የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ማደግ የሚችለው ጠንካራ የሥራ ባህል፣ ቅንነት፣ አስተዋይነትና አርቆ አሳቢነት በተሞላበት አስተሳሰብና ነገን በሚያልም ማህበረሰብ ሲገነባ ነው። የአደጉ ሀገራት የብልፅግና ምስጢራቸውም ይኸው ባህላቸው እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ። አሜሪካ የዓለም ኃያል ሀገር ልትሆን የቻለችው 24 ሰዓት መስራት የሚችል፣ ጊዜውን በዋዛ ፈዛዛ ሳይሆን በሥራ የሚያውል ማህበረሰብ መፍጠር መቻሏ፤ በኢኮኖሚውም ሆነ በሌላው ጉዳይ የዓለም ቁንጮ ሆና ከፊት እንድትመራ አስችሏታል።
በኢኮኖሚ አሜሪካን እየተገዳደረች የምትገኘው ቻይናም ሌላዋ ጠንካራ የሥራ ባህልን ያዳበረች ሀገር በመሆን እየተፎካከረች ትገኛለች። ቻይና የኢትዮጵያ ዋና የልማት አጋር በመሆን በተለይ በልማታዊ እንቅስቃሴዋ ሰፊ ድርሻ ያላት ሀገር በመሆን በቀዳሚነት ተቀምጣለች። በተለይም የተለያዩ የመንገድ ግንባታዎችንና ሕንፃዎችን በመገንባት ትልቅ የልማት አጋራችን ናት። በኢትዮጵያ መንገዶችንም ሆነ ሕንፃዎችን በምትገነባበት ወቅት እያንዳንዱ ተቋራጭ የመጣበትን ግዛት ሻንጋይ፣ ህዋን፣ ቤንጂንግ፣ ሆግ ኮንግ፣ ህዋንግዙና የመሳሰሉት ግዛቶቿን የሚያስተዋውቁ አምባሳደሮች አሏት። እነዚህ ተቋራጮች ግዛቶችን ብቻ ሳይሆን ቋንቋዎቻቸውንና የሥራ ባህላቸውን ጭምር ያስተዋወቁት። ቻይና የኢትዮጵያ ቁልፍ አጋር ስለሆነች ለአብነት አነሳን እንጂ ሌሎችም ሀገሮች ለሀገራቸው የቻሉትን ያስተዋውቃሉ።
በቱርክ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ሆኖ እየሰራ የሚገኘው የጓደኛዬ ወንድም ያጫወተኝን ማስታወስ ወደድኩ። ቱርክ አንድ የልብስ መደበር ገብተህ የአቅምህን ልብስ ስትገዛ እንደገዛኸው የልብስ መጠን አንድ ወይም ሁለት ልብስ ቦነስ ይሰጥሃል አለኝ። ይህን የሚያደርጉት ለራሳቸውም ሆነ ለሀገራቸው ቁልፍ የሆነ አላማ ስላላቸው ነው ሲል አጫወተኝ። ለምሳሌ ሁለት ሱፍ ስትገዛ አንድ ሸሚዝ ይመርቁልሃል። ይህም ቀጣይ ሌሎች ደንበኞችን ለመሳብና ለሀገራቸው መልካም አመለካከት እንዲኖርህ በማሰብና መልካም ገፅታ በመገንባት ዲፕሎማት በመሆን ያገለግላሉ።
የሀገራችን የንግድ ባህል ግን ከውጭው ዓለም በእጅጉ የተለየ ይመስላል። እንኳን ቦነስ ይቅርና ሱቅ ገብቶ መልካም ፊት አይቶ መውጣት የምንናፍቅበት ጊዜ ደርሰናል። አንድ ሰው ጫማ ወይም ሱሪ ለመግዛት ወደ አንድ የልብስ መደበር ይገባል። ከዚያም የፈለገውን ጫማ ይመርጣል። ነጋዴው ልብስ ወይም ጫማ ለማሳየት ፍላጎት አይታይበትም። ይልቁ ንም የለበሰውን ጫማና ሱሪ ይመለከትና ከሱቁ ካለው ጋር መመጣጠን ካልቻለ ሹፈት ይጀመርና እንዲወጣ ያደርገዋል። አንዳንዶች ልብሱን ወይም ጫማውን ካስመረጡ በኋላ ብር ለመክፈል ሲዘጋጅ የመረጠውን ሳይሆን ሌላ ቀይረው ይሰጣሉ። ‹‹አረማመዱን አይተው ዱላውን ይቀሙታል›› ማለት ይህ ነው። ለመቀየር ሲመለስ ስድብ አለፍ ሲልም ዱላ ይጋበዙበትና ነፍሴን አውጭኝ ብሎ ወደቤቱ እንዲመለስ ያደርጉታል።
ወደ አንድ ቦታ ለሥራ ያቀና ጓደኛዬም ለዚሁ ሀሳብ ማጠናከሪያ ነገረኝ። ባለው ውስን ሰዓት የከተማውን የንግድ እንቅስቃሴ ለመቃኘት ዕድሉ ገጠመውና አንድ ሱቅ ገባ። ‹‹ሱቁ ውስጥ የተቀመጠ ሻጭ ባለመኖሩ ዞር ብዬ በዓይኔ ፍለጋ ገባሁ›› አለኝ። ከርቀት ምንድን ነው? ምረጥ የሚል ድምፅ ሰምቶ ሲመለከት የሱቁ ባለቤት የተቀመጠው አስፓልት ማዶ ከጎረቤቶቹ ጋር እያወራ ነው። እሱም ከገባሁ አይቀር በሚለው ጫማ መርጦ አንስቶ አሳየው፣ ‹‹600 ብር›› ብሎ ዋጋውን ሲነገረው ‹‹መጨረሻውስ?›› ሲለው ‹‹አዎ መጨረሻው ነው፤ ካልከፈለክ ውጣ›› የሚል ምላሽ የሚሰጡ በርካታ ናቸው። ይህ ለሀገራችን ኢኮኖሚ አለማደግ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ስንቱ ታዝቦ ይሆን? የውጭ ሀገር ነጋዴዎች ለሀገራቸው አምባሳደር ሲሆኑ የሀገራችን ግን ‹ሆድ አደር› የሆኑ ናቸው ብል ስድብ እንዳይሆብኝ ይቅርታ ይታከልበት።
በሀገራችን ከፍ ዝቅ የሚለቀው የኢኮኖሚ ሁኔታ የዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ጫና አሳድሯል። የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ በሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ ባህር ማዕበል ወጀብ አስነስቷል። በተለይም ምክንያታዊ ያልሆነ የነጋዴዎች የዋጋ ጭማሪ ነዋሪዎችን ግራ አጋብቷል ይላሉ። አሁን ላይ ታክሲ ላይም የአንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም ትራንስፖርት አምስት ብር ሆኗል። መልስ ከጠየክ ተስቆብህ የሚሰጥህ ምላሽ ‹‹ጤፍ አራት ሺ 500 ሲገባ የት ነበርክ?›› ብለውህ አፍህን ያስይዙሀል።
ስለነጋዴዎቻችን እና ንግድ ካነሳን አይቀር ወቅታዊውን ትዝብት ላጋራችሁ። ካሳለፍነው ታኅሣሥ ወር መጨረሻ ጀምሮ በቻይና ህዋን ግዛት የተቀሰቀሰው ኮሮና ቫይረስ ከቻይና በማለፍ ዓለምን ያስጨነቀ መሆኑ የሚሰወርበት ሰው ያለ አይመስለኝም። ይህ ቫይረስ ታዲያ የአውሮፓ ሀገራትን አቆራርጦ በአንድ ጃፓናዊ አማካኝነት ሀገራችን ገብቶ ሕዝቡን ጭንቀት ውስጥ ከቶት ይገኛል። ለዚህ ደግሞ በማህበራዊ ድረ ገፆች የሚለቀቀው የሀሰተኛ መረጃ ከፍተኛውን ተፅዕኖ ይዟል። ለኮሮና ቫይረስ ዶክተር ያልሆነ የፌስቡክ አርበኛ የለም። አንዳንዶቹ ፌጦ፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ሎሚና ማር ቀላቅሎ መውሰድ ፍቱን መድኃኒት ነው ይላሉ። ውሸቱ እውነት የመሰለው ማህበረሰብም ለመግዛት ሲጣደፍ ነጋዴው በተራው ለመሸጥ ሳይሆን ለዘረፋ የተዘጋጀ ይመስል ዋጋቸውን እንዳይቀመሱ ያደረጉት ተግባር ከሆድ አደርነት የከፋ ይመስላል።
ነጋዴዎች አንድ ሎሚ 15 ብር ማለት ጀመሩ፣ ማህበረሰቡም ጤና በ15 ብር ስለይማገኝ ምን ምርጫ አለን በማለት ለመግዛት ሲሽቀዳደሙ ተስተውለዋል። በዚህ ወቅት ታዲያ መንግሥት የወሰደው እርምጃ ይበል የሚያሰኝ ነው። ማህበረሰቡ አንዱ የመንግሥት አካል መሆኑን ዘንግቶ በዓይኑ የሚያየውን ሕገ-ወጥነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንደር ወረደው ዳኝነት እንዲሰጧቸው የሚፈልጉ አልጠፉም።
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2012