በአሁኑ ወቅት ዓለማችን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እየተፈተነች ትገኛለች፡፡ በቫይረሱም ምክንያት ሰው እንደ ቅጠል በእያንዳንዱ ሰከንድ ይረግፋል። በሽታው በትንፋሽና በንክኪ በቀላሉ የሚዛመት መሆኑ ደግሞ ስርጭቱን በቀላሉ ለመቆጣጠር አዳጋች አድርጎታል፡፡
ታዲያ በዚህ የዓለማችን ስጋት በሆነው በሽታ ስጋት የገባው አባወራ ራሱንና ልጆቹን ለማዳን ያደረገው ድርጊት የሰሞኑ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው ግለሰቡ የሊትዌንያ ነዋሪ ሲሆን በኮኖራ ቫይረስ ተይዛለች በሚል ስጋት ባለቤቱን መታጠቢያ ቤት በማስገባት ቆልፎባት፤ እንዳትወጣም የከለከላት ሲሆን ይህ ድርጊቱም ዓለምን ጉድ አሰኝቷል፡፡
ባሳለፍነው የካቲት ወር አጋማሽ በሊትዌንያን ቪሊኒዩስ የሚገኝ ፖሊስ በአካባቢው ከሚገኝ አንድ ስፍራ አስጨናቂ የስልክ ጥሪ ይደርሳቸዋል፡፡ ለፖሊስ የደረሰው ጥሪም በመኖሪያ ቤቷ መታጠቢያ ቤት በባልዋና በሁለት ልጆቿ የተቆለፈባት አንድ እንስት ጥሪ ነበር፡፡
ወደ ጥሪው ቦታ ያመራው የፖሊስ ቡድን ወደ ትዕይንቱ ቦታ ሲደረስ ድርጊቱን የፈፀመው አባወራ ያለአንዳች ፍርሐት የመኖሪያ ቤቱን በር በመክፈት ሚስቱን በመታጠቢያ ቤት እንደቆለፈባት በመግለጽ ይህንንም ያደረገው ከኮሮና ቫይረስ ጥቃት ራሱንና ልጆቹን ለመከላከል አስቦ ያደረገው መሆኑን ተናግሯል፡፡
የአካባቢው ብሄራዊ ፖሊስ ቃል አቀባይ ራሙናስ ማቶኒስ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት “አባወራውና ሁለቱ ጎረምሳ ልጆቹ እማወራዋን ከመታጠቢያ ቤት እንዳትወጣ የከለከሏት በኮሮና ቫይረስ ተጠቅታ ሊሆን እንደሚችል እንደምትጠረጥር ስለነገረቻቸው ነው፡፡
ሴትየዋ ወደ ጣሊያን ሄዳ በነበረበት ወቅት ከወደ ቻይና ከመጡ ሰዎችም ጋር ተገናኝታ ስለነበር በዚህም ምክንያት በኮሮና ቫይረስ ተጠቅታ ሊሆን እንደሚችል ስጋት እንደገባት ለባለቤቷ ታጫውተዋለች፤ታዲያ በጉዳዩ ላይ ቀልድ የማያውቀው አባወራም ነገሩን በቸልታ አልተመለከተውም አባወራው በአስቸኳይ አንድ የህክምና ዶክተር ጠርቶ በኮሮና ቫይረስ ተጠቅታ ሊሆን እንደሚችል ስጋቱን ነገረው። ሀኪሙም “የእብድ ገላጋይ ድንጋይ ያቀብላል” እንደሚባለው ሙያውን ዘንግቶ ለሰውየው ሴትየዋን ገለል እንዲያደርጋት ይመክረዋል፡፡ አባወራውም የሀኪሙን ምክር በመስማት ከሁለት ልጆቹ ጋር በመሆን እማወራዋን በመታጠቢያ ቤት በማስገባት ቆለፉባት፡፡
ሰውየው እንደተናገረው በሚስቱ ላይ አንዳች ጉዳት ለማድረስ ወጥኖ የሠራው እንዳልሆነና እንዲያው ዝም ብሎ የዶክተሩን ምክር ተከትሎ ሚስቱ በሽታውን እንዳታሰራጭ ለመከላከል ያደረገው መሆኑን ገልጿል፡፡ በድርጊቱ የተከሰተ ምንም ጥቃት የሌለ ሲሆን በሴትየዋም በኩል የቀረበ ቅሬታ የለም፤ስለዚህ ፖሊስ አምቡላንስ በመጥራ ሴትየዋ በሽታዋን እንድትመረመር ወስዷታል፡፡
በመጨረሻ የባልየው ጭንቀትና ፍራቻ መሠረት የለሽ መሆኑንና ሴትየዋም ተመርምራ ከኮሮና ቫይረስ ነፃ መሆኗ ተረጋግጧል፡፡ ቢሆንም ግን ይህ ክስተት ኮቪድ 19 ምን ያህል ሰዎች ላይ ተፅዕኖ እያደረሰ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ሰዎች ራሳቸውን ከበሽታው ነፃ ለማድረግ የትዳር አጋራቸውን መታጠቢያ ቤት ውስጥ ቆልፈው መውጣት ከጀመሩ ጉዳዩ ምን ያህል አሳሳቢ መሆኑን ያሳያናል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