የመዳፍ አንባቢዎች ሥራ ደርቷል:: እሁድ ጠዋት ከሩጫ ስመልስ አንድ ማስታወቂያ ተመለከትኩ:: «በተቀጣጠለው የእጅ መታጠብ አብዮት ምክንያት በአዲስ መልክ መዳፍ ማንበብ ጀምረናል» የሚል:: ወረድ ብሎ «በሳኒታይዘር ምክንያት ከዚህ ቀደም በማይስክሮኮፕ እንኳን የማይታዩ ጥቃቅንና አነስተኛ መስመሮች መታየት በመጀመራቸው የዋጋ ጭማሪ አድርገናል» ይላል::
ተጨንቄያለሁና ከኮሮና ቫይረስ የሚተርፍ የወደፊት ሕይወት እንዳለኝ ለማረጋገጥ ገባሁ:: መዳፍ አንባቢው አጎንብሶ መሬት ያነባል:: አጠገቡ መነጽር አለ:: ቀና ብሎ ሳያየኝ «በአይን ወይስ በመነጽር» ሲል ጠየቀኝ:: «ልዩነት አለው» ጠየኩ:: በመነጽር ከሆነ በቀሪ ዘመንህ የሚገጥምህን ክፉና ደግ ሁሉ እነግርሃለሁ አለኝ:: ከኮሮና ጋር በተያያዘ መምጣቴን ነግሬው ቀና ብሎ ሳያየኝ ያለመነጽር መዳፌን ማንበብ ጀመረ:: ከሃያ ደቂቃ በኋላ «እጅህን በየሃያ ደቂቃው መታጠብ ካቆምክ በኮሮና ምክንያት ሕይወትህ ይቆማል» አለኝ:: ከዚያም እንዳቀረቀረ «ኮሮና በአገር የመጣ ችግር ስለሆነ እንደአንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ራስ ወዳድ መሆን አልፈልግም:: የአይኔን ብቻ 400 ብር ክፈል» አለኝ:: ከፍዬው ወጣሁ::
መዳፍ አንባቢው እጄን በየሃያ ደቂቃው ከታጠብኩ ከኮሮና እንደምተርፍ ስለነገረኝ እረፍት ተሰማኝ:: በእርግጥ ጤና ሚኒስቴር ይህንኑ ሀሳብ ደጋግሞ ሲናገር ሰምቻለሁ ግን እንደ መዳፍ አንባቢው እረፍት አይሰጥም:: አሻጋሪዬ ኮሮናን የምሻገርበትን መንገድ ከጠቆመኝ በኋላ እኔም ሌሎችን ለማሻገር ተነሳሁ::
ማሻገር የምጀምረው ወንዝ ተሻግሮ ለመጣው ኮሮና አገራዊ ስም በመስጠት ነው:: አፍሪካን አፍሪቃ እንላለንና ኮሮናን ቆሮና ብዬዋለሁ:: በመዘናጋት ድንዛዜ ውስጥ ላለነው ለእኛ ምህጻረ ቃልም ነው:: ቆረና … ቆየህ ሮጠህ ና! ብለን ልንተረጉመው እንችላለን:: ከጥንትም በአገራችን ወረርሽኝ የሚመከተው ከግብሩ የሚጣጣም ስም እየተሰጠው ነው:: በ1907 ዓ.ም የተቀሰቀሰውን የትኩሳት በሽታ ለማከም የዣንጥላ መገተሪያ ብረት በእሳት ግሎ የበሽተኛው ገላ ሲተኮስ ይንጣጣ ነበርና የበሽታው ስም ጣጣቴ ተባለ::
“ኮ” ን በ “ቆ” መቀየሬ ካስቆጣችሁ ቆሮና የቃላትን ትርጉም መቀያየሩን ልብ አላላችሁም ማለት ነው:: ወገብ ችቦም አይሙላ ቱቦ፣ አንገት መቃም ሆነ ቀርከሃ፣ አፍንጫ ሰልካካም ይሁን ድፍጥጥ፣ አይነ ቆሎም ተሆነ አይነ ንፍሮ በዘመነ ቆሮና ቁንጅና ንህጽናንና ርቀትን መጠበቅ ሆኗል:: ቆሮና የሚያናፍጠውን ሰልካካ አፍንጫ ማን ዞር ብሎ ያየዋል?
