መደበኛ ባልሆነ በጎዳና ላይ በሚነግዱና ደንብ አስከባሪዎች መካከል የሚስተዋለው አባሮሽና ድብብቆሽ ልጅነቴን ያስታውሰኛል። ቀልብ መሳቡን አመሳሰልኩት እንጂ በእነርሱ ላይ የሚደርሰውን የከፋውን አባሮሽ ማለቴ አይደለም። አሳዳጅና ተሳዳጅ ሲባረሩ መንገደኛው ያዘው፣ አልያዘው እያለ በመሳቀቅ ቆሞ ይመለከታል። የተለያየ አስተያየትም ይሰጣል። ትዕይንቱ ለንግድ የያዙትን ዕቃ በመቀማት ወይም ለመኪና አደጋ በመጋለጥ የሚጠናቀቅበት ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ ጉዳዩን አሳዛኝ ያደርገዋል። የሚገርመው የከፋ ነገር በሚያጋጥመው የጎዳና ንግድ ከቀን ወደ ቀን ቁጥሩ እየጨመረ መሄዱ ነው። በተለይ የሕዝብ ፍሰቱ በበዛበት ኮልፌ፣ መገናኛ፣ ጀሞ አካባቢዎች ችግሩ መባባሱን የከተማዋ አስተዳደርም ተገንዝቧል።
መደበኛ ያልሆነ የጎዳናን ንግድ አስገራሚ የሚያደርገው ሌላው ትዕይንት በመዲናዋ የመሪዎችና ትላልቅ ስብሰባዎች ሲካሄዱ ያ ጎዳናውን ዘግቶ የሚያጨናንቀው የጎዳና ላይ ነጋዴ ደብዛው ይጠፋል። ጎዳናው ረጭ ይላል። ሁከትና ግርግሩ ምን ያህል ተጽዕኖ እንዳለው የሚረዱት በዚህ ወቅት ነው። ጥያቄው ለተወሰነ ቀን መከላከል የሚቻለው የጎዳና ላይ ንግድ ቁጥጥርቸ ለምንስ ዘላቂ ማድረግ አልተቻለም? ይህን መፍትሄ ያጣውን ጉዳይ ይዘን የተለያዩ በሮችን አንኳኩተን የተለያዩ ትዝብቶችንና የመፍትሄ ሀሳቦችን ሰብስበናል። አካባቢዎቹ ለአብነት ተጠቀሱ እንጂ በመዲናዋ የትኛውም አካባቢዎች ችግሩ ተመሳሳይ ነው።
ሀሳባቸውን ካካፈሉን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መካከል መገናኛ አካባቢ ነዋሪ የሆነችው ወይዘሪት ትዕግሥት ከበደ አንዷ ናት። በደንብ አስከባሪዎች ሲባረር በመኪና አደጋ አካሉንም ንብረቱንም ያጣውን ታዳጊ በማየቷ የጎዳና ላይ ንግድን አምርራ ትቃወማለች። በአንድ ጊዜ ለሁለት ጉዳት መጋለጣቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከደንብ አስከባሪዎች ለማምለጥ ሲሮጡ አቅመ ደካሞችንና ሕፃናትን በመጣል መጎዳታቸው፣ መተላለፊያ መንገድ መዝጋታቸው፣ የድምጽ ብክለትም ማስከተላቸው በአጠቃላይ እነርሱም ተረጋግተው ባለመነገዳቸው፣ እግረኛውም እንደ ልቡ መሄድ አለመቻሉና ጥራት ለሌላው ንግድ መጋለጡ፣ ለከተማዋም ገጽታ ምቹ ሆኖ አላገኘችውም።
ወይዘሪት ትዕግሥት መደበኛ ያልሆነ የጎዳና ላይ ንግድ መስፋፋት ከመንግሥት አቅም በላይ ነው የሚል ዕምነት የላትም። በቂ ግንዛቤ ቢፈጠርና የሚሰሩበት ቦታ ቢያመቻችላቸው፣ ሸማቹም የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ ቢችል ጉዳዩ መነጋገሪያ አይሆንም ነበር ትላለች። ‹እኔ ደመወዝ የሚከፈለኝ፣መሠረተ ልማት የሚሟላልኝ ከግብር ከፋዩ በሚሰበሰበው ግብር ነው ብዬ ስለማምን በግሌ በጎዳና ላይ ካለደረሰኝ የሚሸጥ ሕጋዊ ያልሆነ ዕቃ ባለመግዛት አስተዋጽኦ አደርጋለሁ› በማለት ተሞክሯን አካፍላለች። ለምትገዛው ዕቃም አስተማማኝ ዋስትና ለማግኘት ከሱቅ መግዛት እንደምትመርጥም ትገልጻለች።
