ዓለምን እያስጨነቀ ያለውና እስካሁን ከ20ሺ በላይ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመግታት በየአገራቱ የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው፡፡ የሰዎችን እንቅስቃሴ ከመግታት ጀምሮ የሰዓት እላፊ የመጣል፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ሌሎች በርካታ እርምጃዎችም ተወስደዋል፤ እየተወሰዱም ይገኛሉ፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን የተለያዩ ተቋማትም የየራሳቸውን እርምጃ ወስደዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ የሃይማኖት ተቋማት ይጠቀሳሉ::
በኢትዮጵያም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሃይማኖት አባቶች ለምእመኖቻቸው ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል። በተለይ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን በቤት ውስጥ መፈጸም እንዲሁም ንክኪን ማስወገድና እርቀትን በመጠበቅ የእምነት ተከታዮች እራሳቸውን ከበሽታው እንዲከላከሉ አስጠቅቀዋል።
ያም ሆኖ ግን እስካሁን ባለው ሂደት የሃይማኖት ተከታዮች ከሃይማኖት አባቶችና ከጤና ሚኒስቴር የተላለፈውን መልዕክት ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ውስንነቶች እንደሚታዩ መታዘብ ችለናል፡፡ በተለያዩ እምነት ተቋማት አሁንም በተጨናነቀ መልኩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች እየተካሄዱ ናቸው፡፡ በአዳራሽ የሚካሄዱ የአምልኮ ሥርዓቶችም እየተስተዋሉ ነው፡፡
የእምነት ተከታዮች የሃይማኖት መሪዎች፣ መምህራን፣ መንግሥትና የጤና ባለሙያዎች ያስተላለፉትን የጥንቃቄ መልዕክት ተግባራዊ እንዲያደርጉ፤ እራሳቸውንና ሌሎችንም ከበሽታው እንዲጠብቁ የሃይማኖት አባቶችና መምህራን በተደጋጋሚ ቢያሳስቡም በአግባቡ ወደተግባር መለወጥ አልተቻለም፡፡
የእምነት መሪዎችና አባቶች በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ለምዕመናን ተደጋጋሚ የጥንቃቄ መልዕክት የማስተላለፍ ሥራ እየሰሩ መሆኑን የሚገልጹት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የትንሳኤ ማተሚያ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አባ ንቡረዕድ ኤልያስ፤ በቤተክርስቲያኗ በኩል አንድ ሰው ከጥንቃቄ ጉድለት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሕይወቱ እንዳያልፍ ከእምነቱ አስተምሮ በመነሳት የእምነቱ ተከታዮች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በእምነት መሪዎች፣ አባቶች፣ መንግሥትና የጤና ባለሙያዎች የሚተላለፉትን የጥንቃቄ መልዕክቶች ተቀብለው ተግባራዊ እንዲያደርጉ አሁንም ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ነግረውናል፡፡
«ለውጥ በአንድ ጊዜ የሚመጣ ባይሆንም ቫይረሱ የሰውን ሕይወት የሚቀጥፍና በፍጥነት የሚሰራጭ በመሆኑ ፈጣሪ በሰጠን እውቀት ተጠቅመን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረጉ ተገቢ ነው» የሚሉት አባ ንቡረዕድ ኤልያስ፣ ምዕመናን ከቤተ ክርስቲያናት፣ ከእምነቱ አባቶችና ከቅዱስ ሲኖዶሱ እንዲሁም ከመንግሥትና የጤና ባለሙያዎች የሚያስተላልፉትን መልዕክት አስተውሎ በመፈጸም ገዳይ ከሆነው የኮሮና ቫይረስ ራስን መከላከል ይቻላል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል::
የእስልምና ሃይማኖት መምህር ኡስታዝ አህመዲን ጀበል እንደገለጹት፤ የኮሮና ቫይረስ ጉዳይ የዓለም አጀንዳ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ብዙ አገራት እየፈተነና በሚያስደነግጥ ሁኔታ ብዙ ዜጎቻቸውን እየቀጠፈ ይገኛል፡፡ ከዚህ አንጻር አሁን ያለንበት ወቅት ከባድ አገራዊ ፈተና ያጋጠመን ጊዜ ነው፡፡
መንግሥትም የዓለም ስጋት የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመግታት አምስት ቢሊዮን ብር መድቧል፤ 30 ሚሊዮን ተማሪዎች ትምህርት እንዲያቋርጡ ወስኗል:: በቫይረሱ የተጠቁ ዜጎችም በየጊዜው በጤና ሚኒስቴር በኩል እየተነገረ ነው፡፡ የሃይማኖት አባቶችና የእምነት ተቋማትም ለተከታዮቻቸው መልዕክት እያስላለፉ ናቸው::
ሆኖም እምነትና ጥንቃቄ ጎን ለጎን መሄድ ካልቻሉ ብዙ ዋጋ ሊያስከፍሉ ይችላሉ፡፡ ወረርሽኝ በሚከሰትበት ጥንቃቄ ማድረግ እየተቻለ ፈጣሪ ያድነኛል ብሎ እጅን አጣምሮ ማየት ተገቢ አይደለም የሚሉት ኡስታዝ አህመዲን፣ ኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት ሲባል በሃይማኖት መሪዎችና በእምነት አባቶች የሚሰጡ መልዕክቶች፣ በመንግሥት የሚተላለፉ ውሳኔዎችን፣ በጤና ባለሙያ የሚገለጹ የመከላከያ መንገዶቹን መተግበር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያን ወንጌላውያን አቢያተክርስቲያናት ህብረት የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ መጋቢ ዘሪሁን ደጉ በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ ፈጣንና በቀላሉ ሊተላለፍ የሚችል መሆኑን ከጣሊያንና ከስፔን አገራት መረዳት ይቻላል ይላሉ፡፡ እነዚህ አገራት በኢኮኖሚም ሆነ በሥልጣኔ ጫፍ የረገጡ ቢሆንም በከፋ ሁኔታ በቫይረሱ የተጠቁት ሕዝባቸው መንግሥት፣ የጤና ባለሙያዎችና የሃይማኖት መሪዎች የሚያስተላልፉላቸውን መልዕክቶችና ውሳኔዎች ችላ በማለታቸው እንጂ ሃይማኖት ስለሌላቸው አይደለም ብለዋል፡፡
በተለይ ጥግግትን ባለመጠበቃቸውና ራስን ሰዎች ከሚበዙበት አካባቢዎች እንዲቆጠቡ የተላለፉ መልዕክቶችን ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ዛሬ ጣሊያን ብቻ በኮሮና ቫይረስ ከሰባት ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ተቀጥፎል፡፡ ከ67ሺ በላይ ዜጎች በቫይረሱ ተጠቅተዋል:: እኛም ከዚህ ትምህርት ወስድን በሃይማኖት መሪዎች፣ አባቶች፣ መምህራን፣ እንዲሁም በመንግሥትና በጤና ባለሙያዎች የሚተላለፉ መልዕክቶችንና ውሳኔዎችን በማክበርና በመተግበር ራስን ከኮሮና ቫይረስ መከላከል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2012
ጌትነት ምህረቴ