
እቴነሽ ሽብሩ ትባላለች። የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በሳምንቱ መጨረሻ በ30ኛ ዙር ካስመረቃቸው የፖሊስ አባላት መካከል አንዷ ናት። እቴነሽ፣ ‹‹ሰላም የሁሉም መክፈቻ ቁልፍ ናት፤ በአንድ አገር የሰላም አየር እንዲነፍስ ደግሞ የሁሉንም ኃላፊነት መቀበል ብሎም መስዋዕትነት መክፈልን ይጠይቃል።›› ስትል ትናገራለች። ‹‹እኔ ለሰላም ዘብ ለመቆም የወሰንኩትና ሃላፊነት የተረከብኩትም የሰላም መደፍረስ የሚያስከትለውን ጥቁር ጠባሳ ጠንቅቄ ስለማውቅ ብሎም የሰላምን ትልቅ ዋጋ በመረዳት ነው።›› በማለትም ታክላች።
ከቡኖ በደሌ በመምጣት በቡልቡላ ፖሊስ ማሰልጠኛ ጣቢያ ለስድስት ወራት ስልጠናዋን እንደተከታተለችና በቆይታዋም ከባድ ውጣውረዶችን በመቋቋም አስፈላጊ እውቀትን መጨበጧን የምትገልፀው እቴነሽ፣ በስልጠና ባገኘችው የሥነ ምግባርም ሆነ አካል ብቃት አቅም የክልሉ ብሎም የአገርን የፀጥታ ችግሮች ለመከላከልና ሰላም የሚያደፈርሱትን ያለ ምህረት ለመታገል ዝግጁ ስለመሆኗ ታስገነዝባለች።
ክልሉን በፀጥታ ሃይል ማጠናከሩ በየጊዜው የሚፈጠሩ የሰላም ሥጋቶችን ለማስወገድና ሕገ ወጥ ድርጊቶች ለማስቆም ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ያሰመረችበት እቴነሽ፣ የፖሊስ አባላቱም ካለ ምንም አድልዎ ሁሉምን በክልሉ የሚኖሩ ብሔር፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን ለማገልገል በቂ ስልጠና ስለመውሰዳቸው ነው የምትናገረው።
ለአገር ሰላም መሆን በተለይ ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን በሚደረግ ጥረት ግንባር ቀደም ተዋናይ የሆኑ የፀጥታ አካላት ሃላፊነታቸውን በከፍተኛ ጥንቃቄ መከወን እንዳለባቸው አጽዕኖት የምትሰጠው እቴነሽ፣ ከፀጥታ አካላቱ ባሻገር የሰላም የመጀመሪያ ተጠቃሚ ህዝብ እንደመሆኑ ባለቤቷ እና ጠባቂዋም ህዝብ መሆን አለበትም ነው ያለችው።
ሌላኛው ተመራቂ ልዩ የፖሊስ አባል ኢብራሂም አብዱልጀማልም የእቴነሽን ሐሳብ ይጋራል። ከምሥራቅ ሐረርጌ የመጣው ኢብራሂም፣ በክልሉ ብሎም በአገር ጠንካራና አስተማማኝ ሰላም እንዲረጋገጥ የፀጥታ መዋቅሩ የጀመራቸው ቅንጅታዊ አሠራሮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ሃላፊነቱን በቁርጠኝነት ለመወጣት መዘጋጀቱን ይገልፃል።
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሰላም ጠንቅ የሆኑ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ያስታወሰው ተመራቂ ፖሊሱ፣ ከፀጥታ አካላት ባሻገር ህዝቡ ሰላምና ደኅንነት እንዲጠበቅ መሥራት እንደሚገባው ይናገራል፤ ከሁሉም በላይ ሰላሙን ማስበለጥ እንዳለበትም ነው ያስገነዘበው።
