አዲስ አበባ:- በደብረበርሃን ከተማ ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ ታዳጊ መካከለኛ ሽግግር ያደረጉና ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ላስመዘገቡ የግል ኢንተርፕራይዞች መንግስት ለማምረቻ የሚሆን ቦታ እንደሚሰጥ ተገለፀ።
በደብረብርሃን ከተማ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃን ገብረሕይወት፤ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በከተማዋ እያደገ የመጣውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ተከትሎ መንግስት በተለይም ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ ታዳጊ መካከለኛ ሽግግር ላደረጉና ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ላስመዘገቡ የግል ኢንተርፕራይዞች የማምረቻ ቦታ እንደሚሰጥ ገልፀዋል።
የግል ባለሀብቱ የኢንዱስትሪው ዋና ሞተር እንዲሆን መደገፍና ማገዝ አስፈላጊ ነው የሚሉት አቶ ብርሃን፤ በተለይም የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ማበረታታት የከተማ አስተዳደሩ አንዱና ዋናው ስራ ነው።
በመሆኑም በደብረብርሃን ከተማ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪው መቀላቀል እንዲችሉ መድረክ በመፍጠር ሲያወያይ የቆየ መሆኑን አስታውሰው፤ በዚህም ባለፉት ዓመታት በአካባቢው የሚገኙ 30 የግል ኢንተርፕራይዞችን በመደገፍ እና ቅድሚያ በመስጠት ወደ ኢንዱስትሪው መቀላቀል እንዲችሉ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ከተማ አስተዳደሩ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን በልዩ ሁኔታ በመደገፍ፤ ባለሀብቶቹ ከቻሉ በግላቸው ካልቻሉም በጋራ “ፒኤልሲ” በመክፈት ወደ ኢንዱስትሪው እንዲገቡ የማበረታታት ስራ እየሰራ ይገኛል።
ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ ያስመዘገቡ የግል ኢንተርፕራይዞች ላቀረቧቸው የመሬት ጥያቄ መልስ አልተሰጠም ያሉት አቶ ብርሃን፤ ችግሩ መንግስት የአርሶ አደሩን መሬት ካሳ ከፍሎ ማስነሳት ባለመቻሉ ነው ብለዋል።
መንግስት ካሳ ከፍሎ የአርሶ አደሩን መሬት ከሶስተኛ ወገን ነፃ ማድረግ ሲችል፤ በልዩ ሁኔታ በከተማዋ ለሚገኙና ከፍተኛ ገቢ ላስመዘገቡ የግል ኢንተርፕራይዞች መሬት ያቀርባል። በተጨማሪም ከልማት ባንክ ብድር የሚያገኙበት መንገድ ይመቻቻል ብለዋል፡፡
በደብረብርሃን ከተማ በየጊዜው እየተስፋፋ ለመጣው የኢንቨስትመንት ፍሰት ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ህብረተሰቡ መሆኑን የገለፁት አቶ ብርሃን፤ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ከሚገኙት አጠቃላይ ባለሀብቶች 80 በመቶ የሚሆኑት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች መሆናቸውን በመግለፅ ይህም ከተማ አስተዳደሩ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በሚያደርገው ድጋፍ የመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2012
ፍሬህይወት አወቀ