ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የኮሮና ቫይረስ በሽታ አፍሪካ ሀገራት የሚያሳድረውን ጫና ለመቀነስ 150 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ሰሞኑን ለቡድን 20 አባል ሀገራት ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግስት ያለበትን የብድር ወለድ ስረዛ እና የክፍያ ጊዜ ማሻሻያ እንዲደረግም ምክረሃሳብ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሃብት ለማሰባሰብ እያከናወነ ከሚገኘው ጥረት ባለፈ በሀገር ውስጥ ምጣኔ ሃብቱን ለመታደግ ምን አይነት እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው በሚለው ጉዳይ ላይ የዘርፉ ምሁራን ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
<<መንግስት በሚወስዳቸው ምጣኔ ሃብታዊ እርምጃዎች አማካኝነት ይበልጥ ተፈትኖ የሚወጣበት ጊዜ አሁን ነው>> የሚሉት የፓን አፍሪካ ንግድ ምክር ቤቶችና ኢንዱስትሪ ተቋም ዋና ዳይሬክተር እና የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ክቡር ገና ናቸው። መንግስት ምጣኔ ሃብቱን ለመታደግ የበሽታውን ቁጥጥር ላይ የሚወስደውን ጥንቃቄ በእጅጉ ከማሳደግ ባለፈ በዋናነት የአስመጪነት እና ላኪነት ስራውን በዋናነት መወጣት ይገባዋል።
አሁንም በሽታው የሚያደርሰውን ችግር ለመከላከል የግሉ ዘርፍ ብቻ አስመጪነት እና ላኪነት ላይ ይሰማራ ቢባል ከባድ ነው። በመሆኑም በመንግስት ደረጃ በማስተባበር እንዲሁም ዋና ዋና የተባሉ የግል ዘርፍ ተዋናዮችን በመያዝ ለሀገር የሚያስፈልገውን የማስገባት እና የመላክ ተግባሩን በትኩረት ሊመራ ይገባል።
አቶ ክቡር ገና እንደሚሉት፤ በሌላ በኩል በማይክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ ደግሞ አነስተኛውን ማህበረሰብ ለመደጎም እንዲረዳ ቀበሌዎች ላይ የሚሰሩ ስራዎችን ማጠናከር ያስፈልጋል። የታችኛው አስተዳደር ህብረተሰቡን በቅርብት ለማግኘት አይነተኛው መንገድ በመሆኑ ምግብም ማከፋፈል ካስፈለገም ሆነ አስፈላጊውን የበሽታ መከላከል እርምጃ ለመውሰድ ቀበሌዎች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ማድረጉ ተገቢ ነው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ደኑ በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ብቻውን የቆመ ሳይሆን ከሌሎች ሀገራት ጋር የተሳሰረ ነው። የጎረቤት ሀገራት እና ሌሎች ከኢትዮጵያ ጋር ከፍተኛ የንግድ ትስስር ያላቸው ሀገራት ከችግሩ ካልወጡ የኢትዮጵያ ጉዳይ ብቻውን ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም።
ይሁንና ኢትዮጵያ ያላት የኢኮኖሚ አቅም ውስን በመሆኑ ሌሎች ሀገራት እንደተደረገው ዘግቶ መቀመጥ ሳይሆን መጠነኛ እንቅስቃሴ እያደረጉ ፋብሪካዎች እንዲሰሩ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ከዚህ ባለፈ አርሶአደሩ ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረገ የግብርና ስራውን እንዲቀጥል ማድረግ ያስፈልጋል።
ለዚህም በየገጠሩ ኮሚቴ አዋቅሮ በሽታውን የመከላከል እና የግብርና ስራውን ጎን ለጎን በጥንቃቄ ለማከናወን የሚያስችል የመረጃ እና የግብዓት አቅርቦት በማሟላት ኢኮኖሚው እንዳያንቀላፋ ማድረግ ይገባል።
እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ከሆነ፤ አሁን የመጣውን ችግር መንግስት ብቻውን ይቆጣጠረዋል ማለት አይቻልም። በመሆኑም ሀገር ውስጥ ያሉ ዜጎችን እና ከሀገር ውጭ ያሉ ሀገር ወዳዶችን በማስተባበር ለመንግስት የኢኮኖሚ እርምጃዎች የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል። ከዚህ ባለፈ ግን ጉዳዩ የሀገር ህልውና ነውና ነጋዴውም ሆነ ዜጋው ካለው ላይ ቆርሶ በመስጠት መንግስት በሀገር ደረጃ ለሚሰራቸው የበሽታ ቁጥጥር እና የኢኮኖሚ መደጎሚያዎች ማዋል ያስፈልጋል።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ዴሊቨሮሎጂ ትምህርት ክፍል ሃላፊ ዶክተር ተሾመ ዱላ በበኩላቸው እንደሚያስረዱት፤ የሲንጋፖር እና የደቡብ ኮርያ ተሞክሮ ቴክኖሎጂን በመጠቀምና መረጃን ለህብረተሰቡ በማዳረስ ውጤታማ ስራ ተከናውኗል።
በኢትዮጵያም በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን እንደሚታየው እያንዳንዱ ተነስቶ ዛሬውኑ እንቅስቃሴ ይቁም አሊያም ወደከተሞች ሰው አይግባ እንደሚባለው ሳይሆን የበሽታውን ስርጭት የተንተራሰ ወቅታዊ እርምጃ በቴክኖሎጂ ታግዞ ለህብረተሰቡ ማድረስ ላይ ማተኮር ያስፈልጋል።
አሁን ላይ ግን ትልቁን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የያዘውን የገጠሩ ክፍል በበሽታው ዙርያ በቂ ግንዛቤ አልደረሰውም። ትልቁን የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ህብረተሰብ ባላማከለ መልኩ የሚሰራ ስራ ደግሞ ኢኮኖሚውን ክፉኛ ይጎዳዋል።
እንደ ዶክተር ተሾመ ከሆነ፤ መንግስት መረጃውን ለማዳረስ የሚሰራው ስራ የሚበረታታ ሆኖ መጠናከር ግን አለበት። አስገዳጅ ሁኔታ እስካልተፈጠረ ድረስም ሙሉ በሙሉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ሳይገደቡ በአነስተኛ ሰው ስራዎችን ማከናወን እንደሚያስፈልግ መረጃ የማስተላለፉ ስራ መጠናከር አለበት።
ነገርግን ሙሉ በሙሉ ዘግተን እንቀመጥ ከተባለ የሚበላም ጠፍቶ እልቂት ሊከሰት ይችላል። በመሆኑም ኢኮኖሚው የበለጠ እንዳይጎዳ ለማድረግ ወቅታዊ መረጃዎችን በማጠናቀርና ኢኮኖሚውን በመጠኑ ማንቀሳቀስ ይገባል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኮቪደ-19 ወረርሸኝን ለመከላከል የሚያስፈልጉ የገቢ ዕቃዎች እና ግብአቶች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ እንደሚደረግ መንግስት ያስታወቀ ሲሆን የፋይናንስ ዘርፉን ጤንነት አስጠብቆ የመቀጠል እና ባንኮች በኮቪድ-19 ቫይረስ ለተጎዱ ደንበኞቻቸው ጊዜያዊ የብድር እፎይታ እና ተጨማሪ ብድር ለመስጠት እንዲያስችላቸው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተጨማሪ 15 ቢሊየንብር ለግል ባንኮች እንደሚሰጥ ገልጽዋል፡፡
የውጪ ምንዛሬ የሚያስፈልጋቸው እና የኮቪድ- 19 ወረርሸኝን ለመከላከል የሚያስችሉ ዕቃዎችን እና ግብአቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለሚያስገቡ አስመጪዎች ባንኮች ቅድሚያ በመስጠት እንዲያስተናግዱ እንደሚደረግም ጠቁሟል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት19/2012
ጌትነት ተስፋማርያም