ከአርሲ የመጣው ተመራቂ ሱልጣን አብዲም፣ ተመራቂ የፖሊስ አባላቱም የህዝቡን ፀጥታና ደህንነት በመጠበቅ በክልሉ ያለውን የሕግ የበላይነት ለማጠናከር እንደሚያግዙ ይጠቁማል። ከሁሉ በላይ መጪውን አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ከማድረግ አንፃር የልዩ ፖሊሱ አባላት ሚና የጎላ ስለመሆኑ ነው ያመለከተው።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ኮማንደር ጌታቸው ኢታና፣ የዜጎችን ሰላም ለማስጠበቅና ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ ከማድረግ ባሻገር የፀጥታ አካላት ህዝቡን በእውቀት መምራት እንዲችሉ ኮሌጁ በልዩ ትኩረት ብሎም አስፈላጊውን ስልጠና በመስጠት ላይ ስለመሆኑ ይገልፃሉ።
ተመራቂ ልዩ ፖሊሶችም በሥነ ምግባርም ሆነ በአካል ብቃት አቅም ፈጥረው ለታላቅ የግዳጅ አገልግሎት መዘጋጀታቸውን ያመላከቱት ኮማንደሩ፤ በስልጠናቸውም ስለ ሕገ መንግሥት እንዲሁም ስለ ሰብአዊ መብት አያያዝ በቂ እውቀት እንዲያገኙና ብቁ ሆነው እንዲወጡ መደረጉን ነው ያብራሩት።
ተመራቂ ልዩ የፖሊስ አባላቱም በስልጠናቸው ያካበቱትን አቅም በተለይ ህዝብና መንግሥት የሰጣቸውን ሃላፊነት፣ ሕግና ሥርዓትን እንዲሁም የሕዝብ ፍላጎትን መሠረት አድርገው እንዲያከናውኑም ነው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት።
አሁን ባለንበት ዓለም ሰላም የሚረጋገጠው በአንድ ወገን አስተዋጽኦ አለመሆኑን ያስገነዘቡት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የሰላም አየር እንዲነፍስ የሁሉንም ፈጣን መልስና ተሳታፊነትን እንደሚጠይቅና በተለይ ህዝቡ የሰላሙን እሴት መጠብቅ እንዳለበት ነው ያመለከቱት።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ ኦሮሚያ ዛሬ ላይ ከመደረሷ ቀድሞ ብዙ ውጣውረዶች ማሳለፍ የቻለችው ትናንት የሕይወት መስዋትነት በከፈሉና አሁንም ባላት ውድና ቆራጥ ጀግኖቿ ገድል መሆኑን አስታውሰዋል፤ ተመራቂ የልዩ ሃይል ፖሊስ አባላቱም ኦሮሚያን የሚገነቡ፣ ኢትዮጵያን የሚያሻግሩ እንዲሁም ለታላቅ ተልዕኮ የታጩ ጀግኖች ስለመሆናቸው እንዲያስቡ አስገንዝበዋል።
‹‹ለሰው ሰላም ከመቆምና ራስን ለሌላው መስዋዕት ከማድረግ በላይ ምንም የለም።›› ያሉት ርዕሰ መስተዳዳሩ፣ ተመራቂ አባላቱም ህዝብና መንግሥት የሰጣቸውን ታላቅ ተልዕኮ በሥልጠና ባካበቱት እውቀት በመደገፍ በከፍተኛ ሙያዊ ብቃትና ሃላፊነት ክልሉን ብሎም አገርን ማገልገል እንዳለባቸውም ነው ያሳሰቡት።
ተመራቂ ልዩ የፖሊስ አባላቱ በክልሉ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት እንዲከበር ብሎም በሰላምና በደስታ እንዲኖር በአሁን ወቅት የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል ከሁሉም በላይ ህዝብና የሕግ ሥርዓትን ማዕከል በማድረግ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ነው ጥሪያቸውን ያቀረቡት።
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2012
ታምራት ተስፋዬ