
አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሁሉም የየብስ ድንበሮች የሰዎች ዝውውር ዕገዳ መጣሉን ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ገለጹ። በበሽታው ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የጸጥታ አካላት ተከታትለው እርምጃ እንዲወስዱ አሳሰቡ። ለመከላከል ሥራው አምስት ቢሊዮን ብር ተመድቦ እየተሰራ እንደሚገኝ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ከክልል ፕሬዚዳንቶችና ከጸጥታ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ቫይረሱን በመከላከል ዝግጅት ላይ ትናንት ዝርዝር ውይይት አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይቱ የተላለፉ ውሳኔዎችን አስመልክተው እንደገለጹት፤ የመከላከያ ሠራዊት በሁሉም የየብስ ድንበሮች ላይ ቁጥጥር ያደርጋል፤ በድንበር በኩል ከመድኃኒት፣ምግብና ነዳጅ በስተቀር የሰዎች ዝውውር ሙሉ ለሙሉ እንዲቆም ተወስኗል።ይህንንም የፌዴራል የጸጥታ ተቋማት የሚያስፈጸሙት ይሆናል።
መንግሥት ቀደም ሲል ካሳለፋቸው ውሳኔዎች በቂ ውጤት ከአልመጣባቸው መካከል ከንኪኪ በመራራቅ፣ በሽታው ከአንዱ ሰው ወደ ሌላው እንዳይተላለፍ በማድረግ ላይ አቅጣጫ ተቀምጦ እንደነበረ አስታውሰዋል።በዚህ በኩል የሃይማኖት አባቶች ለተከታዮቻቸው መልዕክት ማስተላለፋቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ ባለፈው ቅዳሜና እሁድ የነበሩት የቤተ ክርስቲያን መርሀ ግብሮች በበቂ ደረጃ የጥንቃቄ እርምጃዎች ተግባራዊ የተደረገባቸው ስላለመሆናቸው መረዳት መቻሉን ገልጸዋል።
ከስብሰባ ጋር ተያይዞም የመንግሥት ተቋማት ከነጭራሹ እንዳይሰበሰቡ እገዳ ባይጣልም ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መልዕክት ተላልፏል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ፤ በእንዝላልነት የታጨቁ ስብሰባዎች ፈድሞ ማካሄድ የለባቸውም፤ በፓርቲ ስም የሚካሄዱ ስብሰባዎችም በዚሁ አግባብ መታየት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የትኛውም የፓርቲ አባል ሕይወቱን ለአደጋ አሳልፎ ከሚሰጥ ስብሰባ መቆጠብ እንዳለበት ጠቅሰው፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በክልሎች በኩልም የማስተካከያ ተግባራት መውሰድ እንደሚገባቸው መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
መጠጥ ቤቶች፣ ሽሻ ቤቶች፣ ጫት ቤቶች አሁንም ለበሽታው የሚያጋልጡ እንዝላልነቶች ንኪኪዎች የሚስተዋሉባቸው መሆናቸውን ተናግረው፣ በእጅ ዕቃ የሚቀባበሉበት በመሆኑ የጸጥታ ተቋማት ከትናንት ጀምሮ ክትትል እያደረጉ እርምጃ እንዲወስዱ በመንግሥት ውሳኔ የተላለፈ መሆኑን አብራርተዋል።
በሕዝብ ትራንስፖርት የሚጓጓዘው ሕዝብ ብዛት መቀነስ ያሳየ መሆኑን ጠቅሰው፣ አሁንም ጽዳት፣ አቀማመጥና የተሳፋሪ ቁጥርን በሚመለከት አዲስ አበባን ጨምሮ ሁሉም ክልሎች ተጨማሪ ቁጥጥር እንዲያደርጉ ውሳኔ መተላለፉንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የሰዎችን ንክኪ ለመቀነስ እንደየመስሪያ ቤቶቹ ሁኔታ እየታየ ከፊል ሠራተኞች ከቤታቸው ሆነው ሥራቸውን የሚሰሩበትን መንገድ እንዲያመቻቹ፣ የቢሮ አቀማመጥ ትራንስፖርትና አንቅስቃሴ ለንኪኪ የማይመች እንዲሆን ማድረግ ላይ ከመግባባት ተደርሷል ብለዋል።
