አዲስ አበባ:- የዓለም ስጋት የሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ በቦሌ ለሚ ጨርቃጨርቅ እና ጋርመንትኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኙ የተለያዩ አምራች ኩባንያዎች ያላቸው የስራ እንቅስቃሴ መቀዛቀዙ ተገለጸ።
የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ስራ አስኪያጅ አቶ ትንሳኤ ይማም፤ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የዓለም ስጋት መሆኑን ተከትሎ የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን በማድረግ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።
ይሁን እና ቫይረሱ በኢትዮጵያ በመከሰቱ በኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚገኙ የግል ባለሀብቶች ፍራቻ ያደረባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የግል ባለሀብቶቹ ባደረባቸው ስጋትም በምርት እንቅስቃሴው ላይ ከፍተኛ መቀዛቀዝ እየታየ ነው የሚሉት አቶ ትንሳኤ፤ አብዛኞቹ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን የሚልኩት ወደ አውሮፓና አሜሪካ በመሆኑና እነዚህ አገራት ደግሞ የዓለም ስጋት በሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መዘጋታቸውን ተከትሎ ምርቶቹን መላክ አልተቻለም። በዚህም መቀዛቀዝ ይታይበታል ብለዋል፡፡
ኩባንያዎች የሚያመርቷቸው ምርቶች ወደ ገበያው እየደረሱ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ገዥዎች ከዚህ ቀደም ያዘዙትን ትዕዛዝ እየሰረዙ መሆናቸውን ባለሀብቶቹ ገልፀዋል የሚሉት አቶ ትንሳኤ፤ ባለሀብቶቹ በቀጣይ ስላለው ሁኔታ የሚያውቁት ነገር ባለመኖሩ ለጊዜው የተቀበሉትን ትዕዛዝ ብቻ አምርተው እያስቀመጡ መሆኑን ተናግረው፤ በዚህ ምክንያትም ባለሀብቱ ላይ ፍራቻ መንገሱንና እንቅስቃሴው መቀዛቀዙን ገልፀዋል።
በዓለም ላይ የጤና፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ቀውስ እያስከተለ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢንዱስትሪው እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ የሆነ መቀዛቀዝ እየፈጠረ ሲሆን፤ የችግሩ አሳሳቢነት ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ አይታወቅ እንጂ ኩባንያዎቹ የተቀበሉትን ትዕዛዝ አምርተው ከጨረሱ ማምረት እንደሚያቆሙ ተናግረዋል።
ኩባንያዎች መዝጋት ስለፈለጉ ብቻ መዝጋት እንደማይችሉ የገለፁት አቶ ትንሳኤ፤ በአሁኑ ወቅት ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ መላክ ያቆሙ ባለሀብቶች የመንግስትን ውሳኔ እየጠበቁ ሲሆን፤ ምርቶቻቸውን ወደ ኤዠያ የሚልኩ አንዳንድ ባለሀብቶች ደግሞ በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ ይገኛሉ።
ይሁን እንጂ፤ ችግሩ እየሰፋ ከመጣና መንግስት ፋብሪካዎቹን ለመዝጋት ውሳኔ ላይ የሚደርስ ከሆነ፤ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ስለሚኖርብን አስቀድሞ ሊያሳውቀን ይገባል የሚል ጥያቄ እየጠየቁ መሆኑንም አስታውሰዋል።
በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ 20 ሼዶች ያሏቸው 11 የተለያዩ ኩባንያዎች በጨርቃጨርቅና ጋርመንት ስራ ተሰማርተው ለ18 ሺ 700 ወጣቶች የስራ ዕድል የከፈቱ ሲሆን፤ ከነዚህ መካከልም 95 በመቶዎቹ ሴቶች መሆናቸው ይታወቃል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2012
ፍሬህይወት አወቀ