በኢትዮጵያ ህብረተሰቡን በከፍተኛ ደረጃ እያጠቁ ከመጡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ውስጥ አንዱ የኩላሊት ህመም መሆኑ ይታወቃል። ህመሙ በተለይ አምራች የተባለውን የህብረተሰብ ክፍል በማጥቃትና ከፍተኛ የህክምና ወጪ በማስወጣት የማህበረሰቡንና የሃገር ኢኮኖሚ እየጎዳ ይገኛል።
በአብዛኛው የሚከሰተው የሰዎች የአኗኗር ዘይቤ መለወጥን ተከትሎ በመሆኑ ጤናማ የአመጋገብ ስርዓትን መከተል፣ ከተለያዩ ሱስ አስያዥ እፆች ራስን ማራቅና በየቀኑ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ህመሙን ለመከላከል ዋንኛ መፍትሄ መሆናቸውን የጤና ባለሞያዎች ይጠቁማሉ።
እየጨመረ የመጣውን የኩላሊት ህመም ለመቀነስ የአለም ኩላሊት ህመም ቀን በልዩ ልዩ የግንዛቤ ማስጨበጫዎች በየአመቱ ይከበራል። ዘንድሮም ቀኑ ‹‹የኩላሊት ጤንነት በሁሉም ቦታ ለሁሉም ሰው›› በሚል መሪቃል በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል። የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅም ቀኑን አስመልክቶ የነፃ የኩላሊት ምርመራ ለህብረተሰቡ በማድረግና እየሰጣቸው ያሉትን የኩላሊት ህክምና አገልግሎቶች አስተዋውቋል።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የኩላሊት ንቅለተከላ ዳይሬክተር ዶክተር ፀጋይ ብርሃነ እንደሚገልት፤የኩላሊት ህመም ከመከሰቱ በፊት የአኗኗር ዘይቤን በማስተካከል፣ ኩላሊት ከመታመሙ ወይም ከመጎዳቱ በፊትና ከተጎዳ በኋላ እንዳይባባስ መከላከል ይቻላል። የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታልም በነዚሁ መንገዶች የኩላሊት ህመምን ለመከላከል እየሰራ ይገኛል። ሆስፒታሉ በዋናነት እየሰራ ያለው ኩላሊት ከተጎዳ በኋላ በሚሰጥ የህክምና አገልግሎት ላይ ቢሆንም፣ ህመሙ ከመከሰቱ በፊት አስቀድሞ የመከላከሉ ስራ ሁሌም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። የአለም ኩላሊት ቀንን አስመልክቶም 200 ለሚሆኑ ሰዎች የነፃ ኩላሊት ምርመራ አድርጓል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ሆስፒታሉ የኩላሊት ንቅለ ተከላ አገልግሎት በአንድ ወር ለአራት ሰዎች በመስጠት እስከአሁን ድረስ 140 ለሚሆኑ ሰዎች አገልግሎቱን ማዳረስ ችሏል። ይህም የኩላሊት ንቅለ ተከላ በራስ ባለሙያ በሀገር ውስጥ መስራት እንደሚቻል ትልቅ ማሳያ ነው። ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ይህን ልምድ መንግስት ጥናት አድርጎበት የታዩ ክፍተቶችን አርሞና ጠንካራ ጎኖችን አዳብሮ ወደ ሌሎች ማዕከላት እንዲሰፋ ማድረግ ይኖርበታል።
ሆስፒታሉ ጊዚያዊ የኩላሊት ህመም ላጋጠማቸውና በአጭር ጊዜ ውስጥ ድነው ለሚሄዱ የኩላሊት ታማሚዎች የኩላሊት እጥበት አገልግሎት ይሰጣል። እስካሁንም 3 ሺ የሚጠጉ ታካሚዎች በአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል። 310 ለሚሆኑና የከፋ የኩላሊት ጉዳት ለደረሰባቸው ታማሚዎችም ተመሳሳይ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት ተሰጥቷል። ይሁንና አሁንም1 ሺ 500 ያህሉ የኩላሊት እጥበት ለማድረግ ወረፋ እየተጠባበቁ ይገኛሉ። ለዚህም ምክንያቱ የህክምናው ውድነትና የኩላሊት ማጠቢያ ማሽኖች ቁጥር ውስንነት በመሆኑ በዋናነት ቅድመ መከላከል ላይ በማተኮር መስራት ያስፈልጋል።
አብዛኛቹ የሃገሪቱ የኢንሹራንስ ህጎች የኩላሊት እጥበትን የማያጠቃልሉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ መንግስት የኢንሹራንስ ህግ ሊያዘጋጅ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የዲያሊሲስ ዩኒት ሃላፊ ዶክተር ሊና መሃመድ እንደሚሉት፤ በሆስፒታሉ የሚሰጠው የኩላሊት እጥበት አገልግሎት በስድስት ማሽኖች ተጀምሮ ሰላሳ ሁለት ደርሷል። ሰላሳ ሁለቱ ማሽኖች በፈረቃ ስልሳ አራት ሰዎችን ያስተናግዳሉ።
የኩላሊት እጥበት ህክምና በየትኛውም ሃገር ውድና በሃገር ኢኮኖሚ ላይም የራሱ ተፅዕኖ ያለው መሆኑን ጠቅሰው፣ አገልግሎቱ እንዲሰፋ ብዙም አይመከርም ይላሉ። ከዚህ ይልቅ አመጋገብን በማስተካከል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በማድረግና የደም ግፊትን በመቆጣጠር የኩላሊት ህመምን አስቀድሞ መከላከሉ እንደሚመከር ያስገነዝባሉ። ይህም የኩላሊት እጥበት የሚፍልጉ ታካሚዎችን ቁጥር መቀነስ እንደሚያስችል ይጠቁማሉ።
እንደ ሃላፊዋ ገለፃ፤ የኩላሊት እጥበት ህክምና አገልግሎቱን ከማስፋት ይልቅ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማድረጉ ተመራጭ በመሆኑ በዚህ ላይ ማተኮሮ የበለጠ ያዋጣል። መንግስት ዝም ብሎ የኩላሊት ማጠቢያ መሽኖችን በየጊዜው ቢጨምር ውድና ኢኮኖሚንም የሚፈታተን በመሆኑ ማሽን ከውጪ በማምጣትና የኩላሊት እጥበት አገልግሎትን በማስፋት ብቻ ችግሩን መፍታት አይቻልም። በመሆኑም በሽታውን መከላከል ላይ አተኩሮ መስራትና የኩላሊት ንቅለ ተከላ አገልግሎቶን በሌሎች ሆስፒታሎች ውስጥ ማስፋት ያስፈልጋል።
በሆስፒታሉ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ነርስ አስተባባሪ ሲስተር ሃይማኖት ሃይለማርያም እንደሚገልፁት፤በሆስፒታሉ የኩላሊት እጥበት የሚደርግላቸው ለኩላሊት ንቅለ ተከላ ዝግጁ የሆኑት ብቻ ናቸው። አገልግሎቱን የሚያገኙትም ለዚሁ ታስቦ የተቋቋመው ኮሚቴ የመጨረሻውን ምርመራ ካደረገላቸው በኋላ ነው። የንቅለ ተከላው የኩላሊት እጥበት ዩኒቱ በዋናነት የተቋቋመው ንቅለ ተከላ ለሚደረግላቸው የኩላሊት ታማሚዎች ቢሆንም፣ ሆስፒታሉ የከፋ የኩላሊት ጉዳት ደርሶባቸው ለሚመጡና በግላቸው የኩላሊት እጥበት ለሚያደርጉ አገልግሎት ይሰጣል።
እንደ አስተባባሪዋ ማብራሪያ፤ በሆስፒታሉ የሚደረገው የኩላሊት ቀዶ ህክምናና ንቅለ ተከላ ሙሉ በሙሉ በመንግስት ይሸፈናል። በዚህም ማንኛውም ታካሚ ለንቅለ ተከላው ምንም አይነት ክፍያ አይፈጽምም። ከንቅለ ተከላው በኋላ የሚያስፈልጉ የመድሃኒት ወጪዎችን መሸፈን የማይችሉና ገቢያቸው ዝቅተኛ የሆኑ በማዕከሉ ንቅለ ተከላውን እንዲያደርጉ አይፈቀድም። በዚህም ምክንያት ጎዳና ላይ ለልመና ሲወጡ ይታያሉ። ከተቋሙ አቅም በላይ የሆኑ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሲያጋጥምም ታካሚዎች ውጭ ሃገር ሄደው እንዲታከሙ ቦርዱ ደብዳቤ ይፅፋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/ 2012
አስናቀ ፀጋዬ