‹‹ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እጅግ ዘግናኝ የሆነ ችግር እያስከተለብን ነው።እኔ የተሰማራሁበት የሥራ ዘርፍ ከቀን ሰራተኛ እስከ ከፍተኛው ድረስ ያካተተ ነው።
በሽታው በቀን ሰርቶ የዕለት ጉርሱን የሚሸፍነውን ከሥራ ውጭ እያደረገው ነው። ለዚህ የህብረተሰብ ክፍል እንደ አደጉት ሀገራት ሌሎች አማራጮችን ማስቀመጥ አንችልም። የችግሩ ስፋት በዚህ ልክ ነው የሚገለጸው›› በማለት በሽታው ችላ ሊባል እንደማይገባው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ይገልጻል፡፡
አትሌት ኃይሌ፤ በሽታው አሳሳቢ ቢሆንም ጭራቅ አድርጎ መሳልም የተሳሳተ እንደሆነ ይናገራል። በሀኪሞች የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ እራስን በመጠበቅ ሌሎችንም መታደግ ይገባል ሲል ይመክራል።
አንድ ሰው ጉንፋን ሲይዘው ወደ ሌላ እንዳያስተላልፍ እንደሚጠነቀቀው ሁሉ ይህም ወረርሽኝ እስኪገታ መጠንቀቁ እንደሚበጅ ይናገራል። ምንም እንኳን ወረርሽኙ በየንክኪው ንጽህና መጠበቅን የሚያስገድድ ቢሆንም የግል ንጽህናን መጠበቅ በእጅ አማካኝነት ከሚተላለፉ በሽታዎች ይከላከላል ብሎ ያምናል።
በግሉም በሀኪም የተሰጡ የቅድመ ጥንቃቄ የእጅ ንጽህና መጠበቂያዎችን በመጠቀም ጥንቃቄውን ጨምሯል። መጨባበጥም አቁሟል። ‹‹ይተላለፍብኛል ብቻ ሳይሆን አስተላልፋለሁ ብሎ ማሰብም ይገባል›› ይላል፡፡
ኃይሌ ከእርሱም አልፎ የድርጅቱ ሰራተኞችና ደንበኞቹ ለበሽታው እንዳይጋለጡ ጥንቃቄው እስከነርሱ ዘልቋል። ስጋቱ ኢኮኖሚው ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ ህዝብን ለረሃብ አደጋ እንዳያጋልጥ መጠንቀቅ ላይም መዘናጋት መኖር የለበትም ብሏል፡፡
በዚህ አጋጣሚ የዋጋ ንረት ያስከተሉትንና አላስፈላጊ ሸመታ ያካሄዱትንም ኮንኗል። በዚህ ጊዜ የግል ጥቅም የሚታሰብበት እንዳልሆነ ይገልጻል። ኪሳራ ቢደርስም የግለሰብ ሳይሆን የሀገር መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ ያስረዳል።
ሁሉም እኩል የሚጨነቅበት ወቅት መሆኑን በመጠቆም፣ እርሱ ለግሉ ብቻ ሳይሆን በሥሩ ላሉ ሶስት ሺ ሶስት መቶ ሰራተኞቹ ጭምር እንደሚጨነቅ ነው የተናገረው። ጥንቃቄው ከቤት ጀምሮ ከተተገበረ ውጤት ይመጣል ብሎ ያምናል፡፡
ብዛት ያለው ሸማች ከሚያስተናግዱ ተቋማት መካከል የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት ይጠቀሳሉ። የህዝብ እንቅስቃሴን ለመቀነስ መንግሥት አብዛኛው ሰራተኛ በቤቱ እንዲቆይ ውሳኔ ቢያሳልፍም ማህበራቱ የዕለት ፍጆታ የሚያቀርቡ በመሆናቸው ሥራቸውን አላቋረጡም።
በሽታውን እንዴት እየተከላከሉ ነው የሚለውን ለመቃኘት በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ እፎይታ ሸማቾች ማህበር ተገኝተናል። በበሩ መግቢያ ባዘጋጁት የእጅ መታጠቢያ ሸማቹ ታጥቦ እንዲገባ የመጀመሪያ ጥንቃቄ አድርገዋል።
ወረፋ ሲጠብቁ ደግሞ ተጠጋግተው እንዳይቆሙ በተወሰነ ርቀት በእንጨት ችካል አድርገዋል።በተጨማሪም ወረፋውን የሚያስተናብሩት እያስጠነቀቁ መጠጋጋትን ለማስቀረት ጥረት ሲያደርጉ ታዝበናል።ግንዛቤው ገና ቢሆንም ጥንቃቄው ይበል የሚያስብል ነው፡፡
የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት መንግሥቱና የማህበሩ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዳንኤል ፀጋው በየበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ሸማቹ ዋጋ ባናሩ ነጋዴዎች እንዳይበዘበዝ የህዝብ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ሲሉ በሥራ ገበታቸው ላይ ተገኝተዋል።
ህዝቡንም ሲያገለግሉ የእራሳቸውንም የሸማቹንም ጤና እየጠበቁ መሆን እንዳለበት በመገንዘብ አስፈላጊውን የቅድመ ጥንቃቄ ተግባር በማከናወን ሥራቸውን በመፈጸም ላይ እንደሆኑ ይገልጻሉ።ይሁን እንጂ ወደ እነርሱ የሚሄደው ሸማች ጉትጎታ መፈለጉ አስቸጋሪ እንደሆነባቸው አልሸሸጉም፡፡
አቶ ጌትነት እንዳሉት ሥራቸው በፖሊስ ኃይል ቢታገዝ ሸማቹ ጥንቃቄውን በተሻለ ይተገብራል ብለው ያምናሉ። ሰራተኞቻቸው በየክፍላቸው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ በመስጠት ጥረት መደረጉንም አመልክተዋል፡፡
አቶ ጌትነትም የመከላከያ መንገዶችን በመተግበር እንጂ በመደናገጥና ቸልተኛ በመሆን በሽታውን መከላከል እንደማይቻል ተገንዝቦ የራስን ጥረት ማድረግ እንደሚገባ መክረዋል፡፡
ሸማቹን በእጅ ማስታጠብ እንዲያግዙ የወረዳ ዘጠኝ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤትም ትብብር ሲያደርግ አስተውለናል። የጽህፈት ቤቱ ባለሙያ የሆኑት አቶ አወቀ ተስፋ እንደገለጹልን፤ ወጣቱን በማስተባበር በአቅሙ የሚችለውን እንዲያደርግ በጽህፈት ቤታቸው በኩል ጥረት በመደረግ ላይ ነው፡፡
ወጣቱ በበጎ ተግባር ሙሉ ፈቃደኛ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ አወቀ፣ ሌሎችን ሲረዳ እራሱንም እየጠበቀ መሆን እንዳለበት መክረዋል። በግላቸውም እንደሚጠነቀቁ ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2012
ለምለም መንግሥቱ