‹ዳናት ኮስሞቲክ› የሚል ስያሜ ባለው የአልባሳት፣ ጌጣጌጦችና ቅባቶች መሸጫ ውስጥ ያገኘናት ወይዘሪት ቤተልሄም አባይነህ ደንበኞቿ ወደ ሱቋ መግቢያ እስኪያጡ ድረስ መንገድ ዘግተው በሚረብሽ ድምጽ እየጮኹ ሲሸጡ ትበሳጫለች። ድርጊቱንም ከድፍረት ትቆጥረዋለች። እርሷ እንደምትለው በመሀል ከተማ ላይ የሰለጠነ የንግድ ሥርዓት አለመኖሩ ከተማዋ ውበት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል።
እርሷ የምትይዛቸውን አልባሳትና ጌጣጌጦች ይዘው ከረፋዱ አምስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽት በሱቋ ደጃፍ ላይ ሆነው በመሸጥ ዓይኗ እያየ ደንበኞቿን መውሰዳቸው ቢያስቆጫትም ጉዳዩ የጎዳና ላይ ንግድን ከሚከላከሉት ደንብ አስከባሪዎችም በላይ ስለሆነ ከመቀበል ሌላ አማራጭ የላትም። ሕግ አስከባሪ አለመኖሩ ተስፋ አስቆርጧታል። አሁን አሁን መደበኛ ያልሆነ የጎዳና ላይ ንግድ ሕጋዊ እስኪመስላት ድረስም ማማረሩን ብትተወውም እርሷ በሕጋዊ ፈቃድ በደረሰኝ እየሸጠችና የግብር ግዴታዋንም እየተወጣች በጎዳና ላይ የሚነግዱት በቸልታ መታለፋቸው አግባብ እንዳልሆነ ሀሳቧን ሰጥታለች።
‹ጆሲ ሜንስ ፋሽን› የሚል መጠሪያ ወዳለው የወንዶች ጫማ፣ ሙሉ ልብስና ሸሚዝ መሸጫ ሱቅ ጎራ አልን። በሱቁ ያገኘናቸው አቶ ያሲን ከድር በተለየ መልኩ ነበር ሀሳባቸውን ያካፈሉን። እርሳቸው ከጎዳና ላይ ንግዱ ይልቅ ሥራ ስርቆትና ልመና ላይ የተሰማራው ነው የሚያሳስባቸው። ሰው ከሰራ ወደ ስርቆትም ሆነ ወደ ሕገወጥ ድርጊት አይገባም ብለው ያምናሉ። ሌላው የጎዳና ላይ ንግድ ያላስጨነቃቸው እርሳቸው የሚይዟቸውን አልባሳትና ጫማ ስለማይዙና ደንበኞቻቸውም የተለዩ በመሆናቸው ነው። ዛሬ የትላልቅ ሱቅ ባለቤት የሆኑት ከአነስተኛ ንግድ ተነስተው በመሆኑ ቢበረታቱ ይመርጣሉ። የከተማ ገጽታ እንዳይበላሽ ለሚለው ግን የመፍትሄ ሀሳብ አልሰጡም። የሚመለከተው አካል መፍትሄ እንዲፈልግ ነው የጠቆሙት።
መደበኛ ያልሆነ ንግድ ላይ ከተሰማሩትም ከአብዛኞቹ አስተያየት የተረዳነው የጎዳና ላይ ንግድ ተረጋግቶ ለመስራት ምቹ እንዳልሆነና ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ነው። ቦታ እንዲሰጣቸው በየሚኖሩበት ቀበሌም ጥያቄ እያቀረቡ እንደሆነም ገልጸውልናል።
ከመኖሪያው ኮልፌ ቀራኒዮ ፒያሳ አካባቢ በጎዳና ላይ ዘርግቶ አልባሳትን ሲሸጥ ያገኘነው ወጣት መሐመድ አብዱርዋሂድ አማራጭ በማጣቱ በጎዳና ላይ ለመነገድ እንደተገደደ ይናገራል። በሚኖርበት ቀበሌ የመሸጫ ቦታ እንዲሰጠው በተደጋጋሚ እንደጠየቀና በተያዘው ዓመትም በሚኖርበት ቀበሌ ተደራጅተው እንዲቀርቡ በሰጣቸው መመሪያ መሰረት ሦስት ሆነው ተደራጅተው በቀበሌው በተዘጋጀ ፎርም ላይም ሞልተው በመስጠት ምላሽ እየተጠባበቁ እንደሆነ ያስረዳል። በቀበሌው ያለውን ውጣ ውረድና የኪራይ ሰብሳቢነት አካሄድ ግን ቦታ ማግኘቱን እንዳላፋጠነለት ያስረዳል። በመመላለስ የሚያጠፋው ጊዜ ከሥራው ስላስተጓጎለው ተስፋ በመቁረጥ በጎዳና ንግዱ ቀጥሏል።
