የኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የሰሞኑ አጀንዳ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ነው። ህዳሴ ግድብ ከፍተኛ መስዋእትነት እየተከፈለበት ግንባታው አሁን 71 በመቶ ደርሷል። ህዝቡም ተርፎት ሳይሆን ከጎደሎው እየቆጠበ ለግንባታው የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል እያረጋገጠ ይገኛል። ይህም መንግሥትና ህዝብ ይህን ኃላፊነታቸውን ከመወጣት እንደማይቆጠቡ ያረጋግጣል።
ኢትዮጵያ በአባይ ላይ ይህን ያህል ግዙፍ ግድብ ለመገንባት ስትነሳ ግብፅ ግንባታውን በጸጋ ትቀበለዋለች ብላ አይደለም። ካላት የመልማት ፍላጎት ፣ ውሃውን በፍትሐዊነት ለመጠቀም ካላት መብት እና ዓለም አቀፍ ህግ በመነሳት ነው ወደ ግንባታው የገባቸው።
በትብብር ለመልማት ካላት ጽኑ ፍላጎት በመነጨም በተለይ ከታችኛው የተፋሰሱ ሀገሮች ጋር እየሠራች ትገኛለች። ለግልጽነት በሚልም ግንባታውን ግብፅን ጭምር አስጎብኝታለች። ግብፅ ይህን ግልጽነትና ለትብብር የተዘረጋ እጅ መመልከት ሳትሻ ፣ የኢትዮጵያን በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብት ዛሬም ፊት ለፊትና በእጅ አዙር እየተገዳደረች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ አለቃቀቅ እና ግድብ አሞላል ላይ ድርድር ሲያደርጉ መቆየታቸውና ድርድሩ በማያባራው የግብፅ የራስ ወዳድነት ፍላጎት የተነሳ ተቋርጦ እንደነበር ይታወሳል። ይህ ድርድር በቅርቡ በዓለም ባንክ እና በአሜሪካ መንግሥት ታዛቢነት ቀጥሎ የድርድሩ አዝማሚያ ያላማራት ኢትዮጵያ በድርድሩ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ በቅድሚያ መምከር እንደምትፈልግ በመግለጽ ከድርድሩ መቅረቷን ተከትሎ የአሜሪካ መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ ኢትዮጵያውያንን በእጅጉ አስቆጥቷል።
መጀመሪያ የድርድሩ ታዛቢ በኋላ ደግሞ አደራዳሪ የነበረው የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ለግብፅ ያደላውን የድርድር ሰነድ ሳትፈርም በግድቡ ውሃ መያዝም ሆነ ኃይል መማንጨት የለባትም የሚል ተቀባይነት የሌለውና ኢፍትሐዊ መግለጫ አውጥቷል። ይህ የአሜሪካ መንግሥት ድርጊት ኢትዮጵያውያንን አስቆጥቷል። “ግብፅ ኢትዮጵያ የያዘችውን አቋም ተከትሎ እንዳለፉት ዘመናት ሁሉ ጦሯን በተጠንቀቅ አቁማለች፤ የውክልና ጦርነት ልታካሂድም ትችላለች” የሚሉ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ናቸው።
እርግጥ ነው ግብፅ በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ የሚንቀሳቀሱ ፀረ መንግሥትና ህዝብ ኃይሎችንና የመሳሰሉትን በመደገፍ ህዝቡን እርስ በእርስ ለማጋጨት እንዲሁም በመንግሥት ላይ እንዲነሳ ለማድረግ የማትፈነቅለው ድንጋይ ላይኖር ይችላል። ይሁንና ኢትዮጵያውያን ግን በሉአላዊነታቸው ፣በውሃቸው የሚመጣውን ማንኛውንም ጥቃት እንዳለፉት ዘመናት ሁሉ በማክሸፍ በድል እንደሚወጡት አይጠረጠርም።
ግብፅ በግድብ አሞላል እና ውሃ አለቃቀቅ ላይ በተከታታይ ውይይት ሲካሄድ ቢቆይም፣ በድርድሩ ላይ አዳዲስ ሃሳቦችን በማንሳት እንደለመደችው ድርድሩን ስትጎትት ቆይታለች። በቅርቡ ደግሞ አሜሪካ እና የዓለም ባንክ ታዛቢ ሆነው በጀመሩት ኋላ ላይ አደራዳሪ በሆኑበት ድርድርም ነገሮች ለግብፅ የሚያደሉ ውሳኔዎች እንዲተላለፉ በማድረግ ታሪካዊ ስህተት ይሉት ሸፍጥ ፈጽማለች።
እነዚህ ሁሉ የአሜሪካም ሆኑ የግብፅ ዕርምጃዎች ኢትዮጵያውያን የአባይን ውሃ በፍትሐዊነት ለመጠቀም የሚያካሂዱትን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለአፍታም አያቆሙትም። ይልቁኑም ህዝብና መንግሥት ግንባታው ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ ለማጠናቀቅ እንዲረባረቡ ነው የሚያደርጉት።
ግብፅ ግንባታውን በቀጥታ ባታስጓጉል እንኳ እንዲጓተት ለማድረግ እንዳለፉት ዘመናት ሁሉ መንግሥትን የሚቀናቀኑ እንዲሁም ሌሎች አኩራፊዎችን ልታንቀሳቀስ ትችል ይሆናል። ይህም ቢሆን ታሪክ እንደሚያስገነዝበው እነዚህ ኃይሎች የእሳት እራት ሆነው ይቀራሉ እንጂ የግድቡ ግንባታ ከፍጥነቱ አይስተጓጎልም፤ ይልቁኑ የግብፅም ሆነች የቲፎዞዎቿ ፍላጎት ቅዠት ሆኖ ይቀራል።
የኢትዮጵያ ህዝብ የእነዚህን ኃይሎች ከንቱ የተለመደ ሴራ ለማምከን ልክ እንዳለፉት ዘመናት ልዩነታቸውን ወደጎን በመተው በአንድነታቸው ጸንተው መሥራት ይኖርባቸዋል። ለእዚህም በመካከላቸው ሊኖር የሚችለውን ክፍተት ለማጥበብ ብሎም ለመድፈን በትኩረት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።
ኢትዮጵያ ራሷን ከወራሪም ሆነ ከጣልቃ ገብ የመጠበቅ ልምዱ አላት። ይህን ልምዷን እየተጠቀመች ልማት የሚያደናቅፉ የትኛቸውንም እንቅስቃሴዎች ማስቆም ይኖርባታል። ለእዚህ ደግሞ መንግሥትና ህዝቡ እጅና ጓንት ሆነው በአንድ ልብ ጣልቃ ገብነትን ሊከላከሉ ይገባል።
ብልህ ቸግርን ወደ ውጤት ይቀይራል እንደሚባለው አሁን የተፈጠረውን አጋጣሚ ኢትዮጵያውያን በሚገባ ይሠሩበታል። ክፉ ጎረቤት ዕቃ ያስገዛል እንደሚባለውም ኢትዮጵያውያን ግድቡን ፈጥነው በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ለማስገባት እንደ መልካም አጋጣሚ ሊጠቀሙበት ይገባል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2012