ኢትዮጵያ በግልጽ የተቀመጠ የቋንቋ ፖሊሲ ሳይኖራት ለበርካታ ዘመናት ኖራለች። ይህም በቋንቋዎች ዕድገት ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩን ምሁራን ይገልጻሉ። ይህም ብቻ ሳይሆን የቋንቋ እኩልነት አልተከበረም በሚል ጉዳዩ የፖለቲካ አጀንዳ እስከመሆን ደርሷል።
በአሁኑ ወቅት አገሪቱ የምትከተለውን የፌዴራል ስርዓት እውነተኛ በማድረግ በተያዘው አቅጣጫ መሰረት አማርኛን ጨምሮ ኦሮምኛ፣ ሶማሊኛ፣ ትግርኛና አፋርኛ የፌዴራል መንግስቱ የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ የሚደነግግ የቋንቋ ፖሊሲ ፀድቋል። ምሁራንና የስራ ሃላፊዎች ጅምሩ ለእውነተኛ ፌዴራሊዝም እና ቀጠናዊ ትስስሩ ጉልበት ነው ሲሉ ይናገራሉ።
ዶክተር ሃይለእየሱስ ታየ የፌዴራሊዝም ጥናት ምሁር ናቸው። እንደ እርሳቸው አባባል ሀገራችን የብዙ ብሄረሰቦች፣ ቋንቋዎችና ባህሎች ባለቤት ናት። በስፋት የሚነገሩ ቋንቋዎችን ለስራ ማዋል ዜጎች በቀላሉ የመንግስትን አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።
ቋንቋው የተከበረለት ዜጋ ‹‹እኔ የዚች ሀገር አካል ነኝ›› የሚል የስነ ልቦና ብርታት እንዲያገኝም ይረዳዋል። ይህ የበርካታ ሀገራት ተሞክሮ ነውም ብለዋል።
‹‹የፌዴራል ሥርዓትን በምትከተልና ልሳነ ብዙ በሆነች ሀገር ኢትዮጵያ አንድን ቋንቋ ብቻ የፌዴራል መንግስት የሥራ ቋንቋ አድርጋ መጠቀም የቋንቋ ፖሊሲና መብትን ከግምት ያላስገባ በገሀድ የሚታይ ማህበራዊ ችግር ነበር።
የፌዴራል መንግስት አንድን ቋንቋ ብቻ መጠቀሙ በሌሎች ቋንቋዎች ዕድገትና ተሳትፎ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል፤ ማህበራዊ ግልጋሎታቸውንም ገድቦታል ሲሉ የአቶ ሚልኬሳ ሚደጋ ሃሳብን በኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም የልሳነ ብዝሃነት ፖለቲካዊ እይታና የቋንቋ ፖሊሲ ጥናት ፤ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ጥናት መጽሄት ሁለተኛ እትም ገጽ 87 2008 ዓ.ም ላይ እናገኘዋለን።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው እንደሚያስረዱት ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ማድረግ ካስፈለገ ሁሉንም ቋንቋዎች ማልማት ያስፈልጋል። ብሄር ብሄረሰቦች ከሌሉ ኢትዮጵያን ልናገኝ አንችልም።
ስለዚህ ኢትዮጵያን ለመገንባት የብሄር ብሄረሰቦችን ቋንቋና ባህል ማሳደግ ግድ ይላል። ይህም ለእውነተኛ ፌዴራሊዝም ትግበራ ወሳኝ ነው ይላሉ። የአንድ ማህበረሰብ ማንነት የሚገለጸው በቋንቋው ነው።
በዋናነት የብሄረሰቡ ህልውና የሚረጋገጠውም ቋንቋው አብሮት ሲኖር ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያን ህዝቦች ማንነት ለማስቀጠል ቋንቋቸውን ማልማት ያስፈልጋል።
ይህን ክፍተት ለመሙላትም አሁን ኦሮምኛ፣ ሶማሊኛ፣ ትግርኛና አፋርኛ የአማርኛ ቋንቋን ጨምሮ በፌዴራል ደረጃ የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ የጸደቀው የቋንቋ ፖለሲ አስፈላጊና ወቅታዊ ነው ብለዋል።
እንደ አቶ ሚልኬሳ አገላለጽ ስራ ላይ የነበረው የቋንቋ ፖሊሲ ከአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ውጭ ያሉ የሀገሪቱ ዜጎችን ከግምት ያስገባና የመንግስትን አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል አልነበረም።
