አዲስ አበባ፡- የህዳሴው ግድብና የውሃ አጠቃቀም ዙሪያ የሚካሄዱ ድርድሮች ተነጥለው ሊታዩ እንደሚገባ የውሃ ሀብት ምህንድስና ምሁሩ ዶክተር አድማሱ ገበየሁ ተናገሩ፡፡ የአባይ ወንዝንና የህዳሴው ግድብን በሚመለከት ሚዲያዎች ተናበውና ቋሚ አጀንዳ አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባም ተመልክቷል፡፡ በውሃ ሀብት ምህድስና የዓለም አቀፍ አማካሪና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሲቪል ምህንድስና ትምህርት ዘርፍ መምህር ዶክተር አድማሱ ገበየሁ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ በህዳሴው ግድብ ውሃ አሞላልና ተያያዥ ጉዳዮች የሚያደርጉት ድርድር ውስጥ የውሃ አጠቃቀም (ክፍፍል) መካተት የለበትም፡፡ የህዳሴው ግድብና የውሃ አጠቃቀም ድርድሮች የተለያየ መልክ ስላላቸው ተለይተው መካሄድ አለባቸው፡፡
የውሃ ክፍፍል ጉዳይ በድርድሩ ጣልቃ ሳይገባ የህዳሴ ግድብ በውሃ አሞላልና ተያያዥ ጉዳዮች ብቻ ማተኮር ይሻላል፡፡ ኢትዮጵያ ፣ሱዳንና ግብጽ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የሚያደርጉት ድርድር ሦስተኛ ወገን ሳያስገቡ በቴክኒክና በጤነኛ አስተሳሰብ ተመስርተው ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳለባቸው ያመለከቱት ዶክተር አድማሱ፣ የውሃ አጠቃቀም ድርድሩ አስሩን የአባይ ተፋሰስ አገራት የሚያካትት ሲሆን የህዳሴው ግድብ የውሃ አሞላልና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሚደረገው ድርድር ደግሞ ሦስቱን አገራት የሚመለከት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ በውሃ አሞላልና ተያያዥ ጉዳዮች ሦስቱ አገራት በሚያደርጉት ድርድር ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀምን መሰረት ያደረገ እንዲሆን የጸና አቋም እንዳላት ገልጸው፤ በአንጻሩ ግብጽ ያረጀ ያፈጀው የቅኝ ግዛት ውል እንዲጸናላት በተለያዩ መንገዶች በድርድሩ ጣልቃ የምታስገባ መሆኑና አራምባና ቆቦ የመዝለል ጉዳይ ድርድሩን እንዳዘገየው ተናግረዋል። ግድቡ የውሃ አሞላልና ተያያዥ ጉዳዮች ድርድር ከስምንት ዓመታት በላይ ከወሰደ በውሃ አጠቃቀም ዙሪያ የሚገባበት ውል ምን ያህል ጥንቃቄንና በጥልቀት መታየት እንዳለበት ገልጸው ድርድሩ ረጅም ጊዜ ስለሚወስድ ከህዳሴው ግድብ ውሃ አሞላልና ተያያዥ ጉዳዮች ድርድር ተነጥሎ ለብቻው አስሩን የተፋሰሱ አገራት አካቶ መካሄድ እንዳለበትና ከግብጽ በስተቀር ሌሎች የአባይ ተፋሰስ አገሮች የቀኝ ግዛት ውል ምቾት እንዳልሰጣቸውም ዶክተር አድማሱ አስረድተዋል።
“የአባይ ውሃን በተመለከተም የተፋሰሱ ህዝቦች ከላይ እስከ ታች ልክ እንደ አንድ ዜጋ ሊታዩ ይገባል ያሉት ዶክተር አድማሱ ይህ በየራስ መነጽር ሲታይ ላያግባባ ቢችልም፣ የበይ ተመልካች አካሄድ ቀርቶ አስሩም የተፋሰሱ አገራት የውሃ አጠቃቀምን (ክፍፍልን) ጉዳይ በአንድ ላይ ሆነው ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን መሰረት አድርገው ሊደራደሩ ይገባል” ብለዋል ለዘለቄታዊ የሆነው በውሃ አጠቃቀም (ክፍፍል) ዙሪያ የሚደረገው ድርድር አስሩም የተፋሰሱ አገሮች ለዚህ ዘመንና ለወደፊቱ ትውልድ የሚሆን ነገር አስበው፣ አሰላስለው፣ ተደራድረው ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው ያሉት ዶክተር አድማሱ፤ የውሃ አጠቃቀም ድርድሩ ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገና የሁሉንም አገራት ፍላጎት ያጣጣመ ሆኖ ስምምነት የሚደረስበት በመሆኑ ብዙ ዓመታት ሊወስድ እንደሚችል ተናግረዋል።
