አዲስ አበባ:– ክልሎች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረጉ መሆናቸውን አስታወቁ። የደቡብ ክልል መንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሰናይት ሰሎሞን እንደተናገሩት፣ በክልሉ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የሚመራና ወረዳ ድረስ የሚወርድ ግብረ ኃይል ተደራጅቷል። በዚህም ለኅብረተሰቡ ስለበሽታው ምንነትና መተላለፊያ መንገዶች እንዲሁም አንዳንድ ምልክቶች ሲታዩ ወደ ጤና ተቋማት መሄድ እንደሚገባቸው የግንዛቤ ማስጨበጥ በአማርኛና በየማህበረሰቡ ቋንቋ እየተሰራ ይገኛል።
እጅ ከማስታጠብ በተጨማሪ ተሽከርካሪዎች መጫን ካለባቸው ቁጥር ባነሰ እንዲጭኑና ተራርቀው እንዲቀመጡ ከትራንስፖርት ማህበራት ጋር እየተሰራ ሲሆን የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ለኅብረተሰቡ እየቀረቡ ይገኛል። እስካሁን ሃያ የለይቶ ማቆያ ማዕከላት ተዘጋጅተው ግብአት እየተሟላላቸው ይገኛል። ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ አድርገው በተገኙ 899 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወስዷል። እስካሁን አምስት ግለሰቦች በበሽታው ተጠርጥረው ምርመራ ተደርጎላቸው አራቱ ነፃ ሲሆኑ የአንዱ ምርመራ በሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል።
በተመሳሳይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ፍሬሕይወት አበበ በበኩላቸው በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሚመራው ግብረ ኃይል መደራጀቱን በመግለጽ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ በተሰራው ሥራ እጅ መታጠብና መጨባበጥ ላይ ለውጥ እየታየ ቢሆንም ማህበራዊ ርቀት ላይ ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል። በሰለጠነ የሰው ኃይል ረገድም ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመሆን አስር ሰዎች ሰልጥነው የመጡ ሲሆን አሁንም ተጨማሪ ሥልጠና እየተሰጠ ሲሆን ከሦስት ወረዳዎች ውጪ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን ተዘጋጅቶ እየተጠባበቀ ይገኛልም ብለዋል።
የሕክምና ተቋማትን በማደራጀት በኩል አሶሳ ላይ አንድ ጤና ጣቢያ ሥራ አቁሞ ለዚሁ ብቻ የተዘጋጀ ሲሆን በባለሙያም በቁሳቁስም ዝግጁ ሆኖ እየጠበቀ ይገኛል ያሉት ኃላፊዋ፣ በሁለት ዞኖች ላይም ባለሙያ ሰልጥኖ ቦታም የተለየ ሲሆን በቀናት ውስጥ ቁሳቁስ የማሟላት ሥራ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
ኃላፊዋ ጨምረው እንደተናገሩት፣ በክልሉ ባሉት አምስት የስደተኛ ጣቢያዎች በሚገኙ ከስልሳ ሺ በላይ ስደተኞችን ከቫይረሱ ለመከላከልም ካምፖችን ከሚያስተዳድሩት ጋር በመሆን ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። ለህዳሴው ግድብም ከራሱ ጤና ጣቢያ ውጪ በአቅራቢያ በሚገኝ አንድ ወረዳ መከላከያን ጨምሮ ለተለያዩ ሠራተኞች ሥልጠና በሚቀጥሉት ቀናት የሚሰጥ ይሆናል።
በድንበር አካባቢም ቫይረሱ እንዳይስፋፋ በፌዴራል መንግሥት በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ መግባት የተከለከለ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ከሆኑ ደግሞ ለአስራ አራት ቀናት በራሳቸው ወጪ በማቆያ እንዲሰነብቱ እየተደረገ ይገኛል።
ያለውን የአልኮልና ሳኒታይዘር እጥረት ለመቅረፍም ከጤና ጥበቃ ጋር በተደረገ ስምምንት ሁለት ሺ ሊትር አልኮል ከመተሀራ ስኳር ፋብሪካ የተጫነ ሲሆን ውሃ በቦቴ እየቀረበ መሆኑንም በማስታወስ እስካሁን ከኦሮሚያ ተጠርጣራ ከመጣችውና ተመርምራ ነፃ ከሆነች ሴት በስተቀር ምንም ምልክት አለመኖሩንም ጠቁመዋል።
በተያያዘ ዜና የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትም በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዘግቧል፡፡ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በትናንትናው ዕለት በሰጡት መግለጫ የክልሉ መንግሥት ካቢኔ ሥራ አስፈፃሚ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ውሳኔዎችን ማሳለፉን ገልፀዋል። በዚህም መሠረት በክልሉ ከገጠር ወደ ከተማ፤ ከከተማ ወደ ገጠር እንዲሁም ከከተማ ወደ ከተማ የሚደረጉ ዝውውሮች ተከልክለዋል ብለዋል።
ሕዝብ በብዛት የሚሰበሰብባቸው የገበያ ማዕከላት፤ ማህበራዊ ግንኙነቶች የሚከናወንባቸው እንደ ሰርግ፣ ተስካር እና መሰል ክንውኖች እንዲሁም በክልሉ የሚደረጉ የእግር ኳስ ጨዋታዎች የተከለከሉ ሲሆን የንግድ ተቋማት፣ የመዝናኛ ስፍራዎች፣ ጫት ቤቶች፣ የምሽት መዝናኛ ክለቦች እና ሌሎች ሕዝብ በብዛት የሚሰበሰብባቸው ተቋማት እንዲዘጉ መወሰኑንም ጠቁመዋል።
በክልሉ የሚካሄዱ ማናቸውም ስብሰባዎች መታገዳቸውንና የመንግሥት ሠራተኞችን በተመለከተም ነፍሰ ጡር እና የሚያጠቡ እናቶች፣ ዕድሜያቸው ለጡረታ የተቃረቡ እና ለረጅም ጊዜ የቆየ የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች በቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ መወሰኑንም አስታውቀዋል። መንግሥታዊ አገልግሎት የሚሰጡ ቢሮዎችና ጽሕፈት ቤቶችን በተመለከተ በሚያወጡት መርሃ ግብሮች ሥራቸውን የሚያከናውኑ ይሆናል ብለዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