ዓለማችን ከሶስት ወራት በፊት ነበር ከቻይናዋ ሁቤይ ግዛት አስደንጋጭ ዜና የሰማችው። አደገኛና ገዳይ መሆኑ የተነገረለት ‹‹ኮሮና›› የተሰኘው ቫይረስ በግዙፍ የኢኮኖሚ ባለሀብቷ አገር መከሰቱ በተስተጋባ ቅፅበትም ኤሲያዊቷ አገር ከመደናገጥ ይልቅ ‹‹ወረርሽኝኙን ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም አለኝ›› ያለችው በፍጹም የራስ መተማመን ነበር።
ቫይረሱ ግን እንዳቀለሉት የሚቀል አልሆነም። በብርሃን ፍጥነት ለማለት በሚያስደፍር መልኩ በቀናት ልዩነት መላ ቻይናን በማዳረስ ዜጎቿን ከመንጠቅም አልተቆጠበም። ይህን ያስተዋሉ አገራትም አስከፊው ቫይረስ ድንበራቸውን አቋርጦ እንዳይገባ ከገባም ጉዳቱን ለመቀነስ ወደ ቻይና የሚደረጉ በረራዎችን መቀነስን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስደዋል። ድካማቸው ግን ፍሬያማ አልሆነም።
ከቻይና ውሃን ግዛት የተነሳው ወረርሽኝም በአሁኑ ወቅት ሰው ከማይኖርበት አንታርክቲክ ውጪ ሁሉንም የዓለማችንን አህጉራት በማዳረስ የምድራችን ዋነኛ የጤና ስጋት ሆኗል። ወረርሽኙን በተመለከተም እያደር አስደንጋጭ፣ አሳዛኝና ተስፋ አስቆራጭ ዜና እንጂ የምስራች የሚሆን ሳይሰማ ቀናት፣ ሳምንታት እና ወራት መፈራረቃቸውን ቀጥለዋል።
ዘርና የቆዳ ቀለምን ሳይመርጥ ሁሉንም የሚያጠቃው ይህ ወረርሽኝ ደሃ ሀብታም ፣ አዋቂና ታዋቂ፣ መሪና ተመሪን ሳይለይ ሁሉንም በማጥቃት ከእስያ እስከ አሜሪካ፣ ከአውሮፓ እስከ መካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ መላውን ዓለም በስጋት አርዷል።
እስካሁንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሀገራት ቁጥር ከ177 በላይ ደርሷል። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜም በቫይረሱ ምክንያት ከአስራ አምስት ሺህ በላይ ሰዎች ህይወት አልፏል፤ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ351 ሺህ በላይ ደርሷል። እስካሁን ባለው ሂደት በ43 የአፍሪካ አገራት ውስጥ ከ1 ሺ በላይ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች መገኘታቸውንና ከ20 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ አድርጓል።
በቫይረሱ የተነሳም በርካታ የዓለማችን ከተሞች ረጭ ብለዋል። በዚህ ድባብ የተከበቡት የአፍሪካ አገራትም ቫይረሱ፣ ድንበራቸውን ጥሶ እንዳይገባ ከገባም ጉዳቱን ለመቀነስ በርካታ ስራዎችን በከመከወን ላይ ተጠምደዋል።
አንዳንድ አገራት ብሄራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጅ እስከ ማወጅ ደርሰዋል፤ በዚህም ሰዎች በተቻለ መጠን ቤታቸው እንዲቆዩ አስጠንቅቀዋል። ትምህርት ቤቶች፣ ጂምናዚያዎች፣ ሙዚየሞች፣ ጭፈራ ቤቶች፣ ካፌዎች፣ ሬስቶራንቶችና ሌሎችም ተመሳሳይ የመዝናኛና ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ዝግ አድርገዋል። ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ ከተስፋፋባቸው ሀገራት የሚመጡ መንገደኞች ድንበር እንዳይሻገሩና ዜጎቻቸውም ቢሆኑ ወደ አገራቱ እንዳይጓዙ እገዳ ጥለዋል።
የአፍሪካውያኑ ይህ ቫይረሱን የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባር የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖምን ጨምሮ የበርካቶችን አድናቆትና ሙገሳ ተችሮታል። ይሁንና የቫይረሱ ስርጭት እያደር በአህጉሪቱ መንሰራፋቱ በርካቶች አድናቆታቸውን አቋርጠው በስጋት እንዲርዱ አስገድዳቸዋል።
ስኬቱ እንዳለ ሆኖ ስጋቱ ያስጨነቃቸው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖምም፣ ‹‹አፍሪካውያን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን አስመልክቶ ሊከሰት ከሚችል የከፋ ሁኔታ ራሳቸውን ለመጠበቅ ዝግጁነታቸውን ማጠናከር አለባቸው›› ሲሉ አሳስበዋል። ይህም አህጉሪቱንና ዜጎቿን ይበልጡን አስደንግጧል።
በርካታ መገናኛ ብዙሃንና ምሁራም ዳይሬክተሩን ከመውቀስ ይልቅ ስጋቱ አግባብ ስለመሆኑ አፅእኖት ሰጥተው እያሳሰቡ ይገኛሉ። ‹‹በእርግጥም አፍሪካው ከኮሮና ቀወስ ከባድ ጡጫ በቀላሉ ማምለጥ አይቻላትም›› ያሉት ምሁራኑ፣ ለዚህ እሳቤ ምክንያት የሚሉትን መንስኤዎችም በዝርዝር አስቀምጠዋል።