ወጣት መሐመድ እንደሚለው ብዙ ዕቃ ይዞ መጓጓዝ ስለማይቻል ብዙ አይሸጥም። ፀሐይና ብርድ፣ ደንቦች ቀሙኝ አልቀሙኝ ብሎ መሳቀቅ፣ ሲሯሯጡ ለመኪና አደጋ መጋለጥ፣ በአጠቃላይ የተረጋጋ ሥራ ባለመሆኑ የጎዳና ላይ ንግድን አይመርጠውም። መኖር ስላለበት ደግሞ የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች ለመጋፈጥ ተገዷል። እንደመፍትሄ ያቀረበውም የሚኖርበት ቀበሌ የንግድ ቦታ እንዲሰጠው ነው። የጎዳና ላይ ንግድ በከተማዋ ገጽታ ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ገጽታን በተመለከተ የሌሎቹን አስተያየት ሰጪዎች ሀሳብ ይጋራል።
ደንብ ማስከበር እያልን የምንጠራቸው በቡድን ሆነው የጎዳና ላይ ነጋዴዎችን ሲያባርሩና ዕቃዎቻቸውንም ሲቀሙ እንታዘባለን። ሥራቸው ምን ያህል የተሳካ እንደሆነ ከአትክልት ተራ ወደ ፒያሳ በመዘዋወር ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ካገኘናቸው መካከል በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት የመስክ ክትትልና ቁጥጥር ኦፊሰር አቶ ሉቃስ መርድን ስለ ሥራቸው ጠይቀናቸው ሥራው የጥረታቸውን ያህል ውጤት እንዳላስገኘላቸውና ፈታኝ እንደሆነባቸውም ነበር ምላሽ የሰጡን።
ነጋዴዎቹ ቀድመው ስለሚጠነቀቁ በርቀት ሲያዩዋቸው እንደሚሸሹና በዚህ ወቅትም መሸሻቸውን እንጂ የሚያጋጥማቸውን አደጋ እንደማያዩ፣ ዕቃቸውም እንደሚወድቅባቸው ይገልጻሉ። ምንም እንኳን የከፋ አደጋ ሲደርስ ባያጋጥማቸውም መውደቅና መሰበር፣ ለመኪና አደጋም መጋለጥ እንደሚኖር ይገምታሉ። በአንድ በኩል ተከላክለው ዞር ሲሉ በሌላ በኩል ተመልሰው ዘርግተው ይሸጣሉ። አብዛኛው ኅብረተሰብም እነርሱን በመደገፍ ‹ምን ሰርተው ይብሉ፣ ልቀቁ› የሚሉ የተለያዩ አስተያየቶችን በመስጠት እንደሚቃወሟቸውም ይናገራሉ። ነጋዴዎቹም ዕቃቸው ሲወረስባቸው ስለሚሰድቧቸው ሥራው ፈተና ይበዛበታል። በአንድ ፈረቃ የሚሰማራው የመስክ ክትትልና ቁጥጥር ኦፊሰር ቁጥር እስከ 22 እንደሆነና ካለው ሰፊ የጎዳና ላይ ንግድ ከሰው ኃይሉ ጋር እንደማይጣጣምም ያስረዳሉ። ችግሩ በአንድ አካል ቁጥጥርና ክትትል ብቻ ይፈታል የሚል እምነት የላቸውም።
የጎዳና ላይ ንግድ ሌላም አስከፊ ገጽታ እንዳለው የሚገልጹት በአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ መደበኛ ያልሆነ ንግድ ሥርዓት ማስያዝ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዳኛቸው ሉሌ ናቸው። መደበኛ ያልሆነ ንግድ ዜጎች የሚተዳደሩበት ሲያጡ የሚሰማሩበትና በተለያዩ ሀገራትም የተለመደ መሆኑንም ይጠቅሳሉ። ይህ ሲባል ግን በመዲናዋ አሁን የሚታየውን ሥር የሰደደና ሥርዓት ያጣ ዓይነት እንዳልሆነ ይገልጻሉ። እርሳቸው እንደሚሉት መደበኛ ያልሆኑ ነጋዴዎች የሚይዟቸው አልባሳት አብዛኞቹ የኮንትሮባንድ ውጤቶች ሲሆኑ በከፊል ደግሞ መደበኛ ከሆኑ ነጋዴዎች የሚረከቧቸው ናቸው። የተሰረቁ አልባሳትም ተቀላቅለው እንደሚሸጡ ተደርሶበታል። ሥራ አጥ ዜጎች በዝተዋል በሚልም ለፖለቲካ ፍጆታ የሚቀርብበት አጋጣሚም እየተፈጠረ በመሆኑ ለዘርፈብዙ ችግሮች የተጋለጠ ነው።
