አዲስ አበባ፡- በተለምዶ ቆሼ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ለሚገኙ የጤና ተቋማት ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ የወረዳ አንድ ጤና ጣቢያ አስታወቀ፡፡
በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ጤና ጣቢያ ሜዲካል ዳይሬክተር የጤና መኮንን ኤርሚያስ ተሾመ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የኮሮና ቫይረስ መከላከያን ከመስጠት አንፃር ቆሼ አካባቢ ለሚገኙ የጤና ተቋማት ልዩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡
እንደ ጤና መኮንኑ ገለጻ፤ ጤና ጣቢያው በሽታውን ለመከላከል የተለያዩ እርምጃዎችን ቢወስድም አሁንም በጤና ጣቢያው ኤን 95 የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) እንዲሁም የእጅ ንፅህና መጠበቂያ እጥረት አለ፡፡ መንግስትም ለአካባቢው የተለየ ትኩረት በመስጠት ሊሰራ ይገባል፡፡
የጤና መኮንኑ ቦታው ታጥሮ ባለመከለሉ ምክንያት አሁንም በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች እንዳሉ በመናገር መንግስትም እንደ አማራጭ ወይ ጤና ጣቢያውን ቦታውን መቀየር አልያም በቦታው ቆሻሻ እንዳይደፋ ማስደረግ ቢችል አካባቢው ያለውን የበሽታ ተጋላጭነት መቀነስ ይቻላልም ብለዋል፡፡
መንግስት በተለየ መልኩ ለአካባቢው እየሰጠ ያለው ድጋፍ አለመኖሩን የተናገሩት የጤና መኮንኑ፤ በአካባቢው ማን እንደሚለኩሰው የማይታወቅ ጭስ መኖሩን እና ከቆሼ የሚመጣው ሽታም የአካባቢውን ማህበረሰብ ለበሽታ ተጋላጭ በማድረግ ላይ ስለሆነ መንግስት ለአካባቢው የተለየ ትኩረት በመስጠት የአጭርም ሆነ የረጅም ጊዜም እቅዱ ውስጥ በማካተት መስራት አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ጤና ጣቢያው በሽታውን ለመከላከል ራሱን የቻለ ለይቶ ማቆያ ቦታ እንዳዘጋጀና የጤና ኤክስቴንሽኖች ቤት ለቤት ትምህርት እየሰጡ መሆናቸውን የተናገሩት የጤና መኮንኑ፤ ታካሚዎች ወደ ጤና ጣቢያ በሚመጡበት ወቅትም በመለየት ችግር ከገጠመ በሁለት ሰአት ውስጥ ለህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት እንዲሁም ጤና ቢሮ መረጃ እናደርሳለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ጤና ጣቢያ የበሽታ መከላከል ንኡስ የስራ ሂደት የሆኑት የጤና መኮንን ሰለሞን ታሪኩ በበኩላቸው፤ መንግስት የያዘውን መንገድ መቀጠል አለበት ብለው ለቫይረሱ መከላከያ የሚሆኑ ግብአቶችን በተቻለ ፍጥነት ማዳረስ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
መንግስት ለአካባቢው ቅድሚያ እንዲሰጥ ያሳሰቡት ጤና መኮንኑ መንግስት በራሱ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንዳለና ብቻውን ምንም ማድረግ እንደማይችል ተናግረው፤ መንግስት የሚያወርዳቸውን አቅጣጫዎችም ህብረተሰቡ እየተቀበለ ካላስፈፀመ በቀር መፍትሄ ማግኘት እንደማይቻልም አመላክተዋል፡፡
ጤና ጣቢያው ስለ ኮሮና ቫይረስ ምንነትና መከላከያ መንገዶች ለህብረተሰቡ በተቻለው መንገድ እያስተማረ መሆኑን ጠቅሰው፤ በመከላከል አቅማቸውና ፊትን በተሻለ መልኩ መሸፈን የሚችለው ኤን 95 የፊት መሸፈኛ ወይም ማስክ እጥረት በመኖሩ ምክንያት አልኮልና ሌሎች ነገሮችን በመጠቀም ላይ ያሉ ሲሆን፤ በብዛትም የእጅ መታጠብ ሥርዓትን እየተከተሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቆሼ ከ3 ዓመት በፊት ተደርምሶ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ከ100 በላይ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2012
ዳግማዊት ግርማ