የሰው ልጅ በዓለም ላይ ካሉ ፍጡራን በማሰብና በመመራመር የተለየ ፍጡር ነው። የሰው ልጅ በዓለም ላይ ያሉ ፍጡራንን በላይነት ያስተዳድራል። ከስድስት ሺ በሚበልጡ ቋንቋዎች በመነጋገር የሚግባባው የሰው ልጅ ዓለም ዛሬ ለደረሰችበት ዕድገትና ዘመናዊነት በብቸኝነት አስተዋፅኦ አድርጓል። የቴክኖሎጂ ጠንሳሽና ፈጣሪ በመሆን ዓለም ዛሬ ላለችበትና ወደፊት ለምትደርስበት ደረጃ ብቸኛ ፍጡር ነው።
በሀገራችን የሰው ልጅ ቦታ በበቂ ሁኔታ ዋጋ አይሰጠውም። ሀብት፣ ዝናና ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ከፍ ያለ ቦታ ሲሰጣቸው ይታያል። የሰው ልጅ ከመሆን በላይ ሰው ላይ ያለውን ካባ ትኩረት ይሰጠዋል። የሰው ልጅ ባለው 32 የሰውነት አካላት የሰው ልጅ ያስብለዋል። በዚህም ሰው እንደ ሰው ባለው ተፈጥሮ ብቻ ሰው ተገቢውን ክብር ሊያገኝ እንጂ ሰው ላይ ያለው ካባ ልዩ ቦታ ሊሰጠው አይገባም።
በአንድ ወቅት አንድ በአርባ ምንጭ ከተማ ያጋጠመኝን ገጠመኝ ላጫውጣችሁ። አንዲት የ13 ዓመት ሕፃን የማህፀን በር ካንሰር ታማ ወደ አርባ ምንጭ ሆስፒታል መጥታ ነበር። ካንሰሩም በሰውነቷ ተሰራጭቶ ስለነበር ብዙም ሳትቆይ ለሞት ተዳረገች። ይህቺ ሕፃን የማህፀን በር ካንሰር የተያዘችበት ምክንያት ከአስራ ሁለት ዓመቷ ጀምሮ በተደጋጋሚ ከተለያዩ ወንዶች ጋር ጥንቃቄ ያልተሞላበት ወሲባዊ ግንኙነት ስትፈፅም ስለነበር ነው። የማህፀን በር ካንሰር ‹‹HPV›› የሚባል የቫይረስ ዝርያ የሚያመጣው የአባላዘር የማህፀን በር ኢንፌክሽንን ተከትሎ የሚመጣ የካንሰር ዓይነት ነው። በጊዜው የነበረው ገዢው መንግሥት ከሰው ልማት ይልቅ ሕንፃ ግንባታ ላይ ትኩረት በማድረጉ ለሰው የሚሰጠውን ክብር በእጅጉ በማነሱ ነበር ይህ የተከሰተው።
በሁለተኛ አጋጣሚ አንድ ባለሀብት በኩላሊት ጠጠር በሽታ ይታመምና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለሕክምና ይገባል። ይህ ሀብታም ሊታከም ሳይሆን ሊቀለብ ሆስፒታል የገባ ይመስል የሚያውቁትም ሆኑ የማያውቁት ሰዎች ሳይቀር የሚበላ ምግብና የሚጠጣ ፈሳሽ ያግዙ ነበር። ሾርባ፣ ጁስ፣ ሙቅና የተለያየ የምግብ ዓይነቶች ለአንድ ሰው ሳይሆን ለአንድ ሺ ሰዎች በሚመስል መልኩ ይመጣለት ነበር። ባለሀብቱ ከሆስፒታል ተሽሎት እስኪወጣ ድረስ ጠያቂው ቁጥር ስፍር አልነበረውም። የሆስፒታሉ ሐኪሞች ግራ እስኪጋቡ ድረስ ነበር። ይህ ሰውዬ ሰው የተዋደቀለት ሰው በመሆኑ ሳይሆን ባለው ሀብት ብቻ ነበር።
በሦስተኛ አጋጣሚ በ2007 ዓ.ም አንድ ምስኪን የጂንካ ከተማ ነዋሪ ሚስቱ ሞተችበት። ይህ ሰውዬ ነባር ነዋሪ በመሆኑ በብዙ ሰዎች ይታወቅ ነበር። ከብዙ ሰዎች ጋርም ማህበራዊ ኑሮ መስርቷል። እንግዲህ ሰው ሲሞትበት ነባር ነዋሪ በመሆኑ በሚስቱ የቀብር ሥነ- ሥርዓት ወቅት ብዙ ሰዎች ይጠበቁ ነበር። ግን አልሆነም ነበር። ከዚህ ቀደም ይህ ሰው የሌሎች ሰዎችን ኀዘን ሲጋራ እንደነበር የእሱንም የሚጋሩ ሰዎች በብዛት ይጠበቁ ነበር። የሚገርመው ወደ 20 ገደማ ብቻ የሚጠጉ ሰዎች ከመኖሪያ ቤቱ ወደ ቀብር ቦታ ኀዘን ተጋሪ ሆነው ተገኙ። ሰውየውም ትናንት የደረሰላቸው ሰዎች ዛሬ ላይ በእርሱ ጊዜ ባለመኖራቸው እያዘነ ኀዘን ላይ ኀዘን ሆኖበት ነበር። በእርግጥ ማህበራዊ ሕይወት ብድር ለመመላለስ መሆን የለበትም። መልካም ሥራ ሁሉ ለህሊና መሆን አለበት። ቢሆንም ማህበራዊነት አንዱ ሰው ለአንዱ ሲሆን ነው። መረዳዳትና ኀዘን መጋራት በማህበራዊነት ውስጥ ከሌሉ ማህበራዊ ኑሮ አለ ለማለት ያስቸግራል። ለዚህ ሁሉ ኀዘን ተጋሪ ለማጣቱ ምስጢር ምስኪን ድሃ በመሆኑ ነው። ድህነቱ የሰው ልጅነት ያሳጣው በሚመስል መልኩ ነበር የሆነበት።
