ከመግቢያው በስተቀኝ የአንድ መስኮት አገልግሎት የሚሰጥበት ትልቅ ሕንፃና ትንሽ አለፍ ብሎ ደግሞ ጤና ጣቢያ ይታያል። በስተግራ ግራ ደግሞ ፖሊስ ጣቢያ እና የእሳት አደጋ መከላከያና መቆጣጠሪያ ሕንፃዎች ይገኛሉ። ከእነዚህ ውጪ አንደም ሕንፃ አይታይም በቂሊንጦ የኢንዱስትሪ ፓርክ።
ይህ በ279 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ፓርክ፣ፓርኩ መሰረተ ልማቶች ብቻ እንዲሟሉለት ተደርጎ ዓለሚዎችን እየተጠባበቀ ነው። ሰፋፊ መንገዶች ተገንብተውለታል። የኤሌክትሪክና የስልክ ሳጥኖች በተለያዩ ቦታዎች ላይ ይታያሉ። የመንገድ መብራቶችም ተገጥመዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኩ የተገነባው መድኃኒትና የህክምና መሳሪያዎችን ለሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ነው። በቅርቡም አፍሪ ኪዩር የተሰኘ የመድኃኒት አምራች ኩባንያ የመድኃኒት ፋብሪካ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ አስቀምጧል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሙኒር ካሳ እንዳሉት በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከሚኖረው ህዝብ ውስጥ 57 በመቶ የሚሆነው የሚሞተው በኢንፌክሽን አማካኝነት በሚመጡ የተለያዩ በሽታዎች እና በእናቶች እና ሕፃናት ሞት ነው። ፋብሪካው እንደሚያመርት ከሚጠበቁት መድኃኒቶች መካከል ኢንፌክሽንን ማክም እና ወባን መከላከል የሚያስችሉ መድኃኒቶች መሆናቸው ደግሞ የፋብሪካውን ፋይዳ ያጎላዋል። 37 በመቶው የሚሞተው ደግሞ በስኳር፣ ደም ግፊትና የልብ በሽታ መሆኑን ዶክተር ሙኒር ጠቅሰው፤ ፋብሪካው እነዚህን በሽታዎች ማከም የሚያስችሉ መድኃኒቶ እንደሚያመርት ከምርቶቹ ዝርዝሮች መመልከታቸውን ይገልጻሉ። ሌላው የሞት ምክንያት አደጋ /ኢንጁሪ ትራውማ/ መሆኑን ተናግረው፣ለዚህም የሚሆኑ መድኃኒቶች እንዳሉ ከዝርዝሩ መመልከታቸውን ዶክተር ሙኒር ይገልጻሉ መድኃኒቶቹ በጥራት የሚመረቱ ከሆነ ተፈላጊ መሆናቸው ይጨምራል ይላሉ።
‹‹በእኛ የግዥ ስርዓት መድኃኒት ዛሬ ብናዝ የምናገኘው ከዓመት በኋላ ነው፤ በዚህ መዘግየት በርካታ ጉዳት እየደረሰ ነው።›› ያሉት ዶክተር ሙኒር፣ የፋብሪካው በኢትዮጵያ መገንባት ይህን ችግር በወሳኝ መልኩ እንደሚፈታ ያስረዳሉ።
የአፍሪኪዩር መድኃኒት ፋብሪካ የአክሲዮን ባለድርሻ ዶክተር ታደሰ ተፈሪ በበኩላቸው እንደሚሉት፤የመድኃኒት ፋብሪካው የግንባታ፣ ደረጃ እና ፈቃድ ማውጣቱን ጨምሮ ወደ ማምረት እስኪገባ ድረስ 10 ሚሊዮን ዶላር ተይዞለታል። ከመጀመሪያው ዓመት ምርት በኋላም የምርቱን 25 በመቶ ወደ ውጪ ይልካል። ይህም በየዓመቱ በ10 እና 15 በመቶ እያደገ በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ እስከ 60 በመቶ እንዲደርስ ይደረጋል