የፌዴራል መንግስቱ የስራ ቋንቋ አንድ ብቻ መሆኑ በፌዴራል የመንግስት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ሰራተኞች ሥራቸውን አቀላጥፈው የመስራት ችግር እንደነበረባቸውና ተገልጋዮችም የሚፈልጉትን አገልግሎት ማግኘት አለመቻላቸውን አመላክቷል።
ዛሬ ኢትዮጵያ ከምትከተለው የፌዴራሊዝም ሥርዓት አንጻር የቋንቋ ፖሊሲዋን እንድትፈትሽ የሚያስገድዷት ሁኔታዎች መፈጠራቸውን አቶ ሚልኬሳ በጥናቱ አመላክቷል።
ዶክተር ሂሩት እንደሚስረዱት እስከ አሁን የቋንቋ ፖሊሲ አለመኖሩ ቋንቋዎቻችንን በሚፈለገው ደረጃ አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል አላስቻለም።
በቀደሙት ሥርዓቶች በተለይም በአጼ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት አማርኛ ቋንቋ ብቻ የስራ ቋንቋ ተደርጎ እንደተወሰነ አስታውሰው በወቅቱ የአማርኛ ቋንቋና ስነጽሁፍን ለመደበኛ ቋንቋነት ለማሳደግ የሚያስችል የቋንቋ አካዳሚ መቋቋሙንም ጠቅሰዋል።
በደርግ ዘመነ መንግስትም አካዳሚው አድጎ ወደ አስራ አምስት ቋንቋዎችን በመያዝ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዳሚ በሚል ሲያጠና እንደነበር አስታውሰዋል። ይህ የቋንቋ አካዳሚ በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት በተለይም በህገ መንግስቱ ሁሉም ብሄር ብሄረሰብ በራሱ ቋንቋ የመማርና የመጠቀም መብቱ ሲረጋገጥ አካዳሚው የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ ወደሚል መቀየሩን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በሀገሪቱ የሚገኙ ቋንቋዎች በስፋት የመጠናት ዕድል አግኝተዋል። ብዙ ቋንቋዎችም የትምህርትና የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ አካዳሚው እገዛ አድርጓል።
እንደ ዶክተር ሃይለእየሱስ ቋንቋዎቹ የተመረጡት የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት እስከሆነ ድረስ አገልግሎታቸው በፌዴራል መንግስት ብቻ ሳይወሰን በክልል ደረጃም ቢወርድ የበለጠ ችግር ፈቺ እንደሚሆኑ ይገልጻሉ።
ይህም ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለማጠናከርና ልሳነ ብዙ ትውልድን ለማፍራት ያስችላል። ሀገሪቱም በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ጤናማ የፌደራል ሥርዓት እንድትገነባ ያግዛታል ብለዋል።
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋ ልማት ዳይሬክተር አቶ አውላቸው ሹምነካ በበኩላቸው እንደሚያስረዱት የቋንቋ ፖሊሲ ለአንድ ሀገር አድገት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በርካታ ቋንቋ ባላቸው ሀገራት ደግሞ ትርጉሙ ከዚያም በላይ ነው።
ለፌደራል መንግስት የሥራ ቋንቋነት የተመረጡት አምስቱ ቋንቋዎችም የጽሁፍ አገልግሎት የሚሰጥባቸው፣ የሚዲያ፣ የትምህርትና የስራ ቋንቋ የሆኑ እንዲሁም የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦችን የሚያገናኙና እንደ ሁለተኛ ቋንቋም ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው። በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያሉ ሀገራት የሚጋሯቸውና የሚተሳሰሩባቸውም እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2012
ኢያሱ መሰለ