አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት መንግስት ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መደረግ እንዳለባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳሰቡ።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ብሄራዊ የአደጋ ስጋት መከላከል እና ምላሽ ሰጪ ግብረ ሃይል ከጤና ቴክኒክ ኮሚቴ ጋር በቅንጅት የመንግስትን ውሳኔዎች ተፈፃሚ እንዲያደርጉ እና እንዲከታተሉ ብሄራዊ ስምሪት መስጫ መድረክ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ትናንት ሲካሄድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ እንደገለጹት፤ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት መንግስት ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል።
በየደረጃው የመንግሥት ተቋማት ፍፁም በሰመረ ቅንጅት ለውሳኔዎቹ ተፈፃሚነት በልዩ ትኩረት እና ክብደት መረባረብ እንደሚጠበቅባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተው ፤ “በታሪካችን እጅግ የከፋ ፈተና ውስጥ መሆናችንን በውል በመገንዘብ፤ አገር እና ህዝብን በፍጥነት ለመታደግ ዳር እስከዳር ስልታዊ ርብርብ የምናደርግበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንገኛለን” ብለዋል።
እንደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ብሄራዊ ርብርቡ በአጭር ጊዜ ትርጉም ያለው ውጤት ለማምጣት መንግሥት የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎች በተሟላ መንገድ ተፈፃሚነታቸውን ማረጋገጥ ይገባል። ብሄራዊ ግብረ ሃይሉ እና የቴክኒክ ኮሚቴው ለተሰጠው አገራዊ ተልዕኮ ውጤታማነት ዕለት በዕለት ጥብቅ የአመራር ድጋፍ እና ጠንካራ ክትትል ይደረጋል።
በአገሪቱ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እና ለመከላከል መንግሥት በፌዴራል ደረጃ የሚወስዳቸው እርምጃዎች በሁሉም ክልሎች እና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ወጥነት ባለው አግባብ ተግባራዊ መደረግ እንዳለባቸው ገልጸው፤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን አስመልክቶ መንግሥት ለሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ተፈፃሚነት እና ለሚወስዳቸው እርምጃዎች ተግባራዊነት የተሟላ ውጤት ለማረጋገጥ ጥብቅ አመራር ይጠይቃል ብለዋል።
እንደ አገር ከዚህ ቀደም ላጋጠሙ አስቸጋሪ የተፈጥሮ አደጋዎች በመንግሥት የተሰጡት ስኬታማ ምላሾችን እንደነበሩ አውስተው፤ እነዚህን በሳል ልምዶች እና ውጤታማ ተሞክሮዎች በብሄራዊ ስምሪቱ ውስጥ ተግባራዊ እንደሚደረጉ ጠቁመዋል።
የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እና ለመከላከል እያንዳንዱ ዜጋ የመፍትሔው አካል በመሆን ሰብዓዊ እና አገራዊ ግዴታውን በተግባር እንዲወጣም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ ህብረተሰቡ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡት የጥንቃቄ መርሆዎችን በመከተል ራሱን ከበሽታው አስቀድሞ እንዲከላከል አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2012
ጌትነት ምህረቴ