
የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የህግ የበላይነትን በማስከበር በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለውን የሰላምና ጸጥታ ችግር ለማስወገድ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች ገልጿል። አሁን ላይ ሰላምና ጸጥታ የማስከበር እንቅስቃሴ ምን ገጽታ አለው በሚል አዲስ ዘመን ከክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርቧል።
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ አልፎ አልፎ የሚታየው የጸጥታ ችግር መንስኤው ምንድነው?
አቶ ጌታቸው፡- እንደሚታወቀው ለውጡን ተከትሎ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የጸጥታ ችግሮች ተስተውለዋል። በኦሮሚያ ክልልም የተስተዋለው ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው። በጉዳዩ ዙሪያ የክልሉ መንግስት ሁል ጊዜ ህዝቡን በማወያየት የአካባቢውን ጸጥታ እራሱ እንዲጠብቅ የማድረግ ስራ ሰርቷል። ከዚህ ጎን ለጎን የጸጥታ አካላትን በተደራጀ መንገድ ችግሮች ወዳሉባቸው ቦታዎች በማሰማራት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ተሞክሯል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የክልሉን ጸጥታና ሰላም የማረጋገጥ ስራ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል። በመሆኑም የጸጥታ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎችን በመለየት በጸረ ሰላም ሃይሎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- የጸጥታ ችግር አለባቸው ተብለው የተለዩ አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው? ጸጥታን የሚያደፍርሱትስ እነማን ናቸው? በውል ይታወቃሉ?
አቶ ጌታቸው ፡- ምዕራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮጉድሩና ቄለም ወለጋ ዞኖች እንዲሁም ደቡብ ምዕራብ ጉጂ ዞን ችግሩ የታየባቸው አካባቢዎች ናቸው። የእነዚህን አካባቢዎች ጸጥታ የሚያውኩት ለውጡን ተከትሎ የተለያየ ፖለቲካዊ አመለካከት ያላቸው የተደራጁም ሆኑ በተናጠል የሚንቀሳቀሱ አካላት ናቸው። እነዚህ ቡድኖች ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ እና ለራሳቸው ነጻ አውጭ ጦር የሚል ስያሜ የሰጡ ነገር ግን በየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ዕውቅና የሌላቸው የጥፋት ሃይሎች ናቸው። መንግስት ዓላማቸውን ለማራመድ ዕድል ያላገኙ ዜጎች በሰላማዊ መንገድ ሀገራቸው ገብተው እንዲንቀሳቀሱ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋቱን ተከትሎ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ። አንዳንዶች ግን ያገኙትን አጋጣሚ በተሳሳተ መንገድ በመተርጎምና ህብረተሰቡን በማወክ በክልሉ ሰላምና ጸጥታ ላይ ችግር ፈጥረዋል። እነዚህ ሃይሎች መንግስት በተደጋጋሚ በሰላማዊ መንገድ ሃሳባቸውን እንዲገልጹ ጥሪ ቢያደርግላቸውም የተሰጣቸውን ዕድል መቀበል ያልፈለጉ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ታጣቂ ቡድኖቹ ምን ምን ጉዳቶችን አድርሰዋል?
አቶ ጌታቸው፡- አንዳንዴ ጫካ ውስጥ መሽገው ግድያና ዝርፊያ ይፈጽማሉ፤ አንዳንዴም ደግሞ ወደ ከተማ በመግባት በመንግስት ተቋማትና በግለሰቦች ላይ ጥቃት ያደርሳሉ። ነዋሪዎች ተረጋግተው እንዳይኖሩና ሀሳባቸውን በነጻነት እንዳይገልጹም ያስፈራሯቸዋል። በአጠቃላይ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ያደረሱት ጉዳት በደንብ ተጠንቶ ወደ ፊት በዝርዝር የሚቀርብ ቢሆንም ጉዳታቸው በግልጽ የሚታይና በክልሉ ሰላም ላይ ተጽዕኖ የፈጠረ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በተወሰደው እርምጃ ምን ውጤት ተገኘ ?
አቶ ጌታቸው፡- የሽምቅ ተዋጊዎቹ ባሉበት አካባቢ ያለውን አለመረጋጋት ለማስተካከል የክልሉና የፌዴራል ጸጥታ ሃይል በተቀናጀና ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ የህግ የበላይነትን የማስከበርና ሰላምን የማረጋገጥ ስራ ሰርተዋል። በተወሰነ ደረጃ ህዝቡን ማረጋጋትና ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴው የመመለስ ውጤታማ ተግባር ታይቷል። በምዕራብና ቄለም ወለጋ በተለይ ሰሞኑን በተጠናከረ ሁኔታ በተደረገ ዘመቻ እርምጃ በመወሰዱ፣ ታጣቂዎች እጃቸውን የሰጡበትና ለህግ የቀረቡበት ሁኔታ አለ፡ እርምጃው በሁለት መልክ የተወሰደ ነው። ታጥቀው በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ያሉበትን ቦታ በመለየት እርምጃ ሲወሰድ በሌላ በኩል ከተማ ተቀምጠው የማስተባበርና የመምራት ሚና የነበራቸውንም ለህግ የማቅረብ ስራ ተሰርቷል። በዚህም ቀጣናው መሻሻል ታይቶበቷል።
አዲስ ዘመን ፡- በቅርቡ በቡራዩ ከተማ ጸጥታ ዘርፍ አመራር ላይ በተፈጸመው ግድያ የእነዚህ አካላት እጅ አለበት ተብሎ ይታመናል?
