አዲስ አበባ፡- የምጣኔ ሀብት ምሁራንን ከአገሪቱ ኢኮኖሚ ጋር በማስተሳሰር ረገድ ተጨማሪ ተግባራትን ማከናወን እንደሚጠይቅ ተገለጸ፡፡
የምጣኔ ሀብት ምሁራን በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያላቸው ተሳትፎና አስተዋፆኦን በሚመለከት አዲስ ዘመን ያነገራቸው የኢንሼቲቭ አፍሪካ ዋና ስራ አስፈጻሚና ኢኮኖሚስት አቶ ክቡር ገና እንደገለፁት፣ የምጣኔ ሀብት ምሁራን የአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያጎለብቱ ለህዝብ ሁለንተናዊ ትሩፋት የሚቸሩ የተሻሉ ሃሳቦችን በማፍለቅ ረገድ በቂ አቅም ፈጥረዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡
አገሪቱ የኢኮኖሚ ብልፅግናን እንድትቋደስ የሚያግዙ ምርምሮች ብሎም ኢኮኖሚው የሚመራበትን አቅጣጫ ለማመላከት የሚያግዙ የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች በማቅረብ በተሳትፎ ረገድም ከጥንካሬአቸው ይልቅ ድክመታቸው ጎልቶ ይታያል፡፡
‹‹በኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ምሁራን የት እንዳሉ እራሱ በቅጡ ማወቅ ይችግራል፣ ሁሉም በራሱን የግል ስራ አስተማሪው በማስተማር ፣ አማካሪው በማማከር ላይ ተጠምዷል›› የሚሉት አቶ ክቡር፣ ይህን ለዓመታት የቆየ ችግር ለማስወገድም በአሁኑ ወቅት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችና የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማስተሳሰር በቂ ትኩረት መስጠት ለዚህም የተለያዩ ተግባራትን መከወን ግድ እንደሚል አስገንዝበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ደኑ በበኩላቸው፣ በአሁኑ ወቅት ባካበቱት እውቀትና የስራ ልምድ በመጠቀም የአገሪቱን ኢኮኖሚ በእውቀት እንዲመራ የሚጥሩ የምጣኔ ሀብት ምሁራንና ተቋማት መኖራቸውን አስገንዝበዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚስቶች ማህበርም ከተቋማቱ መካከል ዋነኛው ነው›› ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ማህበሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተፈጠረው እድል በመጠቀም በተለያዩ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት በርካታ ምሁራንን ያሳተፈ የተለያዩ የእድገት አቅጣጫዎችን የሚያመለክቱ ጥናቶችና ውይይቶች እያካሄደ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡
ይሁንና በአገሪቱ ኢኮኖሚን በሚመለከቱ ተቋማት ውስጥ በአማካሪነትም ሆነ በአመራር ደረጃ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ተሳትፎና አበርክቶ ብዙ የሚቀረውና ችግሩም ዓመታትን የተሻገረ መሆኑን የሚጠቁሙት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ በአገሪቱ የምጣኔ ሀብት ምሁራንን ከኢኮኖሚውና ከጠቅላላው የመንግስት ስራ ጋር የማቀናጀቱ ተግባር ብሎም ለባለሙያዎቹ የሚሰጠው ድርሻና ትኩረት ብዙ እንደሚቀረው ተናግረዋል፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት በሰው ሃይል ቅጥር ረገድ የሚወጡ መስፈርቶችና ጥያቄዎች ሳይቀር ከሙያው ጋር ምንም ዝምድና የሌላቸው ሆነው ሲቀርቡ መታዘባቸውን የጠቆሙት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ይህን አይነት አካሄድ የማያዋጣና የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣትም እንቅፋት መሆኑን በመገንዘብ መታረም እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል፡፡
ይህ ግን ሙሉ በሙሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ከኢኮኖሚው ጋር አልተቀራረቡም ማለት እንዳልሆነ አፅእኖት የሚሰጡት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ይሁንና በአንዳንድ ወቅቶች የኢኮኖሚ እውቀትና ልምድ የሚጠይቁ ስራዎች ላይ ሳይቀር ሌሎች ግለሰቦች ሲሳተፉና ሲመደቡ እንዳስተዋሉ አመልክተዋል፡፡
ይህ የሚሆነው በመንግስት ድክመት ነው ወይንስ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቻች ተሳትፎና አበርክቶ ውስንነት? በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄም፣ ችግሩ የአንድ ወገን ብቻ አለመሆኑንና በሁለቱም በኩል ውስንንነቶች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት ባለሙያዎችን ተሳታፊ ለማድረግ ከእውቀታቸው ለመጠቀም በንግግር ደረጃ ፈቃድ ባይነፈገውም በተግባር ግን መሬት እንደማይወርድ ያስታወሱት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ‹‹በተለይ በአሁኑ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው መንግስት ማንኛውም በአገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሁሉ በለውጥ ሂደት በኢኮኖሚም ሆነ በሌሎች መስኮች ባለው እውቀትና አቅም የበኩሉን እንዲወጣ በሩን ክፍት ማድረጉ የሚደነቅ ነው›› ብለዋል፡፡
‹‹እኔን ጨምሮ ማንኛውም ኢኮኖሚስት አገሩ እንድትበለጽግና ከሌሎች አገራት ተርታ እንድትሰለፍ ከፍተኛ መሻት አለን፣ የበኩላችንን ለማበርከትም ዳተኛ አይደለንም›› ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፣ የባለሙያዎችን ተሳትፎና አበርክቶ ለመጨመር ሲታሰብም ምቾት የማይሰጡና ቢሮክራቲክ የሆኑ አሰራሮችን ማስወገድ ብሎም ለባለሙያዎቹ ነፃ ፈቃድንና ምቹ ከባቢን ማደላደል እንደሚያስፈልግም አስምረውበታል፡፡
ዝግጁ የሆኑትን ባለሙያዎች አስተባብሮ ከእውቀታቸው መጠቀም የመንግስት ሃላፊነት መሆኑን ጠቁመው፣ የተከፈቱ በሮች ሲመለከቱም ባለሙያዎች በግልም ሆነ በቡድን ከመንግስት ጋር የአገራቸውን እድገት ለማሳካት እንዲተጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2012
ታምራት ተስፋዬ