“ኢትዮጵያ ሌሎች አገራትን ለመጉዳት አስባ አታውቅም ፣የራሷ መብት ግን እንዲከበር ትፈልጋለች” ያሉት ምሁሩ፤ ግብጽ “ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል” እንደሚባለው ሁሉ ትክክለኛ ያልሆነ ሀሳቧን በዓለም ህብረተሰብ ለማስረጽ እየጣረች መሆኑን አመልከተው፣ በአንጻሩ ኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ ተቀባይነት ያለውን ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን መርህ ተከትላ እየሄደች መሆኑን ገልጸዋል።
“ እኔ ብቻ ልጠቀም የሚለው የግብጽ ብልጣብልጥ አካሄድ ዓለም አቀፍ ፍትሀዊ የውሃ አጠቃቀምን መርህ የሚቃረን መሆኑን የገለፁት ዶክተር አድማሱ ይህንን የተሳሳተ አካሄድ ኢትዮጵያ ለማጋለጥና ትክለኛውን እውነታ ለማስገንዘብ የተጠናከረ የዲፕሎማሲ ስራ አጥብቃ መስራትና ወዳጅ ማፍራት ያለባት መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን መንግስት በተፋሰሱ አገራት ትኩረት ሰጥቶ እያካሄደ ያለው የዲፕሎማሲ ስራ የሚበረታታ ተግባር መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል። እንደ ዶክተር አድማሱ ገለጻ፤ ግድቡ የታፋሰሱ የታችኛው አገሮችን የሚጎዳ ሳይሆን እንዲያውም ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል። በበጋ ወቅት የተመጣጠነ ውሃ ማግኘት ያስችላል። ከጎርፍ ይታዳጋቸዋል። ግድቦቻቸው በደለል እንዳይሞሉ ያደርጋል።
“የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ስራ ሲጀምር በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጸኦ አለው” ያሉት ዶክተር አድማሱ በአገሪቱ የሚታየውን የኃይል ስርጭት ጉድለት እንደሚያስተካክልና ኢትዮጵያዊያን በየቤታችን ለመብራት፣ለምግብ ማብሰያና ለፋብሪካዎች የኤሌክትሪክ ሀይል ከማግኘታችን በጨማሪ ለማገዶ ሲባል የሚደረገው የደን ምንጣሮ እንደሚቀንስም ጠቁመዋል። ከዚህም ባሻገር ታላቁ የህዳሴ ግድብ እናቶችን ከጭስ የሚገላግል፣ የተረፈውን የኤሌክትሪክ ሀይል በመሸጥም ለአገሪቷ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት የሚያስችል ዘርፈብዙ ጠቀሜታ አለው ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።
ጥንትም ሆነ ዛሬ ያሉ የኢትዮጵያ መሪዎች በዲፕሎማሲው ረገድ በአባይ ወንዝ ጉዳይ የኢትዮጵያን ጥቅም በማስጠበቅ ረገድ ክፍተት እንዳልፈጠሩ ገልጸው የዲፕሎማሲው ፍልሚያ የደጀን ድጋፍ ስለሚፈልግ የኢትዮጵያ ህዝብና ሚዲያው ጠንካራ ደጀን መሆን እንዳለባቸው ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል።
ዶክተር አድማሱ ገበየሁ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይ የድንበር አቋራጭ ወንዞች ላይ በመካከለኛው ምስራቅ እስያና በአፍሪካ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ኢፍራተስና ትግረስ ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተደረጉ ጥናቶች ተየተሳተፉ ሲሆን ሲዊኮ በሚባል ዓለም አቀፍ ድርጅት የፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ሆነውም ሰርተዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 11 ቀን 2012 ዓ.ም
ጌትነት ምህረቴ