የኢትዮጵያ የመድኃኒት ገበያ ከሚፈልገው ከ65 በመቶ በላይ የሚሆኑትን የመድኃኒት ዓይነቶች ያመርታል። በአንድ ፈረቃ 103 ቢሊዮን ታብሌቶችንና 14 ሚሊዮን ጠርሙስ ሽሮፖችን የማምረት አቅምም አለው። ከምርቶቹ መካከል በሰፊው የሚፈለጉ እንደ አምፒሲሊንና ፔኒሲሊን የመሳሰሉት ይገኙበታል። ከዚህ በተጨማሪም የእነዚህ ቤተሰብ የሆኑ ከ20 የማያንሱ መድኃኒቶችንም ያመርታል።
በኢትዮጵያ እንዲሁም በአፍሪካ ያለው የመድኃት ፍላጎት ለፋብሪካው ጥሩ ገበያ መሆኑን ዶክተር ታደሰ ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ የመድኃኒት ገበያ እያስመዘገበች ከምትገኘው የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ተያይዞ እየጨመረ መሆኑን ያመለክታሉ። ‹‹የመድኃኒት ፍላጎቱም በየዓመቱ በ25 በመቶ እያደገ መጥቷል፤ የጤና ፋሲሊቲዎች ጨምረዋል›› ይላሉ። ‹‹የህክምና ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለሁ የነበሩት የጤና ትምህርት ቤቶች ሦስት ነበሩ›› ያሉት ዶክተር ታደሰ፤ በአሁኑ ወቅት ከ35 በላይ የህክምና ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ ይህም የሚያመለክተው የፕሪስክሪፕሽን ፓተርኑ የሚቀየር በመሆኑ ብዙ መድኃኒት ያስፈልጋል እንደማለት ነው›› ሲሉ ያብራራሉ።
በአሁኑ ሰዓት አፍሪካ ከምትጠቀማቸው መድኃኒቶች ውስጥ ከ3 በመቶ ያነሰውን ብቻ እንደምታመርት ጠቅሰው፣ በዚህ ዓመት መጨረሻ የኢትዮጵያ የፋርማሲዩቲካል ገበያ ወደ አንድ ቢሊየን እንዲሁም የአፍሪካ ወደ 52 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ይጠበቃል ይላሉ።
እንደዚህ በፍጥነት የሚሰፋ የፋርማሲዩቲካል ገበያ ላይ ሀገሪቱ መድኃኒት በሚገባ ማምረት ካልቻለች የውጭ ምንዛሬ ጫናው እንደሚጨምርም ያስገነዝባሉ። የመኃኒት ፋብሪካዎችን በመክፈት ከውጭ የሚገባውን መጠን ትርጉም ባለው መልኩ በመቀነስ ኢትዮጵያ መቆጠብ ያለባትን የውጭ ምንዛሬ ማዳን እንደሚቻል ያስታውቃሉ።
ዶክተር ታደሰ አፍሪኪዩር ህንድን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች ፋብሪካዎች እንዳሉት ጠቅሰው፣ እስከ 9 ሚሊዮን ዶላር የሚሆን ዓመታዊ ሽያጭም እንዳለው ይጠቅሳሉ። በኢትዮጵያ የሚገነባቸው ፋብሪካ ምርቶቹን ወደ አስር የአፍሪካ ሀገሮች በመላክ የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስገኝም ይጠቁማሉ።
ፋብሪካው ሥራ ሲጀምር ለ109 ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚከፍትም ይገልጻሉ። ከአዚህ ውስጥ 95 በመቶዎቹ ኢትዮጵያውያን እንደሚሆኑ ተናግረው፤ የተቀሩት የውጭ ዜጎች መሆናቸውን ያብራራሉ። ‹‹በሂደት የቀረው አምስት በመቶ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ከተካሄደ በኋላ በኢትዮጵያውያን ይሻፈናል። አቅም ላላቸው ሴቶችም ቅድሚያ ይሰጣል›› ሲሉ ይናገራሉ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2012
ታምራት ተስፋዬ