የጎዳና ላይ ንግድ ቅጥ አጥቶ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ለመድረሱ ሀገሪቷ ላይ ከሁለት ዓመት በፊት የተደረገው የሥርዓት ለውጥ ከመምጣቱ በፊት የነበሩ አመራሮችም ተጠያቂ ናቸው። ከመካከላቸውም አልባሳትን በማቅረብ ላይ የሚሳተፉም ነበሩ። ሌላው አሳዛኝ ነገር ዕድሜያቸው ለሥራ ያልደረሱ ታዳጊዎችም በንግዱ ውስጥ መኖራቸው ኢትዮጵያ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛን ለመከላከል የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ሕጎችም መጣሳቸው ነው። የተለያዩ ሀገራት መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሥርዓት የሌለው ንግድ መካሄዱም የከተማዋን ንጽህና ከማጉደፉም በላይ ለትችት መዳረጓ ችግሩ በተለያየ መልክ እንዲገለጽ አድርጎታል።
እንደ አቶ ዳኛቸው ገለጻ፤ ቢሮው በሥራ ዕድል ፈጠራ ስም በመዲናዋ ጎዳና ላይ ድንኳን ጥለው የሚነግዱትም ከቢሮው እውቅና ውጪ በመሆናቸው ሕገወጥ ናቸው። ዜጎች ጥሪት ይዘው መደበኛው የንግድ ሥርዓት ውስጥ እስኪገቡ ድረስ በሰዓትና በቀናት በተከፋፈለ ንግድ የሚያካሂዱበትን ቦታ በማመቻቸት የሚያግዛቸውን ብቻ ነው በቢሮው እውቅና ያላቸው። በአንድ በኩል የግብር ግዴታውን እየተወጣ፣ በሌላ በኩል ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚካሄደው የጎዳና ላይ ንግድ የንግድ ሥርዓቱን ዝብርቅርቅ አድርጎታል። በመዲናዋ መደበኛ ባልሆነ በስፋት በመከናወን ላይ ያሉት የአልባሳት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የሰብል ምርቶች ንግድ ማሳያ ናቸው። ንግድን ለማዘመን በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይም ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ በማድረስ ላይ ነው።
ቢሮው በአዲስ ተደራጅቶ ችግሩን ለመፍታት በጥናት የተደገፈ የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ የመፍትሄ አቅጣጫ ዕቅድ ነድፎ መንቀሳቀስ ከጀመረ አንድ ዓመት ከስድስት ወር አስቆጥሯል። ችግሮቹን ከመለየት ጀምሮ ሥርዓት ለማስያዝ ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከጽዳት ውበትና መናፈሻ፣ የሥራ ዕድል ከሚፈጥሩ ተቋማትና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር ተናብቦ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ በመፈረምና በመነጋገር የጋራ መፍትሄ ለማምጣት በመስራት ላይ ይገኛል።
