አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት በመንግሥት፣ በጤና ባለሙያዎችና በሃይማኖት አባቶች የሚተላለፉ ውሳኔዎችንና መልዕክቶችን ተግባራዊ በማድረግ አትሌቶችና አርቲስቶች አርአያነታቸውን በተግባር ማሳየት እንዳለባቸው ተጠየቀ፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት አትሌት ደራርቱ ቱሉ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እየተደረገ ያለውን ጥረት በተመለከተ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጸችው፤ የኮሮና ቫይረስ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ችግር ነው፡፡ ይህን አሳሳቢና ገዳይ በሽታ መከላከል የሚቻለው የመንግሥት ውሳኔዎችን፣ የጤና ባለሙያዎችን ሙያዊ ምክርና የሃይማኖት አባቶችን መልዕክት ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ ሲቻል ነው፡፡
«እኔ ራሴን ስጠብቅ፣ ቤተሰቤን፣ ጎረቤቴን፣ ጓደኞቼንና ሕዝቤን እጠብቃለሁ» የምትለው አትሌት ደራርቱ ቱሉ፤ አትሌቶችም ሆኑ አጠቃላይ ሕዝቡ በሚኖርባቸው አካባቢዎች ቤተሰቡን፣ ጎረቤቱንና አጠቃላይ ሕዝቡን ከበሽታው ለመታደግ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት ተብለው የሚተላለፉ የጥንቃቄ መልዕክቶችን ሙሉ ለሙሉ ማክበርና መፈጸም እንደሚኖርበት ተናግራለች፡፡
«በጥንቃቄ ጉድለት በቫይረሱ የሚጠቃ ሰው ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቡም ሆነ ለማህበረሰቡ አደጋ ያስከትላል» ያለችው አትሌት ደራርቱ፤ ማንኛውም ሰው ለራሱ ሲል የሚያደርገው ጥንቃቄ ለቤተሰቡም ለማህበረሰቡም የሚሻገር በመሆኑ እንዝላልነት የሚታይባቸው ሰዎችን መምክረና ማስታወስ ያስፈልጋል ብላለች፡፡
መንግሥት፣ የጤና ሚኒስቴርና የሃይማኖት አባቶች ቀዳሚ ትኩረት ሰጥተው በሚዲያዎች በመጠቀም የሚያስተላልፏቸው ውሳኔዎችና መልዕክቶች እንዲተገበሩና ሕዝቡ በበሽታው እንዳይጠቃ መሆኑን ገልጻ፣ ጊዜው ፈታኝና አስቸጋሪ በመሆኑ በአንድነትና በመተጋገዝ ወቅቱን ልንሻገር ይገባል ስትል ገልጻለች፡፡
ስለ ኮሮና ቫይረስ በዓለም አቀፍ፣ በማህበራዊና በአገር አቀፍ ሚዲያዎች የሚተላለፉ የጥንቃቄ መልዕክቶች ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ተሞክሮ ናቸው የምትለዋ አትሌቷ፤ ከሕፃን እስከ አዋቂ ድረስ ሁሉም በሽታውን ለመከላከል የሚደረጉ ጥረቶችን በማገዝና በመተግበር ኃላፊነታችንን በየፊናችን መወጣት እንዳለብን መልዕክቷን አስተላልፋለች፡፡ «እኔ በመንግሥት፣ በሃይማኖት አባቶች፣ በጤና ባለሙያዎችና በሚዲያዎች የሚተላለፉ መልዕክቶችን በሙሉ ከእነ ቤተሰቤ እየተገበርኩ ነው፡፡
ተራርቆ መቀመጥ፣ ንክኪን ማስወገድ፣ ሳኒታይዘር መጠቀም፣ እጅን በሳሙናና በውሃ መታጠብንና ብዙ የሕዝብ መጨናነቅ ወደ አለባቸው ቦታዎችን ባለመሄድ እንዲሁም የመከላከያ መልዕክቱን ላልሰማ መልዕክቱን በትክክል ማስተላለፍና መፈጸም፤ አቅም ለሌላቸው ወገኖች የንጸህና ዕቃዎች ማካፈል፣ ራሴንና ቤተሰቤን ከኮሮና ቫይረስ እየተከላከልኩ ነው» ስትል ተሞክሮዋን አካፍላናለች፡፡
ወቅታዊ የኮሮና ቫይረስ መቅሰፍትና ዓለም አቀፍ ስጋት ነው፡፡ ማንንም የማይለይ አይደለም፡፡ ቫይረሱን ለመከላከልም የሁሉንም ጥረትና ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው የሚሉት የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፎች ማህበራት ህብረት ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት ይፍሩ፤ በአገር ደረጃ ጦርነት፣ በሽታና ድርቅ ሲያጋጥሙ ኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሕዝቡን ለአንድ ዓላማ በማነሳሳትና ግንዛቤ በመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ገልጸዋል፡፡
አሁንም የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን በመግታት ረገድ ፈጠራ የታከለበትና ለኅብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ትምህርት የሚሰጡ የኪነ ጥበብ ውጤቶች መስራት እንዳለባቸው አደራ ብለዋል፡፡
እንዲሁም አርቲስቶች የኅብረተሰቡ አካል እንደመሆናቸው መጠን ለበሽታው ከሚያጋልጡ የሥራ ሁኔታዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2012
ጌትነት ምህረቴ