አራዳነት ጣቶችን ፊት ላይ ላለማሮጥ፤ ጉንጭን ከጉንጭ ላለማጋጨት፤ ላለማቀፍ ላለመታቀፍ መጠንቀቅ ሆኗል:: የቆሮና ዘመን አራዳ ጅንን ነው:: ብትሰቅለው እጁን ለሰላምታ አይዘረጋም:: ቀድመው እጅ ቢዘረጉለትም አጸፋውን የማይመልስ ኩሩ ነው:: ጉንጭ ላይ አይለጠፍም፤ አንገት ስር አይወተፍም:: ቀን እስኪያልፍ ርቀቱን ይጠብቃል:: አራዲትም ቢሮ፣ መስክና ሱቅ ስትሰራ ውላ መሸታ ቤት ዝር ሳትል በጊዜ የምትገባ፤ በሳሙና አሊያም በሳኒታይዘር ታጥባ ልጇን የምታጠባ ፤ ርቀቷን ጠብቃ የምትግባባ ናት:: ቆሮና የያዘው ሰው እንደ ገነፈለ እስክሪብቶ በአይን አይለይማ!
ከደረቅ ወደብ ከጫነው ኮንቴይነር ጋር ደረቅ ሳል ጭኖ መጥቶ በጫነው ኮንቴይነር ውስጥ ኳራንቲን መደረግ የሚፈልግ ማንም የለም:: ስለዚህ ቆረና በራችንን ሲቆረቁር በቀላሉ ዘው እንዲል መፍቀድ የለብንም:: በእውቀቱ ስዩም በአንድ ግጥሙ
አንኳኳ ይከፈትልሃል፣
ስትገባ ሌላ በር ይጠብቅሃል፤
እንዳለው የቆሮናን መግቢያ በሮች ሁሉ ቆልፈን በቢሮክራሲው ደክሞና ተሰላችቶ እንዲመለስ ማድረግ አለብን:: ሞትና ሰርግ አንድም አይደል:: «አናስገባም ሰርገኛ እደጅ ይተኛ»ን እየዘፈንን በራችንን መዝጋት ነው:: ከተዘናጋን ግን ቆሮና እንደ ወንድ ሙሽራ ደርምሶን ገብቶ ይጨፍርብናል:: ከዚያማ ሥራችን «አሸኙንም ሆይ ልንሄድ አይደልም ወይ» እያሉ የሚዘፍኑትን ወደ ሆስፒታል መሸኘት ይሆናል:: ሆስፒታል ከገቡ በኋላ ህመሙ ጸንቶባቸው «ልንሄድ አይደለም ወይ» እንዳሉት ጨርሰው ከሄዱም «አስወስጄ መጣሁ አስወስጄ» እያልን ሙሾ ልናወርድ ነው:: ይህ ሁሉ እንዳይሆን መፍትሄው ንጽህናንና ርቀትን መጠበቅ ነው:: ቆሮና በር እስኪቆረቁር ድረስ አለማቀርቀር! ቀድሞ ታጥቆ መጠበቅ!
የሕዝባችንን ሁኔታ ስመለከት የእግር ኳስ ተጫዋቾች የሚመቱት የማዕዘን ምት (ኮርና) እና ኮረና ይመሳሰሉብኛል:: አንድ ተጫዋች ኮርና ሲመታ ሌሎቹ ጎል አካባቢ ተሰብስበው ኳሷን ይሻማሉ:: በመድኃኒት ቤቶች፣ በታክሲዎች ውስጥና በአንዳንድ ቦታዎች በርካቶች ተሰብስበው አንድ የቆሮና ቫይረስ ተጠቂ ሲያስነጥስ አሊያም ሲያስል የከበቡት ሰዎች ቫይረሱን ሻሞ ይላሉ:: የእግር ኳስ ጨዋታዎች ቢከለከሉም ኮርና ግን እንደቀጠለ ነው::
የተባልነውን ትተን ያልተባልነውን ሙጥኝ እያልን ነው:: ለእጁ ንጽህና ግድ የሌለው ለአራት ሰዓታት ብቻ በሚያገለግል የፊት ማስክ ሙሉ ቀን ታፍኖ ይውላል:: አንዳንዱም ማስኩን እንደ ውስጥ ሱሪ እያጠበ ይጋግሞ ያሸርጣል:: በሽታው እኔን አይይዘኝም እያለ የሚፎልልም አለ:: ይህ አንድ ታሪክ ያስታውሰኛል:: ከ90 ዓመት በፊት የአጼ ኃይለሥላሴ አጎት ደጃች ወልደ ሥላሴ ለመንግሥት ሥራ በአውሮፕላን ወደ ደሴ ያመራሉ:: ሲመለሱ አውሮፕላኗ የቴክኒክ ችግር ስለገጠማት ፓይለቶቹ በሰላም ለማረፍ ትግል ያዙ:: በዚህ ጊዜ ተሳፋሪዎች ቀበቷቸውን አጥብቀው እንዲያስሩ ሲነገራቸው ደጃች ወልደ ሥላሴ አሻፈረኝ አሉ:: ይባስ ብለው ቆመው ይፎክሩ ጀመር:: አውሮፕላኑ ሲያርፍ ራሳቸውን በኃይል መቷቸው ከተሳፋሪዎቹ መካከል እሳቸው ብቻ በአደጋው ሞቱ። አደጋ ሲያንዣብብ ቀበቶን ጠበቅ አድርጎ የሚሰጡ መመሪያዎችን መተግበር ሕይወትን ይጠብቃል::
ነጭ ሽንኩርት ይሸረክተዋል፤ ፌጦ ይፈጠፍጠዋል፤ ጤና ዳም ጤና ያሳጣዋል በሚል መዘናጋት ሕይወት ያስከፍላል:: በዓለም የጤና ድርጅት እውቅና ያልተሰጠውን አዲስም ሆነ ነባር መድኃኒት መጠቀም ራስ ላይ አደጋ መጋበዝ ነው::መድኃኒት አገኘሁ ባዩ የበዛው ጭንቀት በፈጠረው ስካር ምክንያት ይመስለኛል:: የፈጠራ እናት ችግር አይደለች:: እንዲያውም ትምህርት ቤት ለረጅም ጊዜ የሚዘጋ ከሆነ ሳይንቲስቶችን ቀድመው የቆረናን መድኃኒት የሚያገኙት ወላጆች ናቸው::
እኔ የምለው ተጨማሪ የቆሮና ቫይረስ ተጠቂ በተገኘ ቁጥር ሚዲያዎቻችን ሰበር ዜና እያሉ የሕዝቡን ቀልብ ባይሰብሩ ምናለበት? ጤና ሚኒስቴር እንዲህ የሚል መግለጫ ሰጠ እያሉ ቢዘግቡ ይሻላል:: በዚህ የጭንቅ ወቅት እንኳን መርዶ የምስራችን በሰበር ዜና መንገር ገድሎ ማዳን ነው:: የሕዝብን ሥነልቦና አጢኖ ከአስበርጋጊ ይልቅ አረጋጊ ቃላትን መጠቀም ይገባል:: ሚዲያዎቻችን ጭንቀታችንን በልኩ የተረዱት አይመስሉም:: የመታን ድንጋጤ የታክሲ ውስጥ ጥቅስ ሳይቀር አስቀይሮናል:: «ማስነጠስ ክልክል ነው» የሚል ጥቅስ አላነበባችሁም? … የጨነቀ ዕለት ያለው ማን ነበር::
አንዳንድ የጤና ባለሞያዎች ግን ቆሮና መዓት ብቻ ሳይሆን በረከትም ይዞልን እንደመጣ እየተናገሩ ነው:: እጅን በሚገባ የማጽዳት ባህልን ይገነባል:: ይህ ደግሞ የእጅን ንጽህና ባለመጠበቅ በሚመጡ በሽታዎች እየተመዘገበ ያለውን እልቂት ያስቆማል:: የቆሮና መልሶ ማልማት እንበለው ?
አዲስ ዘመን መጋቢት 16 /2012
ቆረና