ቢሮው በንግድ ዘርፍ ውስጥ የሚገኙት ስለሚነግዱት ዕቃና ከየት እንደሚያስመጡ መታወቅ ስላለበትና በሕጋዊ መንገድ ሰርተው የሚጠበቅባቸውን ግብር እንዲከፍሉ ባደረገው ጥረትም ባለፉት ጊዜያት መደበኛ ባልሆነ ንግድ ላይ የተሰማሩ 58ሺ6 ሰዎች መዝግቧል። ከነዚህ ውስጥም ለ19ሺ 600 ሰዎች የመሸጫ ቦታ፣ የሽግግር ጊዜ ፈቃድና የግብር መክፈያ (ቲን ነምበር) በመስጠት ወደ ሥራ አስገብቷል። ሕጋዊ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ መለያ(ባጅ)ተሰርቶ ተሰጥቷቸዋል። የቢሮው ባለሙያዎችም ነጋዴዎቹ ሕጉን አክብረው መንቀሳቀሳቸውን በመከታተልና በማረም ያግዟቸዋል። መደበኛ ባልሆነ ንግድ ላይ የተሰማሩትን ብዛት ማወቅ የሚቻለው ምዝገባ በማካሄድ በመሆኑ በቀጣይም ምዝገባ ለማካሄድ ቢሮው ተዘጋጅቷል። ባለው ተሞክሮ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የቁም እንስሳት ንግድ ወቅትን የተከተሉ በመሆናቸው ለመለየት አያዳግትም።
ቢሮው በረጅም ጊዜ ዕቅዱ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ከተማ በሚያስገቡ በአምስቱም በሮች አካባቢ የቁም እንስሳት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የግብርና ምርቶች መገበያያ ማዕከላት ለመገንባት ሲሆን፣ እንቅስቃሴውንም ጀምሯል። ማዕከላቱ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ለመፍጠር እንዲሁም ሸማቹንና አምራች አቅራቢውን በሚያገናኝ ሁኔታ ምቹ ሆነው የሚገነቡ በመሆናቸው ችግሩን ይቀርፋል የሚል እምነት ተይዟል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ግን በጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራውና በሀገር ደረጃ የተነደፈው የሥራ ዕድል ፈጠራ ዕቅድ ሙሉ ለሙሉ ተተግብሮ ለውጥ ሲመጣ ሥራ ፍለጋ በሚል ሰበብ ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት መቆም ሲችል እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ዳኛቸው፣ ቢሮው መደበኛ ባልሆነ ንግድ ላይ የሚሰማሩት ከየትኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ወደ መዲናዋ የሚመጡ እንደሆኑ በመለየት ከክልሎች ጋር ምክክር በማድረግና በሥልጠናም ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነ አመልክተዋል። ሥራዎች በዚህ መልኩ ከቀጠሉ አዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚስተዋለው ጫና ይቀንሳል የሚል እምነት አላቸው።
ኅብረተሰቡ አጋጣሚ በማግኘቱና ርካሽ ነው በሚል እሳቤ ብቻ የጎዳናውን ዕቃ ከጎዳና ላይ ገዝቶ መጠቀሙም ጉዳት እንደሆነ በማስገንዘብ በኩል ቢሮው እንደሚቀረውና ቀጣይ ተግባሩም እንደሆነ ገልጸዋል። የግንዛቤ ሥራውን በወጣት፣ በሴቶችና በሌሎች ኅብረተሰቡ ጋር ተደራሽ በሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በመያዝ ለመስራት መታቀዱንም ተናግረዋል። ቢሮው መደበኛ ባልሆነ ንግድ ላይ የተሰማሩትን ቁጥር ለማወቅም በቅርቡ ምዝገባ በማካሄድ ለመለየት ዝግጅት ላይ ይገኛል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2012
ለምለም መንግሥቱ