ከጅማ ዞን 21 ወረዳዎች አንዷ ናት፤ 41 ቀበሌዎችንና አምስት አነስተኛ ከተሞችን ይዛለች። ወደ ሶስት መቶ ሺህ ህዝብም ይኖርባታል። 90 በመቶ ያህሉ ህዝቧ በቡና ምርት ገቢ ይተዳደራል – የኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ጎማ ወረዳ።
የጎማ ወረዳ የአረቢካ ቡና መገኛ ስለመሆኗ የወረዳዋ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቶፊቅ ራያ ይናገራሉ። ወረዳዋ በዓመት ቢያስ ከ17 እስከ 18 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ እንደምታቀርብም ነው የሚገልፁት። የጅማ ዞን ለማዕከላዊ ገበያ ከሚያቀርበው ቡና አንድ ሶስተኛውን የምታቀርበው የጎማ ወረዳ እንደሆነች ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኑሮውን የሚመራውም በቡና መሆኑን ያመለክታሉ።
እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ በወረዳዋ የቡና ምርት ጥራት የተጠበቀ እንዲሆን በሚከናወነው ተግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ የቡና ምርት መጠንም እየጨመረ ይገኛል። ይሁንና አርሶ አደሩ የምርቱ ተጠቃሚ መሆን አልቻልኩም እያለ የተለያዩ ጥያቄዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል። የሚያገኘው ገቢ እና ድካሙ እንደማይመጣጠን ይጠቁማል።
መንግስት ይህን ችግር ለመፍታት እየሰራ መሆኑን አቶ ቶፊቅ ይገልጻሉ። አርሶ አደሩ መጠቀም ይኖርበታል በሚል አዲስ አቅጣጫ በማስቀመጥ ከሁለት ሄክታር መሬት ቡና በላይ ያላቸው አርሶ አደሮች በቀጥታ ቡናቸውን ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዲችሉ እድሉን ማመቻቸቱን ያስረዳሉ። በዚህም መሰረት በጎማ ወረዳ ቢያንስ 105 አርሶ አደሮች ቡናቸውን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ህጋዊ ፈቃድ ማግኘታቸውን ጠቅሰው፣ ህጋዊ ፈቃድ ካገኙት መካከልም ከ15 እስከ 20 የሚደርሱት ቡናቸውን ለውጭ ገበያ መላክ መጀመራቸውን ነው የገለፁት። ይህ በአንድ በኩል አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች አርሶ አደሮች በልማቱ ይበልጥ እንዲሰሩ እንደሚያነሳሳቸው ይጠቅሳሉ።
እንደ አቶ ቶፊቅ ገለፃ፤ ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ውስጥ ከቡና ጋር ተያይዞ በተከናወነው ስራ ውጤት ተገኝቷል። አርሶ አደሩን የውጭ ገበያ እድል ተጠቃሚ መሆን ብቻ ሳይሆን ቡና ገዥ የውጭ ዜጎች አርሶ አደሩ ያለበት ጎማ ወረዳ ድረስ በመምጣት ቡናቸውን በመጎብኘት በቀጣይ ለመግዛት ፍላጎት እንዲያድርባቸው ለማድረግ ፋይዳው ከፍተኛ ነው። ጉብኝታቸው ከውጭ ገበያ ጋር የመገናኘት እድል ከማስፋቱም በተጨማሪ አርሶ አደሩ ጥራት ያለው ቡና እንዲያመርት የሚያነሳሳው ጭምር ይሆናል።
የከታመዱጋ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር ዩኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ አስናቀ ንጋት በበኩላቸው፤ የቀድሞው ዩኒየን አገልግሎቱ ውስን ነበር ይላሉ። አባላቱ በመስማማት የአሁኑን ‹‹ከታመዱጋ›› የሚል ስያሜ ይዞ በአዲስ መልክ በ2009 ዓ.ም እንዲቋቋም መደረጉን ይጠቅሳሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ዩኒየኑ በጅማ ዞን ውስጥ ካሉ ወረዳዎች አምስቱን አቅፎ ይንቀሳቀሳል። ከእነዚህ መካከል አንዱ የጎማ ወረዳ ነው። እነዚህ ወረዳዎች 61 መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት በስራቸው ያሉ ሲሆን፣ 30 ሺህ ቡና አምራች አርሶ አደሮችን አቅፈዋል። ዩኒየኑ በአዲስ መልክ ከተቋቋመ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በቀጥታ ቡና ወደ ውጭ መላክ ጀምሯል። በዩኒየኑ ያሉ አባላትም ዋና ፍላጎታቸው ቡና በጥራት ማምረትና በቀጥታ ወደ ውጭ መላክ ነው።
በዚህም መሰረት በ2009 ዓ.ም አንድ ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ አገር በመላክ ስድስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዶላር ማግኘት መቻሉን አቶ አስናቀ ጠቅሰው፣ በ2010 ዓ.ም ደግሞ አንድ ሺህ 500 ቶን ቡና በመላክ ስምንት ሚሊዮን ዶላር አግኝቷል። በ2011 ዓ.ም አንድ ሺህ 800 ቶን ቡና በመላክ ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል።
ይህም የሚያሳየው ዩኒየኑ በየዓመቱ እያደገ መምጣቱን ነው ያሉት አቶ አስናቀ፣ በዋናነት ዩኒየኑ የተለያዩ መዳረሻዎች እንዳሉት ይገልጻሉ። ከእነዚህም አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ጃፓን፣ እንዲሁም አውስትራሊያ ተጠቃሽ መሆናቸውን ያመለክታሉ።
የጎማ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ጠይቦ አባቡልጉ፤ 30 ነጥብ አንድ ሄክታር የቡና መሬት አላቸው። ባለፈው ዓመት 270 ኬሻ ጀንፈል ቡና አምርተዋል። ዘንድሮ ደግሞ ወደ 480 ኬሻ ጀንፈል ቡና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እያዘጋጁ ናቸው። የቡናው ጥራት የተጠበቀ እንዲሆን ሰፊ ስራ ለመስራት በብዙ ጥረዋል። በቅርቡም ቡናቸውን ለመግዛት ወደ ቡና ማሳቸው የውጭ ዜጎች ብቅ ማለት የጀመሩ ሲሆን፣ በተሻለ ዋጋ ቡናቸውንም እንደሚሸጡ ተስፋ አድርገዋል፤ በዚህም ደስተኛ ሆነዋል። የቡና ዋጋ እንዳይወርድም ቡናውን ከችግኙ ጀምሮ በአለቃቀሙና በአደራረቁ ዙሪያ ጥንቃቄ በማድረግ ጥራቱን ለመጠበቅ ይጥራሉ።
አርሶ አደር አብዱላዚዝ አባዎሊ በበኩላቸው፤ አርሶ አደሩ መቶ በመቶ ተጠቃሚ ነው ማለት እንደማይቻል ጠቅሰው፣ ዩኒየኑ ከተመሰረተ ጀምሮ ግን ለውጦች መኖራቸውን ይናገራሉ። መንግስት ባመቻቸው እድል እርሳቸው ቡና ወደ ውጭ መላክ የሚያስችል ህጋዊ ፈቃድ አግኝተዋል። በዚህ ዓመት ጥራት ያለው ቡና ለውጭ ገበያ ለመላክም መዘጋጀታቸውን ይገልፃሉ። ይህም ጠቀሜታው ለእርሳቸው ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ወደ ዘርፉ ለሚገቡት መነሳሳትን እንደሚፈጥር ያስረዳሉ። ለአገሪቱም ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑን ነው የገለጹት።
ቡናቸውን የውጭ ዜጎች መጥተው መመልከታቸውን ጠቅሰው፣ ይህም መልካም ነው ይላሉ። ወደ አስር ሄክታር በሚሆን መሬት ላይ ቡና እንደሚያመለሙ ጠቅሰው፣ ዘንድሮ ከአንድ ሄክታር ወደ 18 ኩንታል ለማግኘት ተስፋ አድርገዋል። ቡና አምራች አርሶ አደሩ ሁሉ ቡናውን በጥራት ለማምረት ከተነሳሳ ከዚህም በላይ ምርት ማግኘት ይቻላል ያሉት አርሶ አደሩ፣ መንግስት ከገበያው ጋር በተያያዘ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/ 2012
አስቴር ኤልያስ