አቶ ጌታቸው፡- በእርግጠኝነት፤ ይህ አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ጸረ ሰላሞች እንዲህ አይነት ተግባርን በተለያዩ አካባቢዎች ይፈጽማሉ። በአንድ በኩል ህዝቡን የማደናግርና ብዥታ ውስጥ የመክተት ስራ ይሰራሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አጋጣሚዎችን ተጠቅመው ግድያ ይፈጽማሉ። በተለያዩ ቦታዎች እየተከሰቱና ባልታዩበት አካባቢ እንዲታዩ በመሆን ብዙነን አለን የሚል መልዕክት በማስተላለፍ በህብረተሰቡ ላይ የስነ ልቦና ጫና ይፈጥራሉ። በከተማ የተደራጀ ስኳድ አዘጋጅተው ያስፈራራሉ፤ ይዘርፋሉ፣ ሲፈልጉም በራሳቸው ፍርድ ይገድላሉ። ስለዚህ ገዳዮችን አደራጅተው የሚያንቀሳቀሱ እስከሆነ ድረስ በተለያዩ ሰዎች ግድያ እጃቸው አለበት። በዚህ የተጠረጠሩትም እየተያዙ ለህግ እየቀረቡ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን ፡- ክልሉ የጸጥታ ችግር አለባቸው ባላቸው የወለጋና የጉጂ ዞኖች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ነበር እንዴ?
አቶ ጌታቸው፡- በክልሉ የታወጀ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የለም። ነገር ግን የተጠቀሱት አካባቢዎች የጸጥታ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ የክልሉና የፌዴራል መንግስት የጸጥታ ሃይሎች በጋራ ሆነው የአካባቢውን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ የህግ የበላይነትን እና ጸጥታን በማስከበር ስራ ላይ ተሰማርተዋል። ይህ አልመች ያላቸው አካላት ናቸው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆብናል የሚሉት። ክልሉ መቼም ቢሆን ጸጥታ የማስከበር ስራውን መስራቱን አያቆምም። እንደውም አጠናክሮ ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን ፡- ታግተዋል የተባሉ ተማሪዎች ጉዳይ በነዚህ አካላት የተፈጸመ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ጌታቸው፡- እንግዲህ አጋቹ አካል አግቻለሁ ብሎ ካልተናገረና የታገቱበት ዓላማ ካልታወቀ፣ ታጋቾቹ የት እንዳሉ በግልጽ ካልተነገረ፣ ይህ ቡድን አግቷቸዋል ብሎ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። እስከ አሁን እራሱን በዚህ ደረጃ የገለጸ አካል የለም። በፌዴራል ደረጃ ጉዳዩን የሚከታተል ሃይል ስላለ የተገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግ እገታው ምን ዓላማ እንደነበረውና ማን እንደፈጸመው የሚመለከተው አካል ወደ ፊት ሊገልጽ ይችላል።
አዲስ ዘመን ፡- በክልሉ ምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ አካባቢ በከረዩ እና በኢቱ ጎሳዎች መካከል ግጭት ተፈጥሮ እንደ ነበር ይታወሳል። የግጭቱ መንስኤ ምንድን ነው ?
አቶ ጌታቸው፡- አካባቢው የአርብቶ አደር መገኛ እንደመሆኑ በግጦሽና በውሃ ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት ግጭቶች ሊከሰቱ ይችላሉ። የከረዩም ሆነ የኢቱ ጎሳዎች ሁለቱም የኦሮሞ ብሄረሰቦች ናቸው። ግጭቱ ሲከሰት በመጀመሪያ ህብረተሰቡ ባህላዊ ስርዓቱን ጠብቆ ችግሮችን እንዲፈታ የማድረግ ስራ ተሰርቷል። የሀገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎችም ወደ ቦታው በመሄድ የማስታረቅ ስራ ሰርተዋል። የማጋጨት ሚና የነበራቸውን ግለሰቦችም ለህግ እንዲቀርቡ ተደርጓል። ከህዝቡና ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን አጥፊዎችን የማጋለጥ ስራ በመሰራቱ የተሻለ መረጋጋት ተፈጥሯል።
አዲስ ዘመን ፡- በግጭቱ የደረሰውን ጉዳት ማወቅ ይቻላል?