ከእነዚህ ፀሃፍት መካከል አንዱ የሆነው ጆን ካምቤል በካውንስል ኦን ፎሬን አፌርስ ላይ ባሰፈረው ሰፊ ሀተታ፣ የቫይረሱ ስርጭት ከሌሎች አህጉራት አንፃር በፍጥነት መስፋፋት ባይችልም፣ የአፍሪካ የጤና ሥርዓትና አገልግሎት አሰጣጥ ደካማነት ግን አህጉሪቱ ይበልጥ የቫይረሱ ተጋላጭ ያደርጋት እንደሚችል አትቷል።
ከዓለማችን የህዝብ ቁጥር 16 በመቶ የሚሆነውን የምትወክለው አፍሪካ፣ ለጤናው ዘርፍ የምትመድበው በጀት አንድ በመቶ ብቻ መሆኑን ያመላከተው ፀሃፊው፣ ‹‹ለአብነት በአሁኑ ወቅት በወረርሽኙ ክፉኛ በመጎዳት ላይ የምትገኘው ጣሊያን በአማካኝ ለ10 ሺ ሕዝብ 41 ሜዲካል ዶክተሮችን ስታቀርብ፣ አፍሪካ በአንፃሩ ሁለት ሜዲካል ዶክተሮች ለ 10 ሺ ታብቃቃለች›› ብሏል።
በዓለም ጤና ድርጅት የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብራዛቪል ማእከል የቴክኒካል ባለሙያ ዶክተር ሜሪ ስትፈንም፣ አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ህዝብ በሚኖርባት አፍሪካ የጤና መሰረተ ልማትና አገልግሎት አሰጣጥ ደካማ መሆን የወረርሽኙን መስፋፋት አስጊ እንደሚያደርገው አስምረውበታል።
አፍሪካ በዚህ ድክመቷ ኢቮላን ጨምሮ ሌሎች አሳሳቢና ቁጥጥር የሚሹ አደገኛ ቫይረሶችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የምታደርገው ርብርብ ሲዳመርበት በአዲሱ ወረርሽኝ የመደቆስ አጋጣሚውን ከፍ እንደሚያደርገው ያመለክታሉ።
‹‹በአሁኑ ወቅትም የአህጉሪቱ ሆስፒታሎች የኮሮናን ቫይረስ ወረርሽን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተለይ በርካታ ቁጥር ያለው ህመምተኛ ለማስተናገድ በቂ ቅድመ ዝግጅት አድርገዋል፤ አስፈላጊውን ህክምና ለመስጠትስ ዝግጁ ናቸው››? ተብሎ ከተጠየቀ መልሱን ለማግኘት አስቸጋሪ ስለመሆኑም ተጠቁሟል። ይህን ሃሳብ የሚጋሩት የማይክሮሶፍት መስራቹ አሜሪካዊው ቢሊየነር ቢል ጌትስም፣ የአፍሪካ የጤና አገልግሎት ደካማ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህ የተነሳም ኮሮና ከ10 ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያንን ሊገድል ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ወረርሽኙ በአፍሪካ በተሻለ የኢኮኖሚ እድገት ላይ የምትገኘውና በጤና መሰረተ ልማት በጎለበተችው ደቡብ አፍሪካ ላይ እያስከተለ ያለውን ኪሳራ ዋቢ የሚያደርጉ ምሁራንም፣ ከዚህ በመነሳትም ወረርሽኙ በሌሎች ደካማ አገራት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጥፋት ለመረዳት አዳጋች እንደማይሆን ጠቁመዋል።
ለዚህ እሳቤያቸው ዋቢ ማስረጃነትም በአህጉሪቱ የጤና መሰረተ ልማትና የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ደካማ የሆነችውንና ለዓመታት በጦርነት ስትታመስ የሰነበተችው ሶማሊያን ምሁራኑ ይጠቅሳሉ። ምሁራኑ በተለይ ‹‹የአገሪቱ አንዳንድ ግዛቶች ሰብአዊ ድጋፍና የህክምና እርዳታ የሚሠጡ ባለሙያዎችን ሳይቀር አይናችሁን ለአፈር በሚል ጥቃት በሚያደርሰው አክራሪ የሽብር ቡድኑ አልሻባብ ቁጥጥር ስር መሆን የወረርሽኙን ቀውስ ይበልጥ እንደሚያገዝፈው አትጠራጠሩ›› ብለዋል።
ባለሙያዎቹ በአህጉሪቱ ወረርሽኝኙን ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም ለመፍጠር መደረግ ስለሚኖርበት ጥንቃቄም ምክረ ሃሳባቸውን አጋርተዋል። ዶክተር ሜሪ ስትፈን፣ የመረጃ ልውውጥና ተደራሽነትን ማጎልበት እጅግ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህም የመገናኛ ብዙሃን ቅንጅትና ሁለንተናዊ ሚና የላቀ መሆን እንዳለበት ያስገነዝባሉ። ‹‹የየአገራቱ መንግስታትም በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜትና ፍጥነት ስለወረርሽኙ ወቅታዊ ሁኔታ ለህዝቦቻቸው መረጃ መስጠት አለባቸው›› ነው ያሉት።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖምም፣ በሽታውን ይበልጥ ለመከላከል አገራት የበሽታው ምልክት ያለባቸውን ሰዎች መለየት፣ መመርመር፣ ማስታመም ሌሎች ታማሚዎች መኖር አለመኖራቸውን መከታተል መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/ 2012
ታምራት ተስፋዬ