አዲስ አበባ፡- በሕይወት መስዋዕትነት ባገኘው ድል ተጠቃሚነትን ሳይሆን በአፈና ውስጥ መኖርን ያተረፈው የትግራይ ሕዝብ ከተጫነበት አፈና እንዲላቀቅና ለሌላው የኢትዮጵያ አካባቢ የወጣው የብልጽግና ፀሐይ እዛም እንዲወጣለት እንደሚሰራ የብልጽግና ፓርቲ ተናገረ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አወሉ አብዲ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የትግራይ ሕዝብና እናቶች አሁንም በአፈና ውስጥ ሆነው ዋጋ እየከፈሉ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ቀደም ሲል ትልቅ የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለው ያገኙትን ድል እንዳያጣጥሙ፤ እነርሱ በከፈሉት መስዋዕትነትም ጥቂቶች የቅንጡ ኑሮን እንዲያሳልፉ ሆኗል፡፡ በመሆኑም የትግሉ ፍሬ በአፈና የተተካበት የትግራይ ሕዝብ ከአፈና እንዲላቀቅና ለሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የወጣ የብልጽግና ፀሐይ እዚያም እንዲወጣ ብልጽግና ፓርቲ ያላሰለሰ ትግል ያደርጋል፡፡
እንደ አቶ አወሉ ገለጻ፤ በሕዝብ መስዋዕትነት በመጣ የሕዝብ ድል ተጠቅሞ ለ27 ዓመታት በቅንጦት ሲኖር ሕዝቡን የት ወደቅህ ያላለ አካል ዛሬ ላይ በለውጥ ኃይል ቦታ ሲያጣ ተመልሶ የረሳውን ሕዝብ እንደ መጠጊያ እየተጠቀመው ነው፡፡ በመሆኑም ይሄ ሕዝብ ሕይወቱን ገብሮ ባመጣው መስዋዕትነት ያጣውን ነፃነት እንዲያገኝና ያለተጨማሪ መስዋዕትነት የብልጽግና ጉዞው ተጠቃሚም ተሳታፊም እንዲሆን የማስቻል ተግባር ይከናወናል፡፡ ትግሉ የመጨረሻ ምዕራፍ ትግል ይሆናል፡፡
አቶ አወሉ እንደሚሉት፤ ከህወሓት አባላት አብዛኛው ወደ ብልጽግና ፓርቲ ተቀላቅለዋል፡፡ ይሄን ተከትሎም ህወሓት የራሱን ዕድል በራሱ እንዳቃጠለ ይቆጠራል፡፡ ምክንያቱም በይቅርታና በመደመር ችግሮቻችንን እንሻገር በሚል አዲሱ የለውጥ ኃይል ባቀረበው ጥሪ መሠረት ሕዝብ ተቀብሎ ይቅርታ ቢያደርግም፤ ህወሓት ያንን ባለመቀበል የራሱን መንገድ መርጧል፤ አጣብቂኝ ውስጥም ገብቷል፡፡ አሁን በትግራይ አካባቢ ያለው ሕዝቡን እያፈነና ከአዲስ አበባ የወጣው ኃይልም እዚያ ሆኖ ሕዝቡን እየተጫነ የሚኖርበት ምዕራፍም እያበቃ ነው፡፡ በመሆኑም የብልጽግና አመራር ከአዳዲስ አባላትና ደጋፊዎች ጋር በመቀናጀት በሚደረገው ትግል ሕዝቡን ከአፈና በማውጣት የብልጽግና ፀሐይ እንዲያይ ይደረጋል፡፡
አገራዊ ችግር የሆነውን የኮሮና ወረርሽኝ መመከት ከተቻለና እንደታሰበው ምርጫውን በተቀመጠው ጊዜ ከተካሄደም በምርጫው በማሸነፍ ክልሉ በአዲስ የለውጥ ኃይል የሚመራበትና ሕዝቡም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከአፈና የሚገላገልበት ዕድል ይፈጠራል፡፡ ይሄን በመገንዘብ የለውጥ ኃይሉን የተቀላቀሉት ለሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠታቸው የሚመሰገኑ ሲሆን፤ ገና ያልተቀላቀሉና በመንገድ ላይ ያሉትም ቶሎ ወስነው ወደ ለውጡ መርከብ እንዲቀላቀሉ እና አገር ወደ ብልጽግና በምታደርገው ጉዞ ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ ነው አቶ አወሉ ጥሪ ያቀረቡት፡፡
ለሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ ሰጥተው ለመታገል ብልጽግና ፓርቲን በተቀላቀሉ እውነተኛ የትግራይ ሕዝብ ልጆች የሆኑ ታጋዮችን ስም ማጥፋትና ማዋከብ ሰፊ ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አወሉ፤ ድርጊቱ ሕዝቡን በጠመንጃ ቤት ለቤት እየሄዱ እያስፈራሩና እያፈኑ የሚኖሩበት ሁኔታ መኖሩ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ለውጡን የተቀላቀሉ ኃይሎችንና ሌሎች በክልሉ ያሉ ተፎካካሪ ድርጅቶች ላይ በተደራጀ የአፈና መረብ ታግዞ የሚከናወነው አፈና፣ ዛቻ፣ ድብደባና እስራት ከባድ መሆኑን በመግለጽም፤ ይህ ግን የለውጥ ኃይሉን የተቀላቀሉ ወጣቶችን የበለጠ የሚያተጋ እንጂ የሚያዳክም አለመሆኑን አብራርተዋል፡፡ ምክንያቱም ህወሓት ቀደም ሲልም ታንክና ባንክ ይዞ በለውጡ ኃይል እንደተሸነፈ ሁሉ አሁንም ሕዝብን ከአፈና የማላቀቅና የብልጽግና ጉዞው ባለቤትነቱን ከማረጋገጥ አኳያ የሚደረገው ትግል በድል የሚጠናቀቅ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ አወሉ ገለጻ፤ የሚታየው የህወሓት ተግባር አሸናፊ ሀሳብ የማጣት የተሸናፊዎች ተግባር ሲሆን፤ ይሄም ለውጥን ካለመፈለግ የሚመጣና መዳረሻን ካለማወቅ የሚወለድ ሽንፈት ነው፡፡ እነርሱ እንደሚሉት ማንኛውም የጸረ ሰላምና ጸረ ዴሞክራሲ መንገዳቸውን ያልተከተለና ያልተቀበለ ሰው ባንዳ ነው፡፡ ይሄንንም ሕዝቡ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ይህን ተከትሎም ሕዝቡም፣ ወጣቱም፣ የንግዱ ማህበረሰብም ከብልጽግና ጎን መሆኑን አሳይቷል፡፡ የራሳቸው አመራሮችም ቢሆኑ ከግማሽ በላይ ወደብልጽግና ተቀላቅለዋል፡፡
በመሆኑም ህወሓትና የትግራይ ሕዝብን አንድ ለማድረግ በመሞከር የሚደረግ ጥረት የተበላ ቁማር መሆኑንም መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም የትግራይ ሕዝብ በፊትም የተጨቆነ፤ ላለፉት ዓመታትም እነርሱ ሲዘርፉና ሲበለጽጉ በነበረበት ጊዜ ሕዝቡ በድህነትና በጭቆና ውስጥ ሆኖ በእነርሱ ስም የተገፋ ሕዝብ ነው፡፡ እናም ሕዝቡ አሁን ነፃነቱን ይፈልጋል፡፡
ይሄን ነፃነቱን የሚወስንበት ምርጫም ከፊቱ ስላለ ህወሓት ስላለ ብቻ የሚሆን ነገር አይደለም፡፡ አሁን በብልጽግና ውስጥ ሆነው የሚታገሉትም የዚሁ ነፃነት ፈላጊ ሕዝብ የቁርጥ ቀን ልጆች እንደመሆናቸውም፤ ሕዝቡ ከእነዚህ ልጆቹ ጎን በመሆን ሊያግዛቸውና የሚደርሰውን ጭቆና በቃ ሊል ይገባል፡፡
ህወሓት እስከዛሬ የሌለውን የተሻለ ሀሳብ ስለማያመጣ ከዚህ በኋላ ሕዝብን በመሸሻነት የሚጠቀሙበትን አካሄድ በቃ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ብልጽግና ፓርቲም ከሕዝቡ ጎን ሆኖ የቻለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2012
ወንድወሰን ሽመልስ