መርከብ ላይ ደግሞ በአማካይ 36 ሰዎች ይሰማራሉ። በመሆኑም ማንም ሰው ወደ መርከብ እንዳይገባና የገባውም እንዳይወጣ እርምጃ ተወስዷል፡፡
አንዱ መርከበኛ በሚያደርሰው ችግርም የመርከቡ እና የሀገር ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ለአደጋ እንደሚጋለጥ ስለሚታወቅ መርከብ ላይ ያለው ጥንቃቄ ቀድሞም ቢሆን ጠንካራ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ኮሮና ከተከሰተ በኋላም የሚደረገው ቁጥጥር ከፍተኛ በመሆኑ ካፒቴኖች በግብዓት የታገዘ እና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ የመከላከል ስራውን በብቃት እየመሩት እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ አገልግሎት ድርጅት በየወቅቱ በመንግስት የሚሰራጩ እና በሽታውን ለመከላከል አስፈላጊ የሆኑ መልዕክቶችን ለመርከበኞቹ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች እያሰራጨ እንደሚገኝና የቫይረሱ ስርጭት ከቻይና ከተሰማ ጀምሮ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፅሁፎች ያለማቋረጥ በሳምንት ሁለት ቀን በመሰጠት ላይ መሆኑን አቶ አሸብር ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ 11ዱ መርከቦች ለሀገሪቷ ወጪና ገቢ ዕቃዎች 20 በመቶ የማይሞላ ድርሻ እንዳላቸው የገለጹት አቶ አሸብር፤ ተቋሙ ዕቃዎችን ለማመላለስ የሌሎች ሀገራት እና ድርጅቶች መርከቦችን በቻርተር በመከራየት እንደሚጠቀም አስረድተዋል። በመሆኑም የሌሎች ሀገራት መርከበኞችም በባህር እና በጅቡቲ ወደብ ላይ የእራሳቸውን የበሽታ መከላከያ መንገዶችን ዘርግተው ጥንቃቄ በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል። አብዛኛዎቹ የኮንቴይነር እቃዎች ከምርት ጀምሮ እስከ ወደብ ማራገፍ ድረስ ከሰዎች ንክኪ ውጭ በማሽን እገዛ ለማከናወን ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
እንደ አቶ አሸብር ከሆነ፤ በኢትዮጵያ በኩልም ከባህር እስከ ወደብ ከዚያም አልፎ እቃዎች በተሽከርካሪ ተጓጉዘው የሚፈለግበት ቦታ እስኪደርሱ ያለውን የበሽታው መከላከል ተግባር የሚመራ እና በተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሯል። የተዋቀረው ኮሚቴ ተቋሙ የሚመራበትን የበሽታ መከላከል ስትራቴጂ የሚመራበትን አዲስ ሰነድ አዘጋጅቷል። በዚህም መሰረት የተቋሙ ሰራተኞች እና የሎጂስቲክስ ዘርፉ ተሳታፊዎች ሊያደርጓቸው የሚያስፈልጉ ጥንቃቄዎች እና አስፈላጊው እርምጃዎች በዝርዝር ተለይተዋል።
እንደ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ አገልግሎት ድርጅት መረጃ ከሆነ፤ ከኢትዮጵያ የሚወጡና የሚገቡ የወደብ እቃዎች መካከል 90 በመቶው የሚጓጓዙት በተቋሙ አማካኝነት ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት19/2012
ጌትነት ተስፋማርያም