
በደሌ፡- በኦሮሚያ ክልል በቡኖ በደሌ ዞን የሚመረተውን ቡና በጥራትም ሆነ በብዛት የተሻለ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ገለጹ።
ኃላፊው አቶ ቶሎሳ ቢሎ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ አካባቢው በቡና የሚታወቅ ነው። ነገር ግን ቡናው በዓለም አቀፍ ደረጃ እምብዛም መወዳደር የሚችል ባለመሆኑ በጥራቱና በብዛቱ ላይ በትኩረት እየተሰራበት ይገኛል።
‹‹ዘንድሮ የቡናን ጥራት በተመለከተ የራሱ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየሰራ ነው። በዞን ደረጃ ስለቡና ጥራት ማስተማሩንም በስፋት ጀምረናል።››
ያሉት አቶ ቶሎሳ፣ ኮሚቴው ከሚሰራቸው ነገሮች መካከል የቡናን ጥራት ከፍሬው ጀምሮ ማስጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል። ሌላው ደግሞ አርሶ አደሩ ቡናውን በየቦታው በኮንትሮባንድ መልክ መሸጡን ትቶ በአግባቡ ወደሚመለከተው እንዲያቀርብ መከታተል መሆኑን አስታውቀዋል።
እንደ ኃላፊው ገለፃ፤ በዩኒየንም ይሁን በአርሶ አደሩ ማህበራት የሚቀርበው ቡና ብቻ ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን በርካታ ሥልጠናዎች በዞን ደረጃ ተሰጥተዋል።
ዘንድሮ ጉዳዩ የተያዘው በልዩ ሁኔታ ነው። ትልቁ ግብም ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ በመቅረብ የሚሰጠውን የቡናውን የጥራት ደረጃ በማሻሻል ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ የማስቻል ሥራ መስራት ነው።
የቡናው ጥራት እንዲጠበቅ የአርሶ አደሩ ማህበራትም ሆኑ ዩኒየኑ በአግባቡ እንዲሰሩ እስከ ክልል ድረስ ሂደው ሥልጠና የወሰዱ አካላት አሉ። ስለዚህም በቀጣይ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ይቀርባል የሚል እምነት አለ። ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር ያላቸው ግንኙነትም መልካም የሚባል ነው።
‹‹ለቡና ጥራት መነሻው አርሶ አደሩ አካባቢ ነው፤ ይህን ቡና አስመልክቶ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ትልቅ ኮንፈረንስ ከቀበሌ እስከ ዞን ድረስ ተካሂዷል።›› ያሉት አቶ ቶሎሳ፣ ‹‹ከዚህም የተነሳ ደረጃውን የጠበቀ ቡና በብዛትና በጥራት ለውጭ ገበያ እናቀርባለን የሚል ተስፋ ሰንቀናል።›› ብለዋል።
ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡ ምርቶች ከፍተኛው ቡና እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይ ደግሞ በዞኑ ሁለት ወረዳዎች የሰሊጥ ምርት በማምረት በሰሊጥም ተወዳዳሪ ለመሆን እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
ለቡና ልዩ ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀው፣ ቡና በጥራት እንዲቀርብ የማይናቅ ሥራ መሰራቱን አስረድተዋል። በዚህ ጉዳይ የግብርና ቢሮ፣ የገበያ ልማትም ሆነ የህብረት ሥራ ማህበራቱና ዩኒየኑ በጥምረት እየሰሩ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
በዚህ መልኩ ከተሰራም በቀጣይ ተወዳዳሪ በመሆን የሕዝቡን የኢኮኖሚ ልማትና እድገት በማሳደግ አኗኗርን መቀየር እንደሚቻል ተናግረዋል። በዚህ ረገድ እየተከናወነ ካለው ተግባር ጥሩ ውጤት እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የበደሌ ቅርንጫፍ የጥራት ክፍል ተቆጣጣሪ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣንና በኢትዮጵያ ምርት ገበያ አስተባባሪነት በስፍራው ተገኝቶ ለጎበኘው የጋዜጠኞች ቡድን፣ እንደ በደሌ ቅርንጫፍ የቡና ደረጃው በአብዛኛው ስድስተኛና እስከ ከደረጃ በታች ውስጥ የሚወድቅ እንደሆነ መገለጹ ይታወሳል።
ለዚህም በምክንያትነት የተገለፀው የቡና ጥራት ችግር ነው። የአካባቢው ቡና ደረጃው ዝቅ ማለቱ በተፈጥሮው የጥራት ችግር ኖሮበት ሳይሆን፣ በአለቃቀምና በአያያዝ ጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ እንደሆነም ተነግሯል፤ የቡና ጥራት ተጠብቆ ለውጭ ገበያ መቅረብ እንዲችል የሚመለከታቸው አካላትን ትኩረት የሚሻ መሆኑንም መነገሩ ይታወቃል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 15 /2012
አስቴር ኤልያስ