
በቅጥር ግቢው ውስጥ ጀንፈል ቡና ይወርዳል፤ እልፍ ብሎ ደግሞ ጀንፈል ቡና እንዲደርቅ ሠራተኞች ያስጣጡታል። ደርቆ የተፈለፈለው ጀንፈል ቡና ይበጠራል፤ ይለቀማል፤ ቅሽር ቡናው ይጫናል። ይህ ሁሉ ሂደት ቡናው ተፈልቶ ከመጠጣቱ በፊት የሚከናወን ተግባር ነው – በደረቅ ቡና ማበጠሪያ መጋዘን ውስጥ።
ወይዘሮ ጩኒ ተስፋዬ በመጋዘኑ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላታል። በመጋዘኑ ቡና በማበጠርና በመልቀም ሥራ ላይ የተሰማራች ወጣት ናት። ጠዋት ሁለት ሰዓት ሥራ ገብታ ዘጠኝ ሰዓት ነው የምታወጣው። እሷና ባልደረቦቿ ለአምስት በመሆን ባላቸው ሰዓት እስከ አራት ኩንታል ቡና አበጥረው ይለቅማሉ። በዚህም በቀን እስከ 50 ብር ድረስ ያገኛሉ።
ወጣት አማረ መኮንን በጫኚና አውራጅነት ሥራ ላይ ተሰማርቷል፤ ጀንፈል ቡና የማድረቅ ተግባርም ያከናውናል። ቀኑን ሙሉና ሌሊት ጭምር በፈረቃ እየሰራ መሆኑን ጠቅሶ፣ በዚህ ሥራም ራሱንና ቤተሰቡን እየደጎመ መሆኑን ይናገራል።
አቶ አየሁ ካሰውም እንደ ወጣት አማረ በመጫንና በማውረድ እንዲሁም ቡና በማድረቅ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል። ሥራውም ቀንና ሌሊት በፈረቃ በመስራት በወር እስከ አምስት ሺህ ብር ድረስ በማግኘት ቤተሰባቸውን እንደሚያስተዳድሩ ይገልጻሉ።
አቶ አየሁ በሚሰጣቸው ክፍያ ላይ ግን ቅሬታ አላቸው። በጉልበት ሥራው ከሚያገኙት ብር ጋር ያልተመጣጠነ መሆኑን ተናግረው፣ የቡናው አቧራ እንዲሁም ገለባው ሲቃጠል የሚወጣው ብናኝ በራሱ ችግር እንደሆነባቸው ያብራራሉ።
ቡናቸውን ለማስፈልፈል በቅጥር ግቢው ያገኘናቸው አቶ ገመቹ ቀኖ በዚያው ኢሉባቡር ዞን መቱ ከተማ የ02 ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። የሚተዳደሩት በቡና ንግድ ነው፤ቡናቸውን የሚያቀርቡትም በግል ነው። ቡናውን ከአካባቢው አርሶ አደር ገዝተው መቱ ከተማ ባለው የደረቅ ቡና ማበጠሪያ ያስበጥራሉ። በዚህም ጥራቱን የጠበቀ ቡናን ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ ያቀርባሉ።
ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ መቱ ቅርንጫፍ የመጡበት ዋናው ምክንያት ከቡናቸው ላይ ናሙና ተወስዶ የቡናው ደረጃ እንዲለይ ለማድረግ መሆኑን አቶ ገመቹ ይገልጻሉ። ደረጃ አሰጣጡ የሚያስማማቸው ከሆነ ቡናቸውን ወደ አዲስ አበባ ለሚጭኑ ቡና ነጋዴዎች እንዲሸጥ ያደርጋሉ። ጥራቱን የጠበቀ ቡና አቅርበው ምርት ገበያው ደረጃ ሰባትና ከዚያ በላይ የሚሰጠው ከሆነ ቅሬታ ያቀርባሉ።
አንዳንዴ የደረጃ አሰጣጡ ላይ ስምምነት የማይፈጠር ከሆነ አዲስ አበባ እስከ ዋናው መስሪያ ቤት ድረስ በመሄድ ተገቢውና ትክክለኛው የቡና ደረጃ እንዲሰጥ የሚደረግበት ሁኔታ እንዳለም አቶ ገመቹ ያመለክታሉ። ቡና ነጋዴው ደረጃው እንደገና እንዲታይለት ዋናው መስሪያ ቤት ድረስ በሚሄድበት ወቅት ወጪውን ሁሉ ራሱ ነጋዴው እንደሚያወጣ ነው ያስረዱት።
እዚያ ድረስ በመሄድ ቅሬታ ማቅረቡ ላልተፈለገ ወጪ እንደሚዳርግ ጠቅሰው፣ እሱን ወጪ ለማስመለስ ነጋዴው ወደክስ ሄዶ ሌላ ነገር ከማምጣት መተውን እንደሚመርጥ ያመለክታሉ። ‹‹አሁን ነጋዴው ተደራጅቷልና እንዲህ ዓይነቱ ችግር በሚያጋጥመው ጊዜ በማህበሩ አማካይነት ከዚህ በኋላ መጠየቅ ይችላል›› ሲሉ ያስረዳሉ።
የቡና ጥራት ሲታይም አርሶ አደሩ ፈተናዎች እንደሚገጥሙት ይጠቅሳሉ። ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ አርሶ አደሩ ተረጋግቶ ቡናውን በጥራት እንዳይለቅም ቡናው ለለቀማ ሲደርስ ሌባ ማስቸገሩ ነው።
አርሶ አደሩ ሌባ ቡናውን እንዳይለቅምበት በጥድፊያና ጥራቱን ባልጠበቀ መንገድ ለመልቀም እንደሚገደድ ጠቅሰው፣ አርሶ አደሩ ተረጋግቶ የቡናውን ቀይ ቀዩን ፍሬ ብቻ ቢለቀም ጥራቱ እንደሚጠበቅ እና የልፋቱን ዋጋ እንደሚያገኝም ይገልጻሉ። ጥራት ያለው ቡና ከሆነ ግን ለአርሶ አደሩ፣ ለቡና ነጋዴውም ሆነ ለአገር ፋይዳው የጎላ ነው ይላሉ።
የአቶ ቢኒያም ገብረእግዚአብሔር ደረቅ ቡና ማበጠሪያ መጋዘን ማናጀር ወይዘሮ ራህመቱ መሃመድ እንደሚገልፁት፤ ማበጠሪያ መጋዘኑ በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮችም ሆኑ ቡና ነጋዴዎች ወደ ደረቅ ቡና ማበጠሪያ መጋዘን በመምጣት ጀንፈል ቡናቸውን በማስፈልፈልና በማስበጠር ወደ ቅሽር የማስቀየር አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ያደርጋል።
አንድ ኩንታል ቡና የሚፈጩት በ50 ብር ነው፤ ከተፈጨ በኋላ ደግሞ አንዲት አበጥራ ለምትለቅም ሠራተኛ 70 ብር ነጋዴው የሚከፍል ሲሆን፣ ለጫኚና አውራጅ ደግሞ 50 ብር ይከፍላል፤ በጥቅሉ አንድ ነጋዴ ለማስፈጨቱም፣ለማበጠሩም ሆነ ለመጫን ማውረዱም በአንድ ኩንታል ቡና 170 ብር በመክፈል ነው ከግቢው የሚያወጣው።
የደረቅ ቡና ማበጠሪያው መብራት እስካልጠፋ ድረስ ቀንም ሆነ ሌሊት እስከ 160 ኩንታል አካባቢ እንደሚፈለፍል ማናጀሯ ያመለክታሉ። ይሁንና አብዛኛውን ጊዜ መብራት እየጠፋ እንደሚቸገሩ ይናገራሉ። ሌላው ችግር የአርሶ አደሩ ቡና የሚመጣው በማዳበሪያ መሆኑ የቡና ጥራት ይቀንሳል ሲሉ ይጠቁማሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤የማዳበሪያ ጆንያ ቡና ያጠቁራል። ለዚህ ሁሉ ችግሩ ደግሞ የጆንያ ዋጋ እስከ 90 ብር መሆኑ ነው። ስለዚህ የቡናው ጥራት ይጠበቅ ዘንድ አንዱ መንገድ ቡናው የሚቀርብበት ዕቃ በመሆኑ እዚህ ላይ መንግሥት መላ መፈልግ ይኖርበታል።
ቡና በማዳበሪያ እንዳይያዝ ተነግሯል። እንዲያውም በእነሱ መጋዘን ውስጥ በማዳበሪያ የተቀመጠ ቡና ካለ መጋዘኑ እስከመታሸግ የሚያደርሳቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ አርሶ አደሩ ዘንድም እንዲህ ዓይነቱ ቁጥጥር ቢኖር ለቡና ጥራት መጠበቅ ጥሩ መሆኑን አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 15 /2012
አስቴር ኤልያስ