አቶ ጌታቸው ፡- በግጭቱ ከሁለቱም ወገን ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች አሉ። ንብረተም ወድሟል። የክልሉ መንግስት የመጀመሪያ ተግባርም ግጭቱን ማስቆምና ማረጋጋት ነበር ፤ ይህም ተደርጓል። በቀጣይ ምንያህል ጉዳት ደረሰ የሚለው ይጣራል። በቀጣይ ችግሮች እንዳይከሰቱ ከአካባቢው ማህበረሰብ፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና ከአባ ገዳዎች ጋር በመሆን እየተሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፡-በክልሉ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች የጸጥታው ሁኔታ ምን ይመስላል?
አቶ ጌታቸው፡- ዩኒቨርሲቲዎችን በበላይነት የሚከታተለው ፌደራል መንግስት ቢሆንም የቦርድ አመራሮች ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን የዩኒቨርሲቲዎችን እና የአካባቢውን ማህበረሰብ የማወያየት ስራ ተሰርቷል። በዚህ መሰረት በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ሰላማዊ ሁኔታዎች እየታየ ነው። ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሁኔት እንዲፈጠር ክልሉ ከሚመለከታቸው የፌዴራል ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ እየሰራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- መጪው ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ክልሉ ምን እየሰራ ነው?
አቶ ጌታቸው፡- ምርጫ ማለት ህዝቦች ወደ ስልጣን ማምጣት የሚፈልጉት አካል በድምጻቸው የሚወክሉበት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ነው። የዘንድሮው ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች በተሻለ ሁኔታ ፍትሃዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ተአማኒ እንዲሆን ታስቦ እየተሰራ ነው። ምርጫውን በዚህ ደረጃ ውጤታማ ለማድረግ የጸጥታ አካላት ሚና ከፍተኛ ነው። በክልሉ ያሉ የጸጥታ አካላት ግንዛቤ አግኝተው ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ በመሆን ምርጫውን ሰላማዊ የማድረግ ተልዕኳቸውን እንዲወጡ እየተደረገ ነው። ምንም አይነት ሁኔታዎች ምርጫውን እንዳያደናቅፉ ከወዲሁ ትኩረት ሰጥቶ የመስራቱ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
አዲስ ዘመን ፡-የክልሉን ህዝብ አንድነት የሚፈታተኑ ሁኔታዎች እየተስተዋሉ ነው የሚሉ አካላት አሉ ምን ምላሽ አለዎት?
አቶ ጌታቸው፡- በኦሮሞ ህዝብ መካከል ልዩነትን ለመፍጠር የሚፈልጉ ፖለቲከኞች ቢኖሩም ህዝቡ ግን መቼም ቢሆን በአንድነቱ ጉዳይ ክፍተት ፈጥሮ አያውቅም። በዚህ ደረጃ የሚታሰብ ነገር ሊኖርም አይችልም። የኦሮሞ ህዝብ በኦሮሞነቱ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያዊነቱም ጭምር የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን አቅፎና ደግፎ የያዘ እንጂ እርስ በእርሱ የሚገፋፋና የሚከፋፈል አይደለም። እንዲህ አይነት ታሪክም የለውም። አጀንዳ ያጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አጀንዳ ለመፍጠር የሚያናፍሱት አሉባልታ ካልሆነ በስተቀር የኦሮሞ ህዝብ ምንም አይነት ልዩነት በመካከሉ አልተፈጠረም ፤ ወደ ፊትም አይፈጠርም። ህዝቡ የራሱ ባህል ያለውና በገዳ ስርዓት የሚተዳደር ከራሱ አልፎ ለሌሎችም የሚተርፍ የሰላም ፣ የአንድነትና የመቻቻል እሴት ያለው ህዝብ ነው። ልዩነት ተፈጥሯል ብለው በሁኔታዎች ለመጠቀም የሚፈልጉ አካላት ካሉ መቼውም ቢሆን ሊሳካላቸው ስለማይችል ከዚህ እኩይ አላማቸው መታቀብ ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ ሰሌዳ አስቀድመው የምረጡን መሰል ዘመቻ ሲያደርጉ ይስተዋላል። ይህም ብቻ ሳይሆን ተገቢ ያልሆነ ንግግር ሲያደርጉ ይደመጣል። እንዲህ አይነት ሁኔታዎች በክልሉ ሰላምና ጸጥታ ላይ ተጽዕኖ አይኖራቸውም? ክልሉ ሁኔታውን እንዴት ያየዋል?
