አዲስ አበባ፡- በህዳሴው ግድብ ውሃ አሞላልና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሚደረጉ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ ባለመጠቀሟ እያጋጠማት ያለው ጉዳት ግምት ውስጥ እየገባ አለመሆኑን ኡስታዝ አህመዲን ጀበል ገለጸ፡፡
ኡስታዝ አህመዲን ጀበል የአባይ ወንዝ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ዙሪያ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፀው፤ በአባይ ወንዝ አጠቃቀም፣ በህዳሴው ግድብ ውሃ አሞላልና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሚደረጉ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ሥራዎች የሚያተኩሩት በፍትሀዊ ተጠቃሚነት እንጂ እስካሁን ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ ባለመጠቀሟ እያጋጠማት ያለውን ጉዳት ግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም፡፡
ግብጾች ለሕዝባቸውም ሆነ ለሌሎች አገራት የአባይ ወንዝ የእነሱ ብቻና የህልውናቸው መሠረት አድርገው በማቅረብ የተሳሳቱ መረጃዎችን ሰጥተው ሃቅን አዛብተዋል ያለው ኡስታዝ አህመዲን፤ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ሥራዎች ውሃውን የምታመነጨው ኢትዮጵያ ወንዙን ባለመጠቀሟ የምትጎዳው ጉዳት ግምት ውስጥ እየገባ አይደለም ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ እስካሁን የአባይን ወንዝ ተጠቅማ ልማት ባለማካሄዷ ሕዝቦቿ በጨለማ፣ በተደጋጋሚ ድርቅና ርሀብ የምትጠቃ መሆኑን ጠቁሞ በአንጻሩ አባይ ውሃን ተጠቅመው ባካሄዱት ልማት ከራሳቸው ፍጆታ አልፈው አትክልቶች፣ ፍራፍሬዎችና ሌሎች የግብርና ምርቶችን ወደ አረብ አገራት የሚልኩት ግብጻውያን ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ወንዝ ግድብ ገነቡ ብለው መብከንከናቸው ተገቢም፤ ሚዛናዊም አይደለም ብሏል፡፡
ኡስታዝ አህመዲን እንደገለፀው፤ ግብጾች ኢትዮጵያ በአባይ ውሃ እንዳትጠቀም የተለያዩ ጫናዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ሕዝባቸውንም ሆነ ሌሎች አገራትን የተሳሳቱ መረጃዎችን ሰጥተው ወንዙ የነሱ ብቻና ሙሉ ለሙሉ መብት ያላቸው እነሱ እንደሆኑ አድርገው ቀርጸዋል፡፡
«ግብጾች የወንዙ መነሻ የሆነችው ኢትዮጵያ በውሃው የመጠቀም መብት እንደሌላት አድርገው በስፋት ማቅረባቸው ስህተት መሆኑን ብዙ ግብጻውያንና አገራት አይረዱትም» ያለው ኡስታዝ አህመዲን፤ ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ ፍትሀዊ የመጠቀም መብቷን እንዳነሳችና እስካሁን ባለመጠቀሟ የደረሰባትን ጉዳትና የከፋ ድህነት ቁልጭ አድርጋ በማሳየት ረገድ ለአረብ ሊግ አባል አገራትም ሆነ ለዓለም ማህበረሰብ በቂ የዲፕሎማሲ ሥራ እንዳልሰራች ገልጿል፡፡
ግብጽ የአረቡ ዓለም ኢትዮጵያ ላይ በአሉታዊ ምስል እንዲኖረው ማድጓን አመልክቶ፤ በተለይ ኢትዮጵያ የክርስቲያን አገር እንደሆነች፣ የእስራኤል ቀኝ እጅ ሆና ግብጻውያንን ለመጉዳት የምትንቀሳቀስ አገር መሆኗን፣ ኢትዮጵያ ብዙ ወንዞች እያሏት ሆን ብላ ግብጻውያንን ለመጉዳት አባይ ላይ ግድብ እየገደበች መሆኑንና ኢትዮጵያ ውስጥ የጎላ ቁጥር ያለው ሙስሊም እንደሌለ በማስመሰል የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ዓረቡን ዓለም ከጎኗ ማሰለፍ መቻሏን ጠቅሷል፡፡
ግብጻውያን «ሀበሻ» የሚለውን የኢትዮጵያ የቀደመ ስያሜ እንደማይጠቀሙ የጠቀሰው አቶ ኡስታዝ አህመዲን፣ ይህንን ማድረግ ቢላል፣ ነጃሽና ሌሎች በእስልምና ታሪክ የጎላ ሚና የነበራቸውን ዜጎች ስለሚያስታውስ በዓረቡ ዓለም ተቀባይነት አያገኙም ነበር ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለአረቡ ዓለምና ለእስልምናው የዋለችውን ውለታ፣ በውሃ ጉዳይ ላይ ሃይማኖቱ ምን እንደሚል አንስቶ ግብጽን መሞገት ይቻላል ያሉት ኡስታዝ አህመዲን፣ ግብጾች ለብዙ ዘመናት በውሃው እየተጠቀሙ ከድህነት ወጥተዋል፣ በአንጻሩ ኢትዮጵያ በወንዙ ሳትጠቀም በመቅረቷ ከድህነት አልወጣችም፤ ይህን ዘመን ሁሉ የተጠቀመችው ግብጽ ገና ኢትዮጵያ ግድብ በመገደቧ ውሃው ይቀንስብኛል ብላ ጩኸት ማሰማቷ በሃይማኖቱም ሆነ በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መርህ ፍትሀዊ፣ ሚዛናዊም ተገቢም አይደለም ብሏል፡፡
በኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብና በአባይ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ የሚሰሩ የሚዲያ ሥራዎች በቂ አለመሆናቸውንና በአገር ውስጥ ቋንቋዎች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ገልጾ በዓረቡ ዓለም ኢትዮጵያ ፍትሀዊ የውሃ አጠቃቀም መብት ያነሳች መሆኑን አረብ ሚዲያዎችን ተጠቅማ የግብጽ በተሳሳተ መረጃና በኢትዮጵያ ላይ የፈጠረችውን አሉታዊ ምስል ለማስተካከል መስራት እንዳለባት ምክረ ሀሳብ አቅርቧል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአረብኛ ቋንቋ የሚመረቁ በርካታ ወጣቶችን ኢትዮጵያ በማፍራት ላይ መሆኗን ገልፆ በራሳቸው ተነሳሽነት የአረቡ ሚዲያ በመጠቀም ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ዙሪያ ያላት አቋም ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ መሆኑን የማሳወቅ ሥራ እየሰሩ የሚገኙ ግለሰቦች ቢኖሩም የዓባይን ጉዳይ ቋሚ አጀንዳው ያደረገና የአረብኛ ቋንቋንና የአረብ አገሮችን ኢላማ ያደረጉ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን የሚያቀርብና ዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን የውሃ ባለቤትነትና ፍትሀዊ የውሃ ተጠቃሚነት መርህ የሚያሳውቅ ተቋም ማቋቋም እንደሚያስፈልግ ኡስታዝ አህመዲን ተናግሯል፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት በህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ብልሹ አስተዳደር ማጋጠሙና በሚዲያ የቀረበበት መንገድ በኅብረተሰቡ ዘንድ አሉታዊ ስሜት መፍጠሩን ያነሳው ኡስታዝ አህመዲን፤ እንደዚህ ያሉ አገራዊ አጀንዳዎች ይበልጥ በቁርጠኝነት የሚሰሩ እንጂ የሕዝቡን ስሜት የሚጎዱ መሆን የለባቸውም ብሏል፡፡
ኅብረተሰቡ ነገ ብዙ ጥቅም የሚያገኝበት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ቶሎ እንዲጠናቀቅ በባለቤትነት ስሜት ከመዋጮ አንስቶ ለግድቡ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ረገድ የድርሻውን መወጣት እንዳለበትና መንግሥትም በህዳሴው ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ዙሪያ በሚደረጉ ድርድሮች ሕዝቡን እያሳተፈና የተጋጋለውን ሕዝባዊ ድጋፍ ደጀን አድርጎ መስራት እንዳለበት አመልክቷል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2012
ጌትነት ምህረቴ
ремонт iphone москва
Поклонникам творчества Игоря Талькова, не пропустите!
По ссылке вы найдете легендарную
композицию “Я Вернусь” Игоря Талькова Игорь Тальков Я Вернусь.
Переживите момент ностальгии
прямо сейчас!
tFj pBN