በየትኛውም ቦታ መንግሥት የሚሰጠውን አቅጣጫ እየተከተሉ ተግባራዊ ማድረግ ግዴታ መሆኑን ያስገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ያ ሳይሆን ቀርቶ ለሚያጋጥም አደጋ በሕግም ፤ በሞራልም እንደሚያስጠይቅ መገንዘብና የማስተካከያ እርምጃ መውስድ ያስፈልጋል ብለዋል።
«በሽታው እንዳይዛመት ጥንቃቄና ዝግጁ ለሚያደርጉ አገራት ቀላል፤ ለተዘናጉ አገራት ዋጋ የሚያስከፍል ስለሆነ መዘናጋት አያስፈልግም»ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤መከላከያ ሠራዊትና ፖሊስ የየራሳቸውን ሙሉ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፤ሠራዊቱና ፖሊስ በአገር ደረጃ በሚፈጠሩ ማንኛቸውም አደጋዎች የተሟላ ግብረ መልስ መስጠት የሚያስችል የሥልጠና፣ የማቴሪያል ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባቸው አቅጣጫ መቀመጡን አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከውጭ የተገኙ ድጋፎችንና ክልሎች የመደቡትን ገንዘብ ጨምሮ አምስት ቢሊዮን ብር ተመድቦ የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተው፣ ተጨማሪ ሀብት መመደብና የሀብት ማፈላለግ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኘም ገልጸዋል። በቀጣይም ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ሀብት የማሰባሰብ ሥራው ይቀጥላልም ነው ያሉት።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የቡድን 20 አባል አገራትን ጨምሮ ከሌሎች ለጋሽ አገራትና ተቋማት ጋር በመሪዎች ደረጃ ውይይት እየተደረገ ይገኛል። የዓለም ባንክ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎች የአፍሪካን ኢኮኖሚ ለመታደግ በፍጥነት ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ መደገፍ ካልቻሉ ጉዳዩ የአህጉሪቱን ኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ይከታል፣ ድሃውን ኅብረተሰብ ይጎዳል።
የበሽታውን ስርጭት ተቋቁሞ ሰዎችን ከህ ልፈት መታደግ እንዲቻል አገራዊ ዝግጅትና ከማህበረሰቡ ጋር ያለው የመረጃ ልውውጥ ወሳኝ መሆኑን አስታውቀው፣ ከሕዝቡ ጋር በመነጋገር ተጨማሪ እርምጃዎች ለመውሰድና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ ለመጠየቅ ይሰራል ሲሉ ገልጸዋል።
የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች በሸቀጦች ላይ አላግባብ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው ትርፍ ለማግበስብስ የሚያደርጉት ጥረት አነስተኛ ገቢ ባለው ኅብረተሰብ ክፍል ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን አስታውቀው፣ ክልሎች እርምጃ እየወሰዱና ፋብሪካዎች ቀጥታ ምርታቸውን ለተ ጠቃሚ እያቀረቡ ጫናውን ለማቅለል በትኩረት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።
ቫይረሱ በኢትዮጵያ በ11 ሰዎች ላይ የተገኘ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣዮቹ ቀናት ቁጥሩ ሊያድግ ስለሚችል ሁሉም ሰው ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
በአፍሪካ የኮሮና ቫይረስ የመስፋፋት ፍጥነት እና በኢትዮጵያ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣት ተጨማሪ ዝግጅት፣ ጥንቃቄና ሥራ እንደሚጠይቅ መረጃዎች ያስገነዝባሉ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 15 ቀን 2012 ዓ.ም
ጌትነት ምህረቴ