አቶ ጌታቸው፡- ይህ ጉዳይ የክልሉን መንግስት ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ብቻ የሚመለከት አይደለም። በአጠቃላይ ህዝቡም፣ የምርጫ ቦርድም፣ መንግስትም እንደዚህ አይነት አካሄዶችን ሃይ ማለት ይገባቸዋል። የሀገራችን የምርጫ ሥርዓት በህግ የተደነገገ የራሱ ደንብና መመሪያ ያለው ቢሆንም እንደተባለው ግን ጊዜውን ያልጠበቀ ቅስቀሳ ከማድረግ ባለፈ የማስፈራራት፣ ሃሳባቸውን የማይደግፈውን የማሸማቀቅ እና አላስፈላጊ እንቅስቃሴዎችን የማድረግ ሁኔታ ታይቶ ነበር። በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ እጃቸው ያለበት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለሚመለከተው የምርጫ ቦርድ በማሳወቅ አካሄዳቸውን እንዲስተካከሉ ለማድረግ ተሞክሯል።
አዲስ ዘመን ፡- ክልሉ ልዩ ሃይል ሰልጣኞችን ከማስመረቁ ጋር ተያይዞ አንዳንድ አካላት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተለያየ አንድምታ ያላቸውን ሀሳቦች ሲሰነዝሩ ይታያል። ክልሉ ልዩ ሃይሉን ለማጠናከር የፈለገበትን ምክንያት እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ጌታቸው፡- የክልሉን የጸጥታ ሃይል ማጠናከር የክልሉን ሰላም ከማጠናከር ውጭ ሌላ ምንም አንድምታ ሊኖረው አይችልም። ክልሉ ካለው የቆዳ ስፋትና የህዝብ ብዛት ፣በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከሚታዩ የጸጥታ ችግሮች አንጻር አሁንም የጸጥታ ሃይሉ ቁጥር ያንሳል እንጂ አይበዛም። ስለዚህ በአግባቡ የሰለጠነና የስነ ልቦና ዝግጅት ያደረገ ፣ በየትኛውም የክልሉ አካባቢዎች ተደራሽ መሆን የሚችል፣ ብቃት ያለውና ለህዝብ የወገነ የጸጥታ ሃይል ያስፈልገዋል። ክልሉ ባለው ስልጣን እንደሌሎች ክልሎች ሁሉ የራሱን የጸጥታ አካላት ከክልል እስከ ቀበሌ በማደራጀት የክልሉን ሰላም ያስጠብቃል። በየሰፈሩ እየተደራጁ ክልሉን የሚያውኩ ህገ ወጦች እንዳይኖሩና ከርቀት ሆነው እጃቸውን እየዘረጉ ክልሉን የሚያውኩትም እድል እንዳያገኙ ልዩ ሃይልን ማጠናከር አስፈልጓል። በአጠቃላይ የልዩ ሃይሉ አስፈላጊነት የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅና የህግ የበላይነትን ለማስፈን ነው።
አዲስ ዘመን ፡- በቀጣይ የክልሉን ጸጥታ ከማስከበር አንጻር የተያዘው አቅጣጫ ምን ይመስላል ? ጸጥታውን ለማስከበር የሚወሰደው ርምጃስ የፖለቲካ ምህዳሩን አያጠበውም?
አቶ ጌታቸው፡- በክልሉ የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። ከዚህ በተረፈ ግን በሃይል ተጠቅሞ ክልሉን ለማተራመስ የሚፈልግ ሃይል በፍጹም ሊኖር አይገባም። ከዚህ በኋላ የህግ የበላይነትን የማስከበር ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ አይሆንም። በየደረጃው ያለው የጸጥታ አካልም ሆነ አመራሩ በጉዳዩ ላይ አጽንኦት ሰጥቶ እንዲሰራ አቅጣጫ ተቀምጧል። ክልሉን ሙሉ ለሙሉ ከጸጥታ ችግር ለማላቀቅም አቋም ተይዞ ወደ ተግባር በመገባቱ አበረታች ለውጥ እየታየ ነው። ይህ ወደ ፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ለክልሉ ህዝብ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ምንድን ነው?
አቶ ጌታቸው፡- የክልሉ ህዝብ ምንግዜም የአካባቢውን ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር ጥረት ያደርጋል። ለተለያዩ ጸረ ሰላም ሃይሎች እጁን ሳይሰጥ ይልቁንም የጸጥታ አካሉን በመተባባር ላደረገው ትብብርም ምስጋና ይገባዋል። መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እና አጥፊዎችን በህግ ፊት ለማቅረብ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ እንዲያግዝና የአካባቢውን ሰላምና ጸጥታ እንዲጠብቅ ለክልሉ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው የሀገሪቱ ህዝቦች መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን ፡- ለቃለ መጠይቅ ስለተባበሩኝ አመሰግናለሁ።
አቶ ጌታቸው ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/ 2012
ኢያሱ መሰለ