በአራተኛ አጋጣሚ በአዲስ አበባ አስፋልት ዳር ካሉ ትላልቅ ሕንፃዎች በረንዳዎች የመኖሪያ ቤት የሌላቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች ለማደር ሲሞክሩ ሲባረሩ አይቼ ነበር። የሚገርመው ነገር የሚፈልጉት ማደሪያ ስላጡ ማደር ብቻ እንጂ ሕንፃውን ተሸክመው አይወስዱትም ነበር። ያለመኝታ አልባሳት በብርድ መተኛት ነበር ፍላጎታቸው። ነገር ግን የሕንፃዎች ጠባቂዎች እየደበደቡ አባረሯቸው። እንደ እነዚህ መኖሪያ ቤት አልባ ዜጎች ሲቸግራቸው ሌሊቱን ሙሉ እየዞሩ ያነጋሉ። አንዳንዴ በመንገድ ዳርቻ ላይ ይተኛሉ። የሰው ልጅነታቸው ከቁጥር ሳይገባ መቅረቱ ተገቢ አልነበረም።
በአምስተኛ አጋጣሚ በአዲስ አበባ በልማት ሰበብ ሕንፃ መገንባት የማይችሉ ተብለው መሐል ከተማ የመኖሪያ ቤት ያላቸው ነዋሪዎች እንዲወገዱ ይደረጋል። በእርግጥ የካሳ ክፍያና ተተኪ ቦታ ይሰጣቸዋል። እንደሚታወቀው ቦታቸው ተወስዶ ለባለሀብቶች ይሰጥና ከተማን የሚያስውቡ ሕንፃዎች ይገነቡ ይሆናል። ነገር ግን በልማት ሰበብ ያለአግባብ ለነዋሪዎች በቂ ጊዜና ካሳ ሳይሰጣቸው በዶዘር መኪና ከነሀብት ንብረታቸው ቤቶቻቸውን መደምሰስ ግን እጅግ ፀያፊ ተግባር ነው። ልማት የሚሰራው ለሰው ልጅ ቢሆንም የሚያምሩ ሕንፃዎችና ፋብሪካዎች ከሰው አይበልጡም። ቁሳዊ ነገሮችም ሁሉ ከሰው አይበልጡም። ሰው ሰው ነው። የሚወዳደረውም ነገር ፈፅሞ የለም። ልማት መሰራት ካለበት ልማቱ ይጠቅመዋል የተባለው ሰው ሲስማማበትና ሲያምንበት መሆን ይኖርበት ነበር።
በስድስተኛ አጋጣሚ በአዲስ አበባ ከተማ ስሙን ለመጥራት የማልደፍረው አንድ ትልቅ ሆቴል አካባቢ የተፈጠረ አንድ አጋጣሚ አምስት የሚሆኑ ችግርተኞች በዚህ ትልቅ ሆቴል በር አካባቢ ረሃብ ስላንቆራጠጣቸው ትርፍራፊ ምግብ ፍለጋ ተሰብስበው ነበር። የሆቴሉ አስተዳዳሪዎች ችግርተኞቹ ከሆቴሉ አካባቢ መሰብሰባቸውን ስለተፀየፉ መናጢ ድሃዎች እያሉ ያቧርሯቸው ነበር። የሚገርመው ሰው መሆናቸውን ሳይታሰብ ድህነት የሰው ልጅነት የሚያሳጣ ተደርጎ ነበር የታየው።
እንግዲህ ከላይ ያሉ ስድስት እጋጣሚዎች እኛ ኢትዮጵያውያን ለሰው ልጅ ሳይሆን እሰው ልጅ ላይ ያለውን ካባ የምናስበልጥ መሆናችንን አሳይተውኛል። መነፅር ከዓይን አይበልጥም እንደሚባል ካባም ከሰው ልጅ አይበልጥም። ሀብት፣ ሥልጣንና ዝና ከሰው ልጅ ላይ የሚቀመጡ ካባዎች እንጂ የሰው ልጅ የሰውነት አካላት አይደሉም። የሰው ልጅነት ማዕረግንም አያሰጡም። ሰው መሆን ብቻውን ለሰው ልጅ በቂ ነው። ሰውን እንደ ሰው ማየትም ያለብን ሰው ስለሆነ ብቻ መሆን አለበት። ይህም ሰው ሁሉ ሰው ስለሆነ ነው። በአጠቃላይ የሰው ልጅ በፈጠረው አምላክ አምሳያነት የተፈጠረ ብቸኛ ፍጡር በመሆኑ ከእንስሳት፣ ከዕፅዋትና ከግዑዛን የማይስተካከል ክብርና ዋጋ ሊሰጠው ይገባል እላለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